በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 20ኛ ሳምንት ወደ ይርጋለም የተጓዘው ጅማ አባጅፋር ሲዳማ ቡናን 3-1 በማሸነፍ የሊጉን መሪነት ከደደቢት ላይ ተረክቧል። በሊጉ የተንራፋው ስርዓት አልበኝነት ዛሬም በይርጋለም ተከስቶ አልፏል፡፡
እንደተለመደው የኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙር ተዘምሮ በተጀመረው ጨዋታ ባለሜዳው ሲዳማ ቡና በ19ኛው ሳምንት በቅዱስ ጊዮርጊስ ከተረታበት ስብስብ የአምስት ተጫዋቾችን ለውጥ አድርጓል። በግሩም አሰፋ፣ አብዱለጢፍ መሀመድ ፍፁም ተፈሪ፣ ወንድምነህ አይናለም እና ሙጃይድ መሀመድ ምትክም አዲሱ ተስፋዬ፣ ትርታዬ ደመቀ ወንድሜነህ ዘሪሁን፣ ዮሴፍ ዮሀንስ እና ማይክል አናንን በማሰለፍ በ4-2-3-1 አሰላለፍ ወደ ሜዳ ገብቷል። አባጅፋሮች ደግም መቐለን በሜዳቸው ከረቱበት ስብስብ ኤልያስ አታሮን በነጅብ ሳኒ ብቻ ተክተው በ4-4-2 አሰላለፍ ወደ ሜዳ ገብተዋል።
በፌዴራል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ በልዩ ብቃት ታግዞ የተካሄደው ጨዋታ ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ ሲታይበት ሁለቱም በመስመር በኩል ማጥቃትን ምርጫቸው አድርገዋል። ጨዋታው ገና 1 ደቂቃን እንዳስቆጠረ ከወንድሜነህ ዘሪሁን ከቀኝ መስመር የላከለትን ኳስ ባዬ ተቆጣጥሮ ለትርታዬ ሰጥቶት ትርታዬ አክርሮ ወደ ግብ በመሞከር ዳንኤል አጄይ የያዘበት ኳስ ቀዳሚዋ ሙከራ ነበረች። በ3ኛው ደቂቃም በድጋሚ ከባዬ ገዛኸኝ ኳስ ያገኘው ትርታዬ በግንባሩ ገጭቶ ወደ ውጪ ወታበታለች። በጅማ አባጅፋሮች በኩል 14ኛው ደቂቃ ላይ ሳምሶን ቆልቻ ሄኖክ አዱኛ ያሻማውን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ግብ ቢያስቆጥርም የእለቱ 1ኛ ረዳት ዳኛ ዳንኤል ዘለቀ ከጨዋታ ውጭ ነው በማለት ግቧን ሽረዋታል፡፡ ከዚህች ቅፅበት በኃላ በመልሶ ማጥቃት በ21ኛው ደቂቃ ላይ ትርታዬ ደመቀ ከማዕዘን ምት ያሻማትን ኳስ ማይክል አናን በግንባሩ ገጭቶ ቢሞክርም በእለቱ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ጋናዊው ግብ ጠባቂ ዳንኤል አጄይ እንደምንም መልሶበታል፡፡
አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ በግራ በኩል የነበረው ዮናስ ገረመውን ወደ ቀኝ መስመር ካመጡት በኋላ ተጫዋቹ ከመስመር ተከላካዩ ኄኖክ አዱኛ ጋር በአንድ ሁለት ቅብብሎች በተደጋጋሚ ወደ ሲዳማ የግብ ክልል እንዲደርሱ አስችሏቸዋል። በዚህ ሁኔታ 31ኛው ደቂቃ ላይ ኄኖክ ከማዕዘን ያሻማውን ኳስ ሳምሶን ቆልቻ በግንባሩ ገጭቶ ሲሞክር ግብ ጠባቂው ፍቅሩ ወዴሳ ቢመልሰውም በአቅራቢያው የነበረው አዳማ ሲሶኮ ጀ ግብነት ለውጦ ጅማን ቀዳሚ አድርጓል።
ጅማ አባ ጅፋሮች ከዚህ ግብ በኋላ በሊጉ የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ኦኪኪ አፎላቢ አማካኝነት በተደጋጋሚ የሚፈጥሩት ጫና ለሲዳማ ቡና ተከላካዮች እጅግ ሲከብዳቸው ታይቷል። ሲዳማ ቡናም አቻ ለመሆን በባዬ ገዛኸኝ እና አዲስ ግደይ አማካኝነት አቻ ለመሆን የሚያስችላቸውን አጋጣሚን አግኝተው በቀላሉ ሲያመክኑ ተስተውሏል። 39ኛው ደቂቃ ላይ ዮናስ ገረመው በቀኝ በኩል በቀጥታ ወደ ሳጥን የላካት ኳስ ኦኪኪ አፎላቢ ጋር ደርሳ ናይጄርያዊ አጥቂ የሲዳማ ተከላካዮችን ሰህተት በመጠቀም ሁለተኛ ግብ አስቆጥሮ መሪነቱን ወደ ሁለት አስፍቷል። ኦኪኪ በአመቱ 12ኛ የሊግ ግቡን ማስቆጠርም ችሏል።
የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀረው አዲስ እና ባዬ በአንድ ሁለት ተቀባብለው አዲስ በቀጥታ ወደ ግብ የመታትን ኳስ ዳንኤል አጄይ በቀላሉ ይዞበታል።
በሁለተኛው አጋማሽ የጫወታ ክፍለ ጊዜ ሲዳማ ቡናዎች መሻሻልን አሳይተው የገቡበት ቢሆንም የኋላ መስመራቸው በቀላሉ ተጋላጭ መሆን ዋጋ አስከፍሏቸዋል። 50ኛው ደቂቃ ላይ ባዬ ገዛኸኝ በግል ብቃቱ ከመሀል ሜዳ እየገፋ ገብቶ ራሱ ማግባት የሚችልበትን እድል ከግብ ጠባቂው አጄይ ጋር ተገናኝቶ ወደ ኃላ መልሶ ለአዲስ ሰጥቶት አዲስ ወደ ግብ ቢመታም ተከላካዩ አዳማ ሲሶኮ ተንሸራቶ ያወጣበት ኳስ ወደ ጨዋታው ለመመለስ የሚያግዛቸው አጋጣሚ ነበር። ከዚህ አጋጣሚ በኋላ ባለሜዳዎቹ ጎል ለማስቆጠር ተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርጉም እንደነበራቸው የጨዋታ ብልጫ ግን ግብ ማስቆጠር ተስኗቸው ታይቷል፡፡
በ63ኛው ደቂቃ ሳምሶን ቆልቻ ከመስመር ወደ ሳጥን ሰብሮ በመግባት ለኦኪኪ ያቀበለውን ኳስ ኦኪኪ በነፃ አቋቋም ለነበረው ኄኖክ ኢሳይያስ አቀብሎት ኄኖክ ወደ ግብነት በመለወጥ የእንግዳዎቹን መሪነት ወደ 3-0 ከፍ አድርጎታል። የግቧን መቆጠር ተከትሎም የሲዳማ ቡና ደጋፊዎች በክለቡ አመራሮችን ቁሳቁስ እና ድንጋዮችን በመወርወር ተቃውሞን ያሰሙ ሲሆን ጨዋታውም ለ10 ደቂቃ ያህል ተቋርጦ ቆይቶ በፀጥታ ኃይሎች አማካኝነት በመረጋጋቱ ጨዋታው ቀጥሏል።
ሲዳማ ቡናዎች እጅግ የበላይ በሆኑበት የመጨረሻወቹ ደቂቃዎች ላይ በርካታ አጋጣሚን አግኝተው መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ 77ኛው ደቂቃ ላይ ግን ሀብታሙ ገዛኸኝ ከመስመር ያሻገራትን ኳስ በጨዋታው ተቀይሮ ከገባበት ሰአት ጀምሮ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ይገዙ ቦጋለ አስቆጥሮ የግብ ልዩነቱን አጥብቧል። ሲዳማ ቡና ተጨማሪ አጋጣሚን በዮሴፍ ዮሀንስ እና ባዬ ገዛኸኝ አማካኝነት ቢያገኙም መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ ጨዋታውም በጅማ አባጅፋር 3 ለ 1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ጅማ አባጅፋር ድሉን ተከትሎ ለረጅም ጊዜያት ሊጉን ሲመራ የቆየው ደደቢትን በመብለጥ በ35 ነጥቦች አናት ላይ መቀመጥ ችሏል።
የአሰልጣኞች አስተያየት
ዘርዓይ ሙሉ – ሲዳማ ቡና
ተከላካዮቼ ጥሩ አልነበሩም። አጥቂው (ኦኪኪ) ደግሞ በጣም ጉልበት ያለው ተጫዋች ነው። ኳሱን መቆጣጠር ባለመቻላችን ግቦች ተቆጥሮብናል። ከእረፍት በኋሃ እንቅስቃሴያቸውን ለማስቆም ብንጥርም በተቆጠሩብን ጎሎች በስነ ልቦናው እንድንወርድ አድርጎናል። እኛ ጋር በጉልበት ተጋጣሚውን ተቋቁሞ የሚጫወት አልነበረም።
ገብረመድህን ኃይሌ – ጅማ አባጅፋር
ጨዋታው በአጠቃላይ ለኛ ጥሩ ነው። ከሜዳችን ውጭ አሸንፈን በመውጣታችን ሊጉን የመምራት ዕድል አግኝተናል። ያለውንም አጋጣሚ ተጠቅመን አሸንፈን መውጣት ችለናል። ከእረፍት በኃላ ግን ጥሩ አልነበርንም፤ ተረጋግተን መጫወት አልቻልንም። እነሱ የተሻሉ ነበሩ፤ እኛ ደግሞ መሪነታችንን ለማስጠበቅ ጥረት አድርገናል፡፡