ዳዊት ፍቃዱ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ባለፉት 10 አመታት በጉልህ ከሚጠቀሱ ጎል አስቆጣሪዎች ተርታ የሚመደብ አጥቂ ነው። ሆኖም ያለፉትን ሁለት አመታት በተለያዩ ምክንያቶች ከተለመደው ጎል አስቆጣሪነቱ እየራቀ ይገኛል። ትላንት ሀዋሳ አዳማ ከተማን 2 – 1 በረታበት ጨዋታ ላይ ሁለተኛውን ጎል ማስቆጠር የቻለው ዳዊት ከህዳር ወር በኋላ የመጀመርያ ጎሉ ሆኖ ተመዝግቧል። ዳዊት ጎሎች ከማስቆጠር የራቀበትን ምክንያት እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየቱን ሰጥቷል።
በህዳር ወር ሐት-ትሪክ ከሰራህ በኋላ ከጎል ርቀህ ቆይተሀል…
ከብዙ ችግሮች በኋላ ነበር ወደ ሀዋሳ የመጣሁት። እዚም ከቡድኑ ጋር አጀማመሬ ጥሩ ሆኖ በአንድ ጨዋታ ሦስት ጎል አስቆጥሬያለው ። በወቅቱ በጣም ደስተኛ ነበርኩ ። በቀጣይም እንዲሁ ጎል እያስቆጠርኩ ቡድኑን ለማገዝ አስቤ ነበር ። ሆኖም በተደራራቢ ጉዳቶች እንዳሰብኩት ጎል ሳላስቆጥር ከጎል ርቄ ነበር። በየጨዋታው ደግሞ ጎል ለማስቆጠር ብዙ ስታስብ ፣ ከጎል ስትርቅ ደግሞ ከልክ ያለፈ መጨናነቅ ውስጥ ትገባለህ ። አሁን በሙሉ ጤንነት ላይ ስለምገኝ ያው ትላንት ጎል አስቆጥሬ ወደ ጎል ማስቆጠሩ ተመልሻለው።
ከጉዳት ባሻገር ሌሎች ምክንያቶች ይኖራሉ?
በብዛት አሁን ቡድኑ ውስጥ ያለነው ተጨዋቾች ጎል የማስቆጠር ከፍተኛ ጉጉት አለ። ወደ ጎልም በብዛት እንደርሳለን ፤ የቡድኑ አጨዋወትም በጣም ለጎል የቀረበ ነው። ግን ጎል ለማስቆጠር ከፍተኛ ጉጉት በመኖሩ ምክንያት ጎል እየሳትን መገኘታችን የቡድኑ ችግር ሆኗል። የእኔ ብቻ አይደለም ችግሩ። አሁን ይህን ማስተካከል እንዳለብን ተነጋግረናል። እኔም ራሴን አስተካክዬ ጎሎች ላይ ትኩረት አድርጌ በርካታ ጎል ለማስቆጠር እሞክራለው።
አምናም በውድድር በአመቱ 1 ጎል ብቻ ነው ያስቆጠርከው። በሀዋሳም ጎል ለማስቆጠር እየተቸገርክ ትገኛለህ። ከሜዳ ውጭ ባለው ህይወትህ ያልተረጋጋህበት ነገር ይኖር ይሆን?
በፍፁም የለም። በቤተሰብ ህይወቴ በጣም የተረጋጋ ደስተኛ ህይወት ነው እየመራው ያለሁት ። ቅድም እንደነገርኩህ አምና በአንዳንድ ችግሮች ምክንያት ጎሎችን ማስቆጠር አልቻልኩም ። ዘንድሮ ደግሞ ሊጉ እንደተጀመረ ሦስት ጎል አስቆጥሬ አለው። ከዛ በኋላ ከቡድኑ ጋር እንዳሰብኩት ማገልገል አልቻልኩም። ጎል ለረጅም ጊዜ አለማስቆጠሬ ደግሞ ከፍተኛ ተጽእኖ አድርጎብኝ እንጂ ከሜዳ ውጭ ሰላማዊና የተረጋጋ ህይወት ነው ያለኝ ።
ትላንት አዳማ ላይ ሁለተኛውን ጎል ካስቆጠርክ በኋላ ወደ ደጋፊው በመሄድ እጅ ነስተሀል። ምክንያቱ ምን ይሆን?
መጀመርያ ላይ ሀዋሳ ስመጣ አስቤ የነበረው ነገር ጎል እያስቆጠርኩ ቡድኑን በማገዝ ለማገልገል ነበር። ያ አልሆነም ፤ ከመጀመርያ ጎሌ በኋላ አልተሳካም ፤ የማገኘውንም አጋጣሚ አመክን ነበር። በዚህ ምክንያት በጣም ከልክ በላይ ተጨናንቄ ነበር። በዚህ ሁሉ አስቸጋሪ ጊዜ ውስጥ ደጋፊው እኔን ታግሶ ፣ ሳይጫነኝ እና ሳይቃወመኝ ይህን ያህል ጊዜ ጠብቀውኝ ጎል በማስቆጠሬ ለእነሱ ያለኝን ክብር ለመግለፅ ብዬ ነው ይህን ያደረኩት ።