በ2019 በኒጀር አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የቶታል የአፍሪካ ከ20 አመት በታች ዋንጫ የመጀመርያ የማጣርያ ጨዋታውን በአዲስ አበባ ስታድየም ባሳለፍነው ሳምንት ያደረገው የኢትዮዽያ ከ20 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን በቡሩንዲ 2 – 0 በሆነ ውጤት በመሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር የማለፍ እድሉን አጣብቅኝ ውስጥ የከተተ መሆኑ ይታወቃል።
በአሰልጣኝ አጥናፉ አለሙ የሚመራው ብሔራዊ ቡድኑ ለመልሱ ጨዋታ ከሳምንቱ መጀመርያ አንስቶ ሲዘጋጅ የቆየ ሲሆን 17 ተጨዋች ብቻ በመያዝ ወደ በትላንትናው እለት ወደ ስፍራው አቅንቷል። ከቡድኑ ጋር አብረው ይጓዛሉ ተብለው ይጠበቁ የነበሩን ሁለቱ ተከላካዮች ሳሙኤል ተስፋዬ እና እዮብ አለማየሁም ከቡድኑ ጋር ያልተጓዙ ተጫዋቾች ናቸው። ቡድኑ በመጀመርያው ጨዋታ ላይ ከነበሩ ተጨዋቾች መካከል በርከት ያሉ ተጨዋቾችን በመቀነስ ተከላካዩ ይትባረክ ሀብታሙ እና አጥቂው እስራኤል እሸቱን ብቻ በማካተት ወደ ቡሩንዲ ተጉዟል።
ቡድኑ ዛሬ ረፍድ ላይ ከዋናው ከተማ ወጣ ወዳለው ኒጎዚ ከተማ በሚጫወትበት ሰው ሰራሽ ሜዳ ላይ የመጨረሻ ልምምዱ ሰርቷል። ጨዋታው ነገ 10:00 ላይ የሚካሄድ ሲሆን የጅቡቲ ዳኞች ጨዋታውን የሚመሩት ይሆናል።