በ21ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መሪው ጅማ አባጅፋር መሪነቱን ያጠናከረበትን የ4-0 ድል በኢትዮ-ኤሌክትሪክ ላይ አስመዝግቧል።
ሁለቱ ቡድኖች በደረጃው ሰንጠረዥ አናት ላይና ግርጌ እንደመገኘታቸው ጅማ አባ ጅፋር መሪነቱን ለማስጠበቅ ፤ ኤሌክትሪክ ደግሞ ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት የሚያደርገው ጥረት የዛሬውን ጨዋታ ተጠባባቂ አድርጎታል። በጅማ አባጅፋር በኩል ባሳለፋነው ሳምንት ሲዳማ ቡናን ከገጠመው ስብስብ በጉዳት ምክንያት ያልተካተተው አምበሉ ኤልያስ አታሮ ወደ መጀመሪያ አሰላለፍ የተመለሰ ሲሆን አጥቂው ተመስገን ገ/ኪዳንም ከጉዳት መልስ ተጠባባቂ ሆኖ አባ ጅፋሮች በተለመደው የ4-4-2 አሰላለፍ ጨዋታውን ጀምረዋል። ነገር ግን ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በ19ኛው ሳምንት ከዓዲግራት አንድ ነጥብ ይዞ የተመለሰውን አሰላለፋቸውን ሳይቀይሩ ነበር ወደ ሜዳ የገቡት።
የመጀመርያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ጨዋታው ቀዝቀዝ ብሎ የተጀመረበት ነበር። በጀመሪያዎቹ 10 ደቂቃዎች በኳስ ቁጥጥር ረገድ ሁለቱም ቡድኖች ተመጣጣኝነት ቢኖራቸውም ወደ ግብ በመድረስ እና ሙከራ በማድረግ ረገድ ሁለቱም የጎላ እቅስቃሴ ማድረግ አልተቻላቸውም። የቡድኖቹ የቀኝ መስመር ተከላካዮች ሄኖክ አዱኛ እና አወትገ/ሚካኤል የሚያደርጓቸው እቅስቃሴዎች እና አልፎ አልፎ የሚያሻግሯቸው ኳሶች በተከላካዮች ጥረት ውጤታማ ሳይሆኑ ቢቀሩም በአስሩ ደቂቃዎች ውስጥ የሁለቱ ተጫዋቾች እቅስቃሴ ሊጠቀስ የሚችል ነበር። ሆኖም 12ኛው ደቂቃ ላይ የእለቱ የመጀመርያ ግብ ተቆጥሯል። በቀኝ መስመር ሄኖክ አዱኛ ጫላ ድሪባን በሚገረም ሁኔታ አታሎ ያሻገረውን ኳስ የኤሌክትሪክ ተከላካዮችን መዘናጋት በመጠቀም ሳምሶን ቆልቻ ጅማዎችን ቀዳሚ አድርጓል። ከግቧ መገኘት በኃላ ጅማዎች ይበልጥ ጫና በመፍጠር ለመጫወት ችለዋል። በተቃራኒው ኤሌክትሪኮች ደግሞ ሙሉ ለሙሉ አፈግፍገው ለመጫወት ተገደዋል። አጥቂው ታፈሰ ተስፍዬም አብዛኛውን የጨዋታ ግዜ ብቻውን ተነጥሎ ተስተውሏል። ሌላው የኤሌክትሪክ ወሳኝ ተጨዋቾች የሆነው አልሀሰን ካሉሻ በአብዛኛው የሚደርሱትን ኳሶች መቆጣጠር ሲሳነው እና ያገኛቸውን ኳሶች ከረጅም ርቀት እየመታ ሲያባክን የነበረበት ሁኔታ ግርምትን የፈጠረ ነበር።
በጅማዎች ሌላ ሙከራ 23ኛ ደቂቃ ላይ ሳምሶን ቆልቻ ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን ቅጣት ምት ኦኪኪ አፎላቢ ሲመታ ሱሌማን አቡ እንደምንም አውጥቶበታል። ጅማ አባጅፋሮች ከ30ኛው ደቂቃ በኃላ በይበልጥ ጫና መፍጠር ቢችሉም 30 ፣ 31 እና 36ኛ ደቂቃዎች ላይ የሚያስቆጩ የግብ እድሎችን በይሁን አደሻው ፣ ሳምሶን ቆልቻ እና ኦኪኪ አፍላቢ አማካይነት ፈጥረው ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። ሆኖም የመጀመርያው አጋማሽ ሊጠናቅ የዳኛው ፊሽካ በሚጠበቅበት ሰአት ኦኪኪ ፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ በሲሴ ሀሰን የተሰራበትን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ራሱ በማስቆጠር የባለሜዳዎቹን የ 2-0 መሪነት አረጋግጧል። ኤሌክትሪኮች የመጀመርያውን አጋማሽ አንድም ኢላማውን ያልጠበቀ ሙከራ እንኳን ሳያደርጉ ነበር ወደ እረፍት ያመሩት።
ሁለተኛውን አጋማሽ በይበልጥ ተነቃቅተው የጀመሩት አባ ጅፋሮች በኳስ ቁጥጥርም ሆነ በቶሎ ወደ ግብ በመድረስ የተሻሉ ነበሩ። በተለይ በ49ኛው ደቂቃ ላይ ተመስገን ገ/ኪደረን ሳምሶን ቆልቻን ቀይሮ ከገባ በኃላ የአባጅፋሮች የማጥቃት እቅስቃሴ ላይ ፍጥነትን በማከል ሁኔታውን በይበልጥ ለኤሌክትሪኮች አስቸጋሪ አድርጎባቸዋል። ነገር ግን ኤሌክትሪኮች ተክሉ ተስፋዬ ጫላ ድሪባን ተክቶ ከገባ በኃላ በኳስ ቁጥጥሩ በተወሰነ መልኩ ብልጫ ቢወስዱም ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም። በአንፃሩ የጅማ አባ ጅፋሮችን ፈጣን መልሶ የማጥቃት እቅስቃሴዎች ለኤሌክትሪክ ተከላካዮች ፈታኝ ነበሩ። በ76ኛው ደቂቃ በመልሶ ማጥቃት ኦኪኪ እና ተመስገን በአንድ ሁለት ቅብብል ሁለት ተከላካዮችን እና ግብ ጠባቂውን በማለፋ የጅማ አባጅፋርን ሶስተኛ ግብ በተመስገን ገ/ኪዳን አማካይነት አግኝተዋል። በ82 እና 86ኛ ደቂቃዎች ከቀኝ መስመር ተከላካዩ ሄኖክ አዱኛ የተሻገሩትን ኳሶች ኦኪኪ አፎላቢ በሚያስቆጭ መልኩ በግቡ አናት ልኳቸዋል። ያም ቢሆን መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በተጨማሪ ደቂቃዎች ኦኪኪ የተከላካዮችን ስህተት በመጠቀም የጅማ አባጅፋርን 4ኛ እና የራሱን 2ኛ ግብ ማስቆጠር አልተሳነውም። በውጤቱም ጅማ አባጅፋርን የደረጃ ሰንጠረዡን በ38 ነጥቦች መምራቱን ቀጥሏል።
የአሰልጣኞች አስተያየት
አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ
በአመቱ ካስቆጠርናቸው ከፍተኛውን ግብ አስቆጠርንበት እና ልጆቼ በታክቲኩም ሆነ በስነ ልቦናው የተሻሉ የነበሩበት ጨዋታ ነው። የነርሱን አጨዋወት በማጥናት ማንን መቆጣጠር እዳለብን የሰራነው ስራ ተሳክቶልናል።
ም/አሰልጣኝ ቦጋለ ዘውዴ – ኢትዮ ኤሌክትሪክ
በጨዋታው ሙሉ ለሙሉ የጨዋታ ብልጫ ነበራቸው። ማሸነፍ ይገባቸዋል። ቀሪ አስር ጨዋታዎች ስላሉ እነሱ ላይ ተዘጋጅተን እንቀርባለን።