በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 21ኛ ሳምንት በሜዳው መከላከያን ያስተናገደው ሀዋሳ ከተማ የ4 – 0 ሽንፈት ሲያስተናግድ ፍፁም ገ/ማርያም በጦሩ መለያ የመጀመሪያ ሐት-ትሪኩን የሰራበት እና በደጋፊዎች ስርዓት አልበኝነት ምክንያት ሁለት ጊዜ ጨዋታው የተቋረጠበት ዕለት ሆኖ አልፏል።
ሀዋሳ ከተማ አዳማ ከተማን ካሸነፈበት የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ በጉዳት ላይ የሚገኙት ጋብሬል አህመድ እና ታፈሰ ሰለሞንን በአስጨናቂ ሉቃስ እና ያቡን ዊሊያም ሲተካ መከላከያዎች ደግሞ አርባምንጭን ከረቱበት ቡድናቸው መሀከል በአዲሱ ተስፋዬ ፣ አማኑኤል ተሾመ እና ምንይሉ ወንድሙ ምትክ ለሙሉቀን ደሳለኝ ፣ አቤል ከበደ እና በኃይሉ ግርማ የመጀመሪያ ተሰላፊነት ዕድል ሰጥተዋል።
ጨዋታው በጥቅሉ የሁለቱ አሰልጣኞችን ታክቲካዊ ብቃት እና ማራኪ እግር ኳስን የተመለከትንበት ሲሆን ሀዋሳ ከተማዎች የመሀል ሜዳ ክፍላቸው ተዳክሞ የታየበት እንዲሁም መከላከያዎች በመልሶ ማጥቃት እና በፍፁም ገ/ማርያም አስደናቂ እንቅስቃሴ ስኬታማ የሆኑበት ነበር። በሌላኛው መልኩ ደግሞ የፌደራል ዳኛ ተካልኝ ለማ አወዛጋቢ ውሳኔዎች እና በሁለት አጋጣሚዎች የተከሰቱ የደጋፊ ተቃውሞዎችን ተከትሎ በድምሩ ለ26 ደቂቃዎች የተቋረጠም ነበር።
እንደተለመደው በሜዳቸው ኳስን ይዘው በመጫወቱ ረገድ ሀይቆቹ በተሻለ መልኩ ሲንቀሳቀሱ መከላከያዎች በሁለቱም ኮሪደሮች በተለይ በሳሙኤል ታዬ ታግዘው ጫና መፍጠር ችለዋል። የመጀመሪያውን የግብ ዕድልን ለመፍጠር ግን ሀዋሳዎች ቀዳሚ ነበሩ። 3ኛው ደቂቃ ላይ ሙሉአለም ረጋሳ በግራ የመከላከያ የግብ ክልል በሚገባ ያሳለፋት ኳስ ያቡን ዊሊያም ጋር ደርሳ ዊሊያም ወደ ግብ ሲሞክር አወል አብደላ አውጥቶበታል፡፡ የመጀመሪያወቹን 10 ደቂቃዎች ባለሜዳው ሀዋሳ በሀይል አጥቅቶ ለመጫወት ጥረቶችን በማድረግ የግብ አጋጣሚን ሲፈጥር ብናይም በጥብቅ እንደቡድን ሲከላከሉ የነበሩት መከላከያዎች ክፍተትን አልሰጡም። በተለይ ፍቅረየሱስ ክፍት የሆኑ የግብ አጋጣሚዎችን ቢፈጥርም የመጨረሻው የኳሷ ማረፊያ ደካማ በመሆኑ ዕድሎቹ በቀላሉ ሲመክኑ ይታይ ነበር።
መከላከያ በአንፃሩ ፍፁም ገ/ማርያምን ማዕከል ያደረጉ ረጃጅም ኳሶችን በመጣል የሀዋሳን የተከላካይ ስፍራ ያስጨነቀ ሲሆን ከዳዊት እስጢፋኖስ እና ቴዎድሮስ ታፈሰ በሚነሱ ኳሶችም ግብ ለማስቆጠር ከፍተኛ ጥረት አድርጓል፡፡ 21ኛው ደቂቃ ላይ ፍቅረየሱስ የመከላከያ የመስመር ተጫዋቾችን እያታለለ ወደ ሳጥን ገብቶ መሬት ለመሬት የላካትን ኳስ ያቡን ዊሊያም እና ፍሬው ሰለሞን እርስ በእርስ ኳሷን ለማግኘት ሲቻኮሉ አጋጣሚው ሳይጠቀሙበት አምልጧቸዋል። ሆኖም 23ኛው ደቂቃ ላይ የሀዋሳ ከተማ ተጨዋቾች የሰሩትን የቅብብል ስህተት በመጠቀም ሳሙኤል ታዬ ከዊሊያም እግር የነጠቀው ኳስ ከግራ የሀዋሳ የግብ ክልል ሲያሻግርለት ፍፁም ገ/ማርያም አስቆጥሮ አዲሱ ቡድኑን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል፡፡
27ኛው ደቂቃ መሀል ሜዳ ላይ ለሀዋሳ የተሰጠውን ቅጣት ምት አዲስአለም ተስፋዬ የይድነቃቸው ኪዳኔን መውጣት ተመልክቶ ወደ ግብ ቢሞክርም ለጥቂት ወደ ላይ ተነስቶበታል። ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ጥረት ያደረጉት መከላከያዎች ጥረታቸው ሰምሮ 28ኛው ደቂቃ ላይ ከሳሙኤል ታዬ እና ዳዊት እስጢፋኖስ አንድ ሁለት ቅብብል የተጀመረውን ኳስ ዳዊት ብቻውን ለነበረው አቤል ከበደ አሳልፎለት ከሶሆሆ ሜንሳህ ጋር የተገናኘው አቤል መሀል ሜዳ አጋማሽ ላይ በግብ ጠባቂው ጥፋት ሲሰራበት የእለቱ ዋና ዳኛ ተካልኝ ለማ ፊሽካ ነፍተው ካስቆሙ በኃላ አቤል ከወደቀበት በመነሳት ኳሷን ከመረብ ሊያሳርፋት ችሏል። የግቧን መፅደቅ ተከትሎም የሀዋሳ ከተማ ደጋፊዎች የውሀ ፕላስቲክ እና ሌሎች ቁሳቁሶችን በመወርወር ዳኛውን በመቃወማቸው ጨዋታው ለ12 ያህል ደቂቃዎች ለመቋረጥ ተገዷል። ግቧን ያስቆጠረው አቤል ከበደም በእንቅስቃሴው በደረሰበት ጉዳት በምንይሉ ወንድሙ ተቀይሮ ወጥቷል፡፡ ጨዋታው ሲቀጥልም ሀዋሳ ከተማ በአምበሉ ደስታ ዮሀንስ አማካኝነት በእለቱ ዳኛ ላይ ክስ አስመዝግቧል፡፡ የአጋማሹ የመጨረሻ በነበረው ሙከራ በጭማሪ ደቂቃ ያቡን ዊሊያም ካሾለከለት ኳስ ዳዊት ፍቃዱ ከግብ ጠባቂው ይድነቃቸው ኪዳኔ ጋር ተገናኝቶ ልዩነቱን ለማጥበብ ቢቃረብም ይድነቃቸው ሙከራውን አድኖበታል፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሀዋሳ ከተማዎች አሰላለፋቸውን ወደ 4-4-2 በመቀየር በዳዊት ፍቃዱ ላይ አላዛር ፋሲካን ጨምረው በማስገባት ለማጥቃት ሲንቀሳቀሱ የአሰልጣኝ ስዩም ከበደው መከላከያ ደግሞ በ4-5-1 ፈጣን መልሶ ማጥቃትን መተግበር ምርጫው አድርጓል፡፡ አሁንም የኮሪደር ላይ አጨዋወትን ሁለቱም ክለቦች ቢከተሉም የመከላከያ የተሻለ ስኬት ነበረው። ሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ ዳዊት ፍቃዱ በቀጥታ አክርሮ የመታው እና በላይኛው የግቡ ብረት የተመለሰበት ኳስ ምናልባትን ሀዋሳን ወደ ጨዋታው የመመለስ ዕድል ነበረው። ጫናን ፈጥረው ግብ ለማስቆጠር እስከ 60 ደቂቃ ድረስ መከላከያ ላይ የበላይ መሆን የቻሉት ባለሜዳዎቹ የይድነቃቸውን መረብ ለመድፈር ግን ተቸግረዋል። ይባስ ብሎም 63ኛው ደቂቃ ላይ ወደ መከላከያ የግብ ክልል ኳስ እየገፋ ሲገባ ተጠልፊያለሁ በማለት በሳጥን ውስጥ የወደቀው ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን ሆን ብሎ ያደረገው ነው በማለት አልቢትሩ በሁለት ቢጫ በቀይ ካርድ ከሜዳ አስወጥተውታል፡፡
ቀሪውን ደቂቃ በጎደሎ ተጨዋቾች ለመጨረስ የተገደደው ሀዋሳ ከተማ ኃላ ላይ በመከላከያ ብልጫ ተወስዶበታል። በዚህም 65ኛ ደቂቃ ላይ በእለቱ ድንቅ የነበረው አጥቂው ፍፁም ገ/ማርያም አክርሮ የመታውን ኳስ ሶሆሆ ሜንሳህ የመለሰበት ሲሆን 67ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ አሰጨናቂ ሉቃስ በረጅሙ የላካትን ኳስ አላዛር ፋሲካ በግንባሩ ገጭቶ ለዳዊት ሰቶት ዳዊት ፍቃዱ በቀጥታ ሲሞክር ይድነቃቸው ይዞበታል፡፡ በሌላኛው የመከላከያዎች ሙከራ 70ኛው ደቂቃ ላይ ምንይሉ ወንድሙ ከቀኝ መስመር በኩል የላካትን ኳስ ቴዎድሮስ ታፈሰ በቀጥታ ሞክሮ አዲስአለም ተስፋዬ አውጥቶበታል፡፡ ከ9 ደቂቃዎች በኃላ የሀዋሳ ከተማ አማካዮች ስህተት በተንፀባርቀበት የቅብብል ስህተት የተገኘችዋን ኳሰ ዳዊት እስጢፋኖስ መሀል ለመሀል ሰጥቶት ፍፁም ገ/ማርያም በድንቅ አጨራረስ አስቆጥሮ የመከላከያን መሪነት ወደ ሶስት ከፍ አድርጓል፡፡
ከዚህች ግብ በኃላም የሀዋሳ ከተማ ደጋፊዎች በእለቱ ዳኛ ላይ በድጋሚ ተቃውሞን በማሰማት ድንጋይ እና ቁሳቁስ ሲወረውሩ የታዩ ሲሆን ጨዋታውም በድጋሚ ለ14 ደቂቃዎች እንዲቋረጥ ምክንያት ሆነዋል፡፡ ሁኔታው ከተረጋጋ በኋላ ጨዋታው በድጋሚ ሲቀጥል 86ኛው ደቂቃ ላይ ዳንኤል ደርቤ ለፍሬው ሰጥቶት ፍሬው አክርሮ መትቶ የግቡ ቋሚ ከመለሰበት ከሁለት ደቂቃ በኃላ በድጋሚ ዳዊት እስጢፋኖስ የሰጠውን ኳስ ተጠቅሞ ፍፁም ገ/ማርያም ለራሱ ሐት-ትሪክ የሰራበትን ግብ ሲያስቆጥር የመከላከያን የ4-0 ድል አረጋግጧል፡፡ በጨዋታው ማብቂያ ላይም መከላከያዎች ለሀዋሳ ደጋፊ ሰላምታ ሰጥተው ወጥተዋል።
ውበቱ አባተ – ሀዋሳ ከተማ
ለኛ ጥሩ ቀን አልነበረም። የመጀመርያዎቹ ሁለት ጎሎች የገቡበት መንገድ ከጨዋታው እንድንወጣ አድርጎናል። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነን ደግሞ ተጫዋች በቀይ ካርድ መውጣቱ ሁኔታዎችን ከባድ አድርጎብናል። ተጋጣሚያችን መከላከያ አጋጣሚዎች በአግባቡ በመጠቀም ረገድ ጥሩ ነበሩ። ጥሩ ተጫውተዋል ፣ ውጤቱም ይገባቸዋል።
ስዩም ከበደ – መከላከያ
በወራጅ ቀጠና ውስጥ ስለሆንን በእያንዳንዱን ጨዋታ 100% ያለንን ለመስጠት ነው የምንገባው። ከጨዋታ ጨዋታ ቡድናችን መሻሻል እያሳየ ይገኛል። እዚህ ስንመጣም ሀዋሳ ከተማ እንደሚፈትነን ብናውቅም አምናም አአ ከተማን ይዤ እንዳደረግኩት ነው ዛሬም ያደረግኩት። የመጀመርያ 15 እና 20 ደቂቃዎች ቡድኑን ተቆጣጥረን ጎል እንዳያስቆጥሩ ካደረግን በቀሪዎቹ ደቂቃዎች እኛ መነሳሳት እንደምንችል አውቅ ነበር። በዛ መልክ ነው ዛሬ የተጫወትነው። ጎል ካስቆጠርን በኋላ ደግሞ በታክቲኩ ረገድ ጠንካራ የነበረው ሀዋሳ መላላት ጀመረ። ለኛም ነገሮች ቀላል ሆነውልናል። ጨዋታዎችን ባሸነፍን ቁጥር የተጫዋቾቼ ስነልቦና እና ተነሳሽነት እያደገ ይሄዳል።