ወልዲያ ዋና አሰልጣኙ ዘማርያም ወ/ጊዮርጊስን በቅጣት ፣ ም/አሰልጣኙ ኃይማኖት ግርማ ደግሞ በመልቀቃቸው ምክንያት በ20ኛው ሳምንት ቡድኑ ከመቐለ ከተማ ጋር ባደረገው ጨዋታ ያለ አሰልጣኝ የመጫወት ግዴታ ውስጥ ገብቶ 0-0 በሆነ አቻ ውጤት ጨዋታውን ማጠናቀቁ ይታወቃል። ይህን ተከትሎም የክለቡ አመራሮች ያለፈውን አንድ አመት በም/አሰልጣኝነት ክለቡን ያገለገሉት ኃይማኖት ግርማን ዳግመኛ ጠርቶ በማነጋገር ከስምምነት በመድረሳቸው ቡድኑን በዋና አሰልጣኝነት ይዘው እንዲቀጥሉ ከውሳኔ ደርሰዋል። የአንድ አመት ቅጣት የተላለፈባቸው አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ ከክለቡ ጋር የሚኖራቸው ጉዳይም በቀጣይ ጊዜያት የሚታወቅ ይሆናል።
በዚህም መሰረት ያለፉትን ቀናት ቡድኑን ተረክበው ልምምድ እያሰሩ የሚገኙት የቀድሞው የሐረር ሲቲ እና ድሬዳዋ ከተማ አሰልጣኝ ኃይማኖት ግርማ ነገ 08:00 ላይ በሰበታ ከተማ ሜዳ ከሲዳማ ቡና ጋር በሚኖረው የ21ኛው ሳምንት ጨዋታ ላይ ቡድኑን በዋና አሰልጣኝነት በመያዝ የመጀመርያ ጨዋታቸውን የሚያደርጉ ይሆናል ።