ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | የሚያዚያ 14 21ኛ ሳምንት ጨዋታዎች

ትላንት በአንድ ጨዋታ የጀመረው የሊጉ 21ኛ ሳምንት ዛሬ አምስት ጨዋታዎች ይደረጉበታል። በሰበታ ፣ ሀዋሳ ፣ ጅማ እና አዳማ ላይ የሚከናወኑትን ጨዋታዎች በዚህ መልኩ ዳሰናቸዋል።

ወልዲያ ከ ሲዳማ ቡና

በፕሪምየር ሊጉ የመጨረሻ ጨዋታዎቻቸው በቂ ነጥቦችን መሰብሰብ የተሳናቸው ሁለቱ ክለቦች እርስ በእርስ መገናኘታቸው ለሁለቱም መልካም አጋጣሚ ይመስላል። በሜዳው ጨዋታዎችን እንዳያደርግ የተላለፈበትን ቅጣት ዛሬ የሚጀምረው ወልዲያ ወደ ወራጅ ቀጠናው ቢቀርብም ራሱን ከስጋት ነፃ ለማድረግ ግን ዕድሉ አለው። ቡድኑ ከዚህ ጨዋታ ሶስት ነጥብ ማግኘት ከቻለም ወደ 10ኛነት ከፍ ያማለት ዕድል ሊፈጥር ይችላል። ከተጋጣሚው በአንድ ነጥብ እና በአንድ ደረጃ ብቻ የሚሻለው ሲዳማ ቡናም ተመሳሳይ ዕቅድ ኖሮት ነው ወደ ሜዳ የሚገባው። በመሆኑም ሰበታ ላይ በ8፡00 የሚጀምረው ጨዋታው ካሁኑ ራሳቸውን በሊጉ ለማደላደል ለቡድኖቹ እኩል ዋጋ ያለው በመሆኑ ጠንካራ ፉክክር እንደሚስተናገድበት ይጠበቃል።

የወልዲያን የቡድን ዜና ማግኘት ባንችልም ቡድኑ በዋና አሰልጣኝነት በሾማቸው አሰልጣኝ ኃይማኖት ግርማ እየተመራ ወደ ሜዳ እንደሚገባ ይጠበቃል። በሲዳማ ቡና በኩል ደግሞ ምንም የጉዳት ዜና የሌለ ሲሆን ግሩም አሰፋ ከጉዳት እንደሚመለስ ይጠበቃል።

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተቀዛቀዘ የመጣው የሲዳማ ቡና የመስመር አጥቂዎች ወደ ውስጥ እየጠበበ የሚመጣ የማጥቃት ዕቅድ አሁንም የቡድኑ የመጀመሪያ ምርጫ ሆኖ ቀጥሏል። በዚህም ጨዋታ የቡድኑ የአማካይ ክፍል ለአብዱለጢፍ መሀመድ እና አዲስ ግዳይ የመስመር እንቅስቃሴ ኳሶችን ከማድረስ ባለፈ ቀጥተኛ ጥቃትን መሰንዘር ካልጀመረ ለመከላከል ቅድሚያ ሊሰጥ ከሚችለው ወልዲያ ጠንካራ ፉክክር የሚጠብቀው ይሆናል። በዳንኤል ደምሴ ልዩ ብቃት በመታገዝ ከተቃራኒ የአማካይ ክፍል ተነስተው ወደ ፍፁም ቅጣት ክልላቸው የሚመጡ ኳሶችን ሲከላከሉ የሚታዩት ወልዲያዎችም በዛሬው ጨዋታ ትኩረታቸው በመሀል እና በመስመር ተከላካዮቻቸው መሀከል በሚገኙ ክፍተቶች የግብ ዕድሎች እንዳይፈጠሩባቸው በማድረጉ ላይ ይሆናል። ከዚህ ውጪ ቡድኑ በማጥቃት ሂደት ወደ ፊት በሚሄድባቸው አጋጣሚዎች በረጃጅም ኳሶች አንዷለም ንጉሴን ለማግኘት እነሚጥር ይታሰባል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ቡድኖቹ 5 ጊዜ ተገናኝተው ወልዲያ 1 ድል ሲያስመዘግብ ሲዳማ ቡና ሁለት ጊዜ አሸንፏል። በሁለት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ወልዲያ 5 ፣ ሲዳማ 6 ጎሎች አስቆጥረዋል።

– ወልዲያ ደደቢትን ከረታበት ጨዋታ ወዲህ 6 ተከታታይ ጨዋታዎችን ማሸነፍ አልቻለም። በተመሳሳይ ሲዳማ ቡናም ካለፉት 8 ጨዋታዎች ድል የቀናው ወልዋሎን በረታበት ጨዋታ ብቻ ነው።

ዳኛ

– ጨዋታውን የሚመራው ኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ ነው።


Hulusport.com | ሊንኩን ተጭነው ይወራረዱ


ሀዋሳ ከተማ ከ መከላከያ

የ20ኛውን ሳምንት በአሸናፊነት ከተወጡ ክለቦች መሀከል የሚካተቱት ሀዋሳ ከተማ እና መከላከያን እርስ በእርስ የሚያገናኘው ይህ ጨዋታ ለሀዋሳ በዚህ አመት ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎችን የማሸነፍ የመጀመሪያ ዕድል የሚሰጠው ሲሆን ጦሩ ሶስት ነጥብ ካሳካ ደግሞ ከ8ኛው ሳምንት በኃላ ለቀይ እና አረንጓዴ ለባሾቹ ሁለተኛ ተከታታይ ድላቸው ይሆናል። 29 ነጥብ ላይ የደረሰው ሀዋሳ ከተማ አሁንም ከበላዩ ለዋንጫው እየተፎካከሩ ወዳሉት ቡድኖች በሚገባ የቀረበ ባይመስልም ይህን ጨዋታ ማሸነፍ ግን እስከ አራተኛነት ከፍ ማለት የሚያስችለው ይሆናል። በሌላ ወገን መከላከያ 10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ ከወራጅ ቀጠናው የራቀ ቢመስልም የነጥብ ልዩነቱን አስፍቶ የበልጥ ራሱን ከጫናው ለማራቅ እንደሚጫወት ይጠበቃል።

በአዳማው ጨታዋ ጉዳት የገጠማቸው የሀዋሳዎቹ ታፈሰ ሰለሞን እና ጅብሪል አህመድ ወደ ልምምድ ቢመለሱም ለዛሬው ጨዋታ የመሰለፍ ያለመሰለፋቸው ጉዳይ አለየለትም፡፡ በተጨማርም መሳይ ፓውሎስ ፣ እስራኤል እሸቱ ፣ ፀጋአብ ዮሴፍ እና ዮሀንስ ሴጌቦ ለኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን በመመረጣቸው ምክንያት የማይገኙ ይሆናሉ፡፡ በመከላከያ በኩል ሽመልስ ተገኝ ቅጣት ላይ ሲሆን ከቴዎድሮስ በቀለ በተጨማሪ በቅርቡ ከጉዳት ተመልሶ እየተሰለፈ የነበረው አዲሱ ተስፋዬም ዳግም መጠነኛ ጉዳት እንደገጠመው ተሰምቷል።

ምንም እንኳን ሁለቱም በተመሳሳይ በአጫጭር ቅብብሎች ወደ ተጋጣሚያቸው የሜዳ ክልል ለመግባት ጥረት የሚያደርጉ መሆናቸው ቢያመሳስላቸውም ሀዋሳ ከተማ በዚህ አቀራረብ የተሻለ ልምድ አለው። ጨዋታው ሜዳቸው ላይ እንደመካሄዱም ሀዋሳዎች የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን በመውሰድ ብቻም ሳይሆን በተመጣጠነ የተጨዋቾች ርቀት የተሻለ የሜዳ ስፋት አጠቃቀም እና የተከላካይ መስመር ሰንጣቂ የሆኑ ኳሶችን በማሳካቱ ረገድ የበላይ ለመሆን ዕድሉ አላቸው። ይህን ማድረግ ከቻሉም ውጤት ማግኘት ላይከብዳቸው ይችላል። መሰል ውህደት ላይ ለመድረስ ብዙ የሚቀረው የአሰልጣኝ ስዩም ከበደ ቡድን በአርባምንጩ ጨዋታ ላይ ካሳየው የተሻሻለ የመስመር ተከላካዮች የማጥቃት ተሳትፎ ባለፈ የአማካይ ክፍል ውህደቱ የመጨረሻ ዕድሎችን ከመፍጠር አንፃርም ሆነ በአስፈላጊ የሜዳ ክፍል ላይ የተሳኩ ቅብብሎችን በማድረጉ ረገድ አሁንም ብዙ ይቀረዋል። ሆኖም የምንይሉ ወንድሙ እና ፍፁም ገ/ማርያም አዲስ ጥምረት በሀዋሳ የመከላከል ቀጠና ውስጥ በርካታ ዕድሎችን ባያገኝ እንኳን ከተወሰኑ አጋጣሚዎች አደጋ የመፍጠር ዕድል እንዳለው የአርባምንጩ ጨዋታ ማሳያ ይሆነናል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ሁለቱ ቡድኖች 25 ጊዜ ተገናኝተው ሀዋሳ ከተማ 11 ጊዜ በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን መከላከያ 6 ጊዜ አሸንፏል። በቀሪዎቹ 8 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ሀዋሳ 28 ፣ መከላከያ 20 ጎሎችን አስቆጥረዋል።

– ሀዋሳ ላይ 13 ጊዜ ተጫውተው 7 ጊዜ ሀዋሳ ሲያሸንፍ 5 ጊዜ አቻ ተለያይተው በአንድ አጋጣሚ ብቻ መከላከያ አሸንፏል።

ዳኛ

– ፌደራል ዳኛ ተካልኝ ለማ የሀዋሳውን ጨዋታ ለመምራት የተመደበው አልቢትር ነው።


Hulusport.com | ሊንኩን ተጭነው ይወራረዱ


አዳማ ከተማ ከ ድሬደዋ ከተማ

በወላይታ ድቻ የአፍሪካ መድረክ ተሳትፎ ምክንያት አንድ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ያላቸው ሁለቱ ቡድኖች በተለያየ ፅንፍ ላይ ቢገኙም የውጤት ወጣ ገባነት ይስተዋልባቸዋል። ለዋንጫ በሚያደርገው ፉክክር ከዚህ በላይ የተሻለ ደረጃ እና የነጥብ ብዛት ላይ የመድረስ ዕድል የነበረው አዳማ በተለይ ከሜዳው ውጪ ነጥብ ይዞ መመለስ ያልቻለባቸው ጨዋታዎች ወደ ኃላ እየጎተቱት ይገኛሉ። ድሬድዋ ከተማም ቢሆን ከመጨረሻዎቹ ሀለት ጨዋታዎች አራት ነጥቦችን ያሳካ እንጂ እንደተጋጣሚው ሁሉ ከሜዳው ሲወጣ ውጤት እየቀናው ባለመሆኑ ከወራጅ ቀጠናው ራሱን ማውጣት አልቻለም። የዛሬው ተጋጣሚ የሜዳ ላይ ሪከርድ ጠንካራነትም ለድሬ ትልቅ ፈተና እንደሚሆን ሲጠበቅ ከዋነኛ የዋንጫ ተፎካካሪዎቹ መሀከል ወደ ታች የተንሸራተተው አዳማም ከዚህ ጨዋታ ሙሉ ሶስት ነጥብ የማግኘት ግዴታ ውስጥ የገባ ይመስላል።

ረጅም ጊዜ ጉዳት ላይ የነበሩትን የአዳማዎቹ ሱራፌል ዳኛቸው እና ሚካኤል ጆርጅ ወደ ልምምድ የተመለሱ ሲሆን ዳዋ ሆቴሳም ለጨዋታው ብቁ እንደሆነ ተነግሯል፡፡ በተጨማሪም በሀዋሳው ጨዋታ ተቀይሮ ገብቶ አዲስ አለም ተስፋዬ ላይ በሰራው ጥፋት ከ6 ደቂቃዎች በኃላ በቀይ የወጣው ሲሳይ ቶሊም በቅጣት የማይኖር ይሆናል፡፡ በሌላ በኩል የድሬደዋ ከተማዎቹ ኩዋሜ አትራም ፣ ዘነበ ከበደ እና ዬሴፍ ዳሙዬ ጉዳት ላይ ሲገኙ ሱራፌል ዳንኤል ወደ ሜዳ እንደምመለስ ይጠበቃል።

በአማካይ ክፍል ተሰላፊዎቹ ጥንካሬ የማይታማው አዳማ ከተማ በዚህ ጨዋታ የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን በመውሰድም ሆነ በፈጣን የማጥቃት ሽግግር ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ በመድረሱ በኩል የበላይነትን ለማግኘት እንደማይቸገር ይታሰባል። ሆኖም ይህን ለማድረግ የተሻለ ዕድል የሚሰጠውን ከግብ ክልሉ ርቆ የሚከላከል የተከላላይ መስመር ከድሬደዋ ከተማ የሚያገኝ አይመስልም። ከአማካይ ክፍላቸው ጥሩ ሽፋን የሚያገኙት የድሬ የተከላካይ መስመር ተሰላፊዎች ከጥሩ የግብ ጠባቂያቸው ብቃት ጋር ከሁሌም አቅጣጫዎች የሚመጡ የማጥቃት ጫናዎችን ለመቋቋም ብቃቱ እንዳላቸው ከደደቢት ነጥብ በተጋሩበት ጨዋታ አሳይተዋል። ቢሆንም እጅግ ደካማ የሆነው የቡድኑ የማጥቃት ሽግግር እና የፊት መስመር ተሰላፊዎቹ የተሳሳቱ የቅብብል ውስኔዎች ዛሬም የሚደገሙ ከሆነ የአዳማን የኃላ ክፍል ሰብሮ መግባት ቀላል አይሆንላቸውም። በጥቅሉ ግን ጨዋታው ወደ ድሬደዋ የግብ ክልል ያመዘነ እና የነከንዓን ማርክነህ እና በረከት ደስታ የማጥቃት እንቅስቃሴ ከነ ኢማኑኤል ላርያ እና ሳውሪል ኦልሪሽ ጠንካራ የተከላካይ አማካይ ጥምረት ጋር የሚገናኝበት መሆኑ የአማካይ ክፍል ፍልሚያውን ተጠባቂ ያደርገዋል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ሁለቱ ክለቦች በሊጉ 13 ጊዜ ተገናኝተው አዳማ ከተማ 6 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ሲይዝ ድሬዳዋ አራቱን አሸንፏል። 3 ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። አዳማ 14፣ ድሬዳዋ 10 ጎሎችን ማስቆጠር ችለዋል።

– አዳማ ላይ 6 ጊዜ ተገናኝተው አዳማ 4 አሸንፎ በ2 ጨዋታዎች አቻ ሲለያዩ ድሬዳዋ አሸንፎ አያውቅም።

– አዳማ በሜዳው 29 ተከታታይ ጨዋታዎች ያለ ሽንፈት ሲጓዝ ድሬዳዋ ከተማ በአንፃሩ ዘንድሮ ከሜዳው ውጪ ምንም ድል አላሳካም።

ዳኛ

– ይህን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት የመምራቱ ሀላፊነት ለፌደራል ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው ተሰጥቷል።


Hulusport.com | ሊንኩን ተጭነው ይወራረዱ


ጅማ አባ ጅፋር ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ

ምንም እንኳን በተለያየ ፅንፍ የሚገኙ ቡድኖች ቢሆኑም ከጨዋታው የሚገኙት ነጥቦች ለሁለቱም እጅግ ወሳኝ ናቸው። የትናንቱን የደደቢትን ሽንፈት ተከትሎ የሊጉ ሰንጠረዥ አናት ላይ መርጋት የቻለው ጅማ አባ ጅፋር ሳምንት ሲዳማ ላይ ያገኘውን ድል ጨምሮ ሶስተኛ ጨዋታውን በተከታታይ ለማሸነፍ ይጫወታል። ይህን ማድረግ ከቻለ ሊጉን በመምራት ከመቀጠሉ ባለፈ ለሻምፒዮንነት ጉዞው ትልቅ የአሸናፊነት ስነልቦናን የሚያጎናፅፈው ይሆናል። ኢትዮ ኤሌክትሪክም ከጅማ ነጥብ ይዞ መመለስ ከቻለ እጅግ በነጥብ የተቀራረቡ ቡድኖች በሚገኙበት ወራጅ ቀጠና ውስጥ መሻሻልን የሚያሳይበት ዕድል አለው።

በሊጉ መሪ ጅማ አባ ጅፋር ቡድን ውስጥ ምንም የቅጣትም ሆነ የጉዳት ዜና የሌለ ሲሆን የኢትዮ ኤሌክትሪኩ ካሉሻ አልሀሰን ለጨዋታው መድረስ አጠራጣሪ ሆኗል።

የጨዋታው አጠቃላይ መልክ በጅማ አባ ጅፋር ከፍ ያለ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ እንዲሁም በኢትዮ ኤሌክትሪክ ወደ ግብ ጠባቂው የተጠጋ እና ክፍተትን ላለመስጠት የሚሞክር የቡድን አወቃቀር የሚገለፅ ይመስላል። በመሆኑም በኦኪኪ አፎላቢ የሚመራው የጅማ ኣባ ጅፋር የአጥቂ ክፍል በዙሪያው በኢትዮ ኤሌክትሪክ ተጨዋቾች ተከቦ በጥቂት ክፍተቶች የግብ ዕድሎችን የመፍጠር ግዴታ ውስጥ የሚገባበት ነው። ከአባ ጅፋር የአማካይ ክፍል ተሰላፊዎች የሚነሱ ተሻጋሪ ኳሶች እና ከሳጥን ውጪ በቀጥታ ወደ ግብ የሚላኩ ኳሶችም ለባለሜዳዎቹ አማራጭ የግብ ዕድል መፍጠሪያ መንገዶች ተደርገው ይወሰዳሉ። በራሱ ሜዳ ላይ ኳሶችን ካቋረጠ በኃላ ከፊቱ እስከተጋጣሚ የግብ ክልል ድረስ የሚኖረውን ሰፊ የሜዳ ክፍል አቋርጦ ወደ ማጥቃት ሂደት ውስጥ ለመግባት ሙሉ በሙሉ በአልሀሰን ካሉሻ የግል ብቃት ላይ ሲመረኮዝ የሚታየው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በበኩሉ እዚህ ሂደት ላይ ያሉበትን በርካታ ችግሮች አሻሽሎ ካልቀረበ ለፊት አጥቂዎቹ በብዛትም ሆነ በጥራት የላቁ የግብ ሙከራዎችን ለመፍጠር ሊቸገር ይችላል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ዘንድሮ በፕሪምየር ሊጉ የተገናኙበት የመጀመሪያ ዙር የ6ኛ ሳምንት ጨዋታ ያለግብ የተጠናቀቀ ነበር።

– ጅማ አባጅፋር በሶስተኛው ሳምንት በፋሲል ከተሸነፈ በኋላ ጅማ ላይ ካደረጋቸው ያለፉት 8 ጨዋታዎች 7 ጨዋታዎችን በአሸናፊነት በመወጣት በድንቅ አቋም ላይ ይገኛል።

ዳኛ

– ፌደራል ዳኛ ይርጋለም ወልደጊዮርጊስ የጅማውን ጨዋታ እንዲመራ ተመድቧል።


Hulusport.com | ሊንኩን ተጭነው ይወራረዱ


ወላይታ ድቻ ከ ፋሲል ከተማ

የጨዋታው በቅጣት ምክንያት ሰበታ ላይ መካሄድ የቀድሞው ክለባቸው ደጋፊ ፊት በተቃራኒ ሲቆሙ የሚፈጠረውን ስሜት ባያስመለክተንም ለአዲሱ የአፄዎቹ አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ልዩ ትርጉም እንደሚኖረው ግልፅ ነው። ፋሲሎች ከቅጥሩ በኃላ ሁለት ተከታታይ ድል ማስመዝገባቸው እየራቁ ይመስሉ ወደ ነበረበት የዋንጫ ፉክክር መልሷቸዋል። ይህን ጨዋታ ማሸነፍ ከቻሉም እስከ ሁለተኛነት ድረስ ከፍ የማለት ዕድል ይኖራቸዋል። ከአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ውጪ የሆነው ወላይታ ድቻም ሙሉ ትኩረቱን ወደ ሊጉ የሚመልስበት እና ከመሀለኛው የሰንጠረዥ ክፍል ወደ መሪዎቹ ለመቅረብ የሚያደርገውን ፉክክር የሚጀምርበት ወሳኝ ጨዋታ እንደሚሆን ይጠበቃል።

የረጅም ጊዜ ጉዳት የገጠመው የወላይታ ድቻው ፀጋዬ ብርንኑ እና ወደ ልምምድ ቢመለስም ብቁ እንዳልሆነ የተነገረለት እርቂሁን ተስፋዬ አሁንም ወደ ሜዳ የማይመለሱ ሲሆን አዲስ ፈራሚው ፀጋዬ ባልቻ እንዳገገመ ተሳምቷል። አይናለም ኃይለ ፣ ያሬድ ባየህ ፣ ይስሀቅ መኩሪያ እና አብዱራህማን ሙባረክ በፋሲል ከተማ በኩል ጉዳት ላይ የሚገኙ ሲሆን ራምኬል ሎክ እና አምሳሉ ጥላሁን ከቅጣት ተመልሰዋል።

ለማጥቃት የተመቹ ክፍተቶች እንደሚገኙበት የሚጠበቀው ይህ ጨዋታ በርከት ያሉ የግብ ዕድሎችን የማስተናገድ አቅም ሊኖረው ይችላል። ከኳስ ውጪ ከአምስቱ አማካዮቹ ሁለቱን የተጋጣሚ የመሀል ሜዳ ቅብብልን ከጅምሩ እንዲያቋርጡ ኃላፊነት ሲሰጥ የሚታየው ወላይታ ድቻ ኳስ በሚያገኝበት ወቅት የመስመር አማካዮቹን በመጠቀም ወደ ጃኮ አራፋት ለመድረስ የሚሞክርበት አኳኃን በፍጥነቱ ዝግ ብሎ ይታያል። ቡድኑ ኳስን ከኃላ መስርቶ ለማጥቃት ሲሞክርም ይህ ችግሩ ጎልቶ ይወጣል። የዘሬ ተጋጣሚው ለማጥቃት ራሱን ክፍት የሚያደርግ መሆኑ ይህን ደካማ ጎኑን ለማስተካከል ዕድል የሚሰጠው ቢሆንም የነአብዱልሰመድ ዓሊ እና በዛብህ መለዮ የቅብብል ውሳኔዎች ፍጥነት እና ስኬት በኄኖክ ገምቴሳ እና ያስር ሙገርዋ ከሚመራው የአፄዎቹ የመሀል ክፍል ብርቱ ፈተና ይጠብቀዋል። ጥሩ የተጨዋቾች መነሳሳትን የሚፈልገው እና በፍጥነት ላይ በተመሰረተ ጥቃት በዋነኝነት የመስመር አጥቂዎቹን ትጋት የሚጠይቀው የፋሲል ከተማ አጨዋወት በአዲሱ አሰልጣኙ ጎሎት የነበረውን የህን የቀድሞ ጥንካሬውን መልሶ እያገኘ ያለ ይመስላል። በዛሬውም ጨዋታ በመጠኑ ወደ ራሱ የሜዳ ክልል ተስቦ ከሚነጥቃቸው ኳሶች ኤርሚያስ ኃይሉ እና ሀሚስ ክዛን በመሳሰሉ አጥቂዎቹ ከድቻ የመስመር ተከላካዮች ጋር የሚገናኝባቸው አጋጣሚዎች ተጠባቂ ይሆናሉ። ከሁሉም በላይ ግን የአሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ የተጋጣሚያቸውን ተጨዋቾች የግል እና የቡድን ደካማ ጎኖችን ማወቅ ፋሲልን ተጠቃሚ እንደሚያደርገው ይታሰባል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ሁለቱ ቡድኖች ሶስት ጊዜ ተገናኝተው ፋሲል ከተማ ሁለት ጊዜ በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን ወላይታ ድቻ አንድ ጊዜ አሸንፏል። ድቻ 2 ጎል ሲያስቆጥር ፋሲል 4 ጎል ማስቆጠር ችሏል።

ዳኛ

– ኢንተርናሽናል ዳኛ ብሩክ የማነብርሀን ይህን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት ይመራዋል።