በ20ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተጠበቂው መርሀ ግብር ሀዋሳ ከተማ አዳማ ከተማን አስተናግዶ በመጀመሪያው አጋማሽ ባስቆጠራቸው ግቦች በመታገዝ 2-1 አሸንፎ ወጥቷል፡፡ አንድ ቀይ ካርድ እና አላስፈላጊ ጥፋቶች በተስተናገዱበት ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ ሁለተኛው የውድድር አጋማሽ ባደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች ላይ ያለመሸነፍ ጉዞውን አስቀጥሏል፡፡
ሀዋሳ ከተማ በ19ኛ ሳምንት ሶዶ ላይ ከወላይታ ድቻ ጋር አቻ ከተለያየው ቡድን ላይ የሶስት ተጫዋቾችን ለውጥ አድርጓል፡፡ ድቻ ላይ ግብ ያስቆጠረው አስጨናቂ ሉቃስ በተጠባባቂነት ሲጀምር ለኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን የተመረጡት መሳይ ጳውሎስ እና እስራኤል እሸቱ ከጨዋታው ውጪ በመሆናቸው በምትካቸው ታፈሰ ሰለሞን፣ ጋብሬኤል አህመድ እና ዳንኤል ደርቤ ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል፡፡ በአዳማ ከተማ በኩል የአጥቂው ዳዋ ሆቴሳ በጉልበት ጉዳት አለመኖር ቡድኑን በፊት መስመር ላይ አስፈሪነቱን እንዲቀንስ አድርጎታል፡፡ አዳማ ባሳለፍነው ሳምንት በመከላከያን 1-0 ካሸነፈው ቡድኑ ላይ ኢስማኤል ሳንጋሪ፣ ተስፋዬ በቀለ፣ ዳዋን በደሳለኝ ደባሽ፣ አንዳርጋቸው ይላቅ እና አዲስ ህንፃ ተተክተዋል፡፡
ሀዋሳ ከተማዎች የጨዋታ ብልጫን ገና ከጅማሮው የወሰዱ ሲሆን የመጀመሪያ ሙከራቸውን ወደ ግብነት በመቀየር መሪነቱን መጨበጥ ችለዋል፡፡ በአራተኛው ደቂቃ ፍሬው ሰለሞን ላይ የቀድሞ ክለቡን የገጠመው ተከላካዩ ሙጂብ ቃሲም የሰራውን ጥፋት ተከትሎ ከ18 ሜትር ርቀት ላይ የተሰጠውን ቅጣት ምት አዲስአለም ተስፋዬ በቀጥታ በመምታት ግሩም ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡
ከግቡ መቆጠር በኃላ በነበሩት 10 ደቂቃዎችም ያልተረጋጋው የአዳማ ከተማ የመሃል ክፍል በሀዋሳ አማካዮች በቀላሉ ብልጫ ተወስዶበታል፡፡ በዚህም የተነሳ በአጫጭር ቅብብሎች እና በቀጥታ ከመሃል ሜዳ በሚጣሉ ኳሶች የግብ እድሎችን ሲፈጥሩ ተስተውሏል፡፡ ጋብርኤል አህመድ በ14ኛው ደቂቃ ከርቀት የሞከረውን ኳስ የአዳማው ግብ ጠባቂ ጃኮብ ፔንዝ አውጥቶበታል፡፡ በ18ኛው ደቂቃ የሀዋሳው ግብ ጠባቂ ሜንሳ ሶሆሆ ከግብ ክልሉ በአግባቡ ያላራቀውን ኳስ ከነዓን ማርክነህ አግኝቶ ለበረከት ደስታ ቢያቀብልም የቀኝ መስመር አማካዩ በሳጥኑ ውስጥ ሆኖ የሞከረውና ሜንሳህ የያዘበት በዳማ በኩል የሚጠቀስ ነበር። ሀዋሳዎች በአደጋ ክልሉ ውስጥ ለሜንሳ ኳስን መመስረቱን እንዲጀምር በሚያደርጉበት ወቅት የመቀባበያ አማራጮችን መፍጠር እየተሳናቸው የአዳማ አጥቂ ክፍል ግብ ጠባቂው ላይ ጫናን እንዲያሳድርም በር ከፍቶ ታይቷል፡፡ ሆኖም በ26ኛው ደቂቃ ደስታ ዮሃንስ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ነፃ አቋቋም ላይ የተገኘው ዳዊት በግንባሩ በመግጨት የሀዋሳን ሁለተኛ ግብ አስገኝቷል፡፡ የቀድሞ የደደቢት አጥቂ ዳዊት ግብ ሲያስቆጥር ከሁለተኛው ሳምንት በኃላ ለመጀመሪያ ግዜ ነው፡፡
አዳማው አምበል ሱሌይማን መሃመድ በጉዳት በ30ኛው ደቂቃ ከሜዳ በጫላ ተሺታ ተቀይሮ ከወጣ በኃላ ሱሌማን ሰሚድ ወደ ግራ መስመር ተከላካይነት ተሸጋሽጓል፡፡ ጨዋታው ከግቦቹ መቆጠር በኃላ በአዳማ ከተማ ተጫዋቾች አላስፈላጊ የሃይል አጨዋወቶች እና ጥፋቶች ሲቋረጥ ተስተውሏል፡፡
ከእረፍት መልስ አዳማዎች ኤፍሬምን በደሳለኝ ምትክ ቀይረው በማስገባት በተሻለ የኳስ ቁጥጥር የነበራቸው ሲሆን የግብ እድሎችን በመፍጠር ረገድ ግን ደካማ ነበሩ፡፡ ሀዋሳዎች በበኩላቸው የሁለተኛው አጋማሽ የኳስ ቁጥጥር ብልጫን ለተጋጣሚያቸው ከመስጠታቸው ባሻገር በግራ መስመር በኩል የሚመጡ የአዳማ ጥቃቶችን ለመከላካል ሲቸገሩ ተስተውሏል፡፡ ሁለቱም ቡድኖች በ63ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ማስቆጠር የሚችሉባቸውን እድሎች ከመገኘታቸው በፊት ግብ ጠበቂዎቻቸው ኳስን አውጥተዋል፡፡
በ76ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው ሲሳይ ቶሊ አምስት ደቂቃዎች ብቻ በሜዳ ላይ ቆይቶ አዲስአለምን ኳስ በሌለበት በመማታቱ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል፡፡ ከሁለት ደቂቃዎች በኃላ ደግሞ የአየር ላይ ኳስ ለማውጣት ጥረት ሲያደርግ የነበረው ጃኮ ሲወድቅ በደረሰበት ጉዳት በአምቡላንስ ወደ ሆስፒታል ተወስዷል፡፡ የጆኮ ጉዳትን ተከትሎም ሶስት ቅያሪዎችን አድርጎ ለጨረሰው አዳማ ተከላካዩ ሙጂብ ግብ ጠባቂ ሆኖ ቀሪ ደቂቃዎችን ጨርሷል፡፡ የግብ ጠባቂ ለውጡን ለመጠቀም የሞከሩት ሀዋሳዋች የጠሩ የግብ እድሎችን ለመፍጠር ያደረጓቸው ሙከራዎች ስኬታማ አልነበሩም፡፡ ይልቁንም በጨዋታው መገባደጃ ላይ የሀዋሳ ተጫዋቾች በራሳቸው የግብ ክልል ላይ የኳስ ተነጥቀው የተገኘውን ክፍተት ከነዓን ተጠቅሞ ግብ በማስቆጠር ጨዋታው በሀዋሳ ከተማ 2-1 አሸናፊነት ተደምድሟል፡፡
ሀዋሳ ከተማዎች በድሉ በመታገዝ በደረጃ ሰንጠረዡ በ29 ነጥቦች 7ኛ ላይ ሲቀመጡ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው አዳማ ከተማ በተመሳሳይ ነጥብ 8ኛ ላይ ተቀምጧል፡፡
የአሰልጣኞች አስተያየት
የሀዋሳ ከተማ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ
“ጨዋታው ጥሩ እና ጠንካራ ነው፡፡ በሁለታችንም በኩል ጥሩ ፉክክር ነበር፡፡ በተለይ የመጀመሪያው 45 ጨዋታውን የወሰነው ክፍል እዛ ላይ ነበር፡፡ ጥሩ ለመንቀሳቀስ ሞክረናል፡፡ ያገኘናቸውን እድሎች መጠቀማችን የበለጠ ጨዋታውን እንድንቆጣጠር ረድቶናል፡፡ ከዛ በተረፈ ግን ትንሽ ሃይል የተቀላቀለበት በመኖሩ መጫወት የፈለግነውን ያህል ተንቀሳቅሰናል ለማለት ይከብደኛል፡፡”
የአዳማ ከተማ አሰልጣኝ ተገኔ ነጋሽ
“መጀመሪያ ላይ በነበረው እንቅስቃሴ እነሱ ኳስ በመነካካት በልጠውናል፡፡ ዞሮ ዞሮ ይህን አስተካክለን በገባን ሰዓት ደግሞ ተጫዋች ወጥቶብናል፡፡ ተጫዋቹ ባይወጣብን ደግሞ የተሻለ ነገር ነበረን፡፡ የማጥቃቱን ነገር ወደ እኛ ዞሮ ነበር፡፡ በመጨረሻም የበረኛችን መውጣት ቀኑን አስቸጋሪ አድርጎብናል፡፡ ሰው ያላወቀው አንድ ነገር በቀዮች፣ በቢጫዎች እና ጉዳቶች ምክንያት ተጫዋቾቻችን የሉም፡፡ እነዛ ልጆች ቢኖሩ ደግሞ የተሻለ ውጤት ይኖር ነበር፡፡ በቀጣይ ጨዋታዎች ሲለሚለሱ የሊጉ መሪዎች የትም አያመልጡንም እንደርስባቸዋለን፡፡”