የብሄራዊ ሊግ ሩብ ፍፃሜ ጨዋታዎች…

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሊግ ሩብ ፍፃሜ ጨዋታዎች ነገ ይደረጋሉ፡፡ ሶከር ኢትዮጵያ ጨዋታዎችን በጨረፍታ ለመዳሰስ ትሞክራለች

ጅማ ከነማ ከ ሆሳእና ከነማ

ጅማ ከነማ የምድብ 3 መሪ ሆኖ አጠናቋል፡፡ የተቀራረበ አቋም ካላቸው ክለቦች ልቆ ወደ ሩብ ፍፃሜው ለማለፍ ሼር ኢትዮጵያ ላይ የመጨረሻ ደቂቃ ግብ አስፈልጎት ነበር፡፡ ክለቡ አሰልጣኙ ፋንታዬ አባተን በቅጣት የሚያጣ በመሆኑ ጨዋታውን በረዳት አሰልጣኙ እየተመራ ወደ ሜዳ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ሆሳእና ከነማ የሞት ምድብ የተባለለትን ምድብ 4 ማንም ባልገመተው መልኩ ቀድሞ ወደ ሩብ ፍፃሜው ማለፉን አረጋግጧል፡፡ ሆሳእና በመጨረሻው ጨዋታ ተሸንፎ በ2ኝነት ቢያልፍም አሰልጣኙ በርካታ ተጫዋቾችን በወሎ ኮምቦልቻው ጨዋታ በማሳረፋቸው በተሻለ ጉልበት ጅማ ከነማን ይገጥማሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ጨዋታው ነገ በ2፡00 በድሬዳዋ ስታድየም ይደረጋል

 

አውስኮድ ከ ሃላባ ከነማ

አውስኮድ ጠንካራ ክለቦች ካሉበት ምድብ 4 በ1ኝነት ሩብ ፍፃሜውን ሲቀላቀል ሃላባ ከነማ ከምድብ 3 2ኛ ሆኖ የመጨረሻዎቹን ቡድኖች ተቀላቅሏል፡፡

በውድድሩ ከተሳተፉት ቡድኖች የተሻለ የተከላካይ መስመር ጥንካሬ እንደያዘ የተመሰከረለትና በ5 ጨዋታዎች 2 ግብ ብቻ ያስተናገደው አውስኮድ ድሬዳዋን ባደመቁት ደጋፊዎቹ ታግዞ የነገውን ጨዋታ ያደርጋል፡፡ በተመሳሳይ ሃላባ ከነማን ለመደገፍ ወደ ትላንት ድሬዳዋ ያመሩት የሃላባ ደጋፊዎች ሲደመሩ የነገው ጨዋታ የደመቀ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፤፤

ጨዋታው ነገ 04፡00 በድሬዳዋ ስታድየም ይደረጋል፡

 

ፌዴራል ፖሊስ ከ ጅማ አባቡና

ጅማ አባ ቡና ከሁሉም ክለቦች ቀድሞ ወደ ሩብ ፍፃሜ ያለፈ ክለብ ነው፡፡ ፌዴራል ፖሊስ ደግሞ ከምድብ 1 ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ያለፈ ክለብ ነው፡፡ ጅማ አባ ቡና በማጥቃት ፌዴል ፖሊስ በመከላከል ረገድ ጠንካራ ቡድኖች መሆናቸውን አሳይተዋል፡፡

ጅማ አባ ቡና ተከላካዩ ምንያህል ወንድሙን በቅጣት የማያሰልፈው ጅማ አባ ቡና የጅማን የእግርኳስ ታሪክ ለመቀየር አልሞ ወደ ሜዳ ይገባል፡፡ ታሪካዊው ፌዴራል ፖሊስም የቀድሞ ስሙን ለመመለስ በማለም አባ ቡናን ይገጥማል፡፡

ጨዋታው ነገ 08፡00 በድሬዳዋ ስታድየም ይደረጋል፡፡

 

ድሬዳዋ ከነማ ከ አዲስ አበባ ከነማ

ድሬዳዋ ከነማ ምድብ 1ን በቀዳሚነት ፤ አዲስ አበባ ከነማ ደግሞ ምድብ 2ን በሁለተኝነትሩብ ፍፃሜውን ተቀላቅለዋል፡፡

በብቸኛዋ ሴት አሰልጣኝ መሰረት ማኒ የሚመራው ድሬዳዋ በደጋፊዎቹ እና በለመደው ሜዳ ታግዞ የሚጫወት ከመሆኑ በተጨማሪ በርካታ ግቦችን የሚያስቆጥር እና በቀላሉ ግብ የማይቆጠርበት ቡድን በመሆኑ ወደ ግማሽ ፍፃሜው የማለፍ ግምት ተሰጥቶታል፡፡

አዲስ አበባ ከነማ ደግሞ ከጨዋታ ጨዋታ መሻሻሎችን እያሳየ እንደመሆኑ በቀላሉ ለድሬዳዋ ከነማ እጅ አይሰጥም ተብሎ ይጠበቃል፡፡ አምና ከሱሉልታ ከነማ ጋር ወደ ፕሪሚየር ሊግ ለመግባት በእጅጉ ቀርበው የነበሩት አሰልጣኝ ታደሰ የብሄራዊ ሊግ ልምዳቸውን ተጠቅመው አዲስ አበባ ከነማን ወደተሻለ ደረጃ ያደርሱታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ጨዋታው ነገ 10፡00 በድሬዳዋ ስታድየም ይደረጋል፡፡


 

[table id=30 /]

 

 

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *