በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 21ኛ ሳምንት ሰበታ ላይ የተካሄደው የወልዲያ እና ሲዳማ ቡና ጨዋታ በሲዳማ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ሲዳማ በውድድር አመቱ ለመጀመርያ ጊዜ ከሜዳው ውጪ ድል ማስመዝገብ ሲችል ጨዋታውን ለ13 ደቂቃ እንዲቋረጥ ያደረገ የደጋፊዎች ግጭትም ታይቷል።
ባሳለፍነው ሳምንት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ባሳለፈው ውሳኔ ቀሪ የፕሪምየር ሊግ የሜዳው ጨዋታዎችን ከ500 ኪሜ ርቀት በላይ በሚገኝ ሜዳ ላይ እንዲያከናውን የተወሰነበት ወልዲያ የቅጣቱ አካል የሆነውን የመጀመርያ ጨዋታ ዛሬ አከናውኗል።
በወልዲያ በኩል በ20ኛው ሳምንት ከመቐለ ከተማ ነጥብ ከተጋራው ስብስብ መካከል በያሬድ ሀሰን እና አሳልፈው መኮንን ምትክ ኤደም ኮድዞ አማረ በቀለን በመጀመርያ አሰላለፍ ሲያካትት ወደ ቡድኑ በተመለሱት ኃይማኖት ግርማ ዋና አሰልጣኝነት እየተመራ ወደ ሜዳ ገብቷል። በሲዳማ በኩል ባለፈው ሳምንት በሜዳው በጅማ አባ ጅፋር ከተረታበት ስብስብ የ4 ተጫዋቾችን ለውጥ በማድረግ በፍቅሩ ወዴሳ፣ ክፍሌ ኪአ፣ ወንድሜነህ ዘሪሁን እና አዲሱ ተስፋዬ ምትክ መሳይ አያኖ፣ ወንድሜነህ አይናለም፣ ዮናታን ፍስሀ እና ፍፁም ተፈሪን ተጠቅመዋል።
ተመጣጣኝ ፉክክር እና ኃይል የተቀላቀለበት እንቅስቃሴ በታየበት የመጀመሪያው አጋማሽ በርካታ የግብ ሙከራዎች የተደረጉ ሲሆን የሰበታ ስታዲየም የመጫወቻ ሜዳ በተለይም በቀኝ ክፍል ውሃ መቋጠሩ በእንቅስቃሴው ላይ ከፍተኛ አሉታዊ አስተዋፅኦ ሲያበረክት ታይቷል። የጎል ሙከራዎች በማድረግ ሲዳማዎች ቀዳሚ ሲሆኑ በ2ኛው ደቂቃ ላይ አዲስ ግደይ ከባዬ ገዛኸኝ የተሻገረትን ኳስ ወደግብ አክርሮ መትቶ ወደ ውጪ ሲወጣበት 5ኛው ደቂቃ በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ወንድሜነህ አይናለም ከሳጥን ውስጥ ወደግብ የመታውን ኳስ ቤሊንጋ ግብ ከመሆን ታድጎታል። በ10ኛው ደቂቃ ላይ ባዬ ገዛኸኝ ተከላካዮችን በማለፍ የሞከራት ሙከራም ሲዳማን ቀዳሚ ልታደርግ የምትችል ነበረች። በወልዲያ በኩል ደግሞ በ4ኛው ደቂቃ ላይ በአንዱለም ንጉሴ የመጀመርያ ሙከራ ሲያደርጉ በ10ኛው ደቂቃ ሐብታሙ ሸዋለም ከርቀት መትቶ ግብ ጠባቂው ያዳነበት ሙከራ ሌላው ተጠቃሽ ሙከራ ነበር።
በ14ኛው ደቂቃ ከረጅም ርቀት ወደፊት የተጣለውን ኳስ የወልዲያው ተከላካይ ቢያድግልኝ ቢደርስባትም ለማራቅ ሲሞክር በቀኝ በኩል ውሃ ቆጥሮ የነበረው የሜዳው ክፍል የኳሱን ፍጥነት በመግታቱ ከተከላካዩ ጀርባ የነበረው አዲስ ግደይ በፍጥነት በመስመር እየገፋ ወደ ግብ ክልል ውስጥ ይዞ በመግባት ለአምበሉ ፍፁም ተፈሪ ያቀበለው ኳስ ፍፁም ወደ ግብነት ለውጦ ሲዳማ ቡና ቀዳሚ መሆን ችሏል።
ከግቡ መቆጠር ባኋላ ሲዳማዎች ከፍተኛ መነቃቃት የታየባቸው ሲሆን በ16ኛው ደቂቃ አዲስ እና ወንድሜነህ በአንድ ሁለት ቅብብል አልፈው የተሞከረውና ቤሊንጌ ያዳነው በ25ኛው ደቂቃ ላይ ባዬ ገዛኸኝ ከትርታዬ ደመቀ በረጅሙ የተሻገረትን ኳስ በመግፋት ከግብ ጠባቂው ጋር ፊት ለፊት ቢገናኝም የቢሊንጋ ድንቅ ብቃት ታክሎበት ወደ ግብነት ሳይለወጥ የቀረው ኳስ የሲዳማን መሪነት ማስፋት የሚችሉ አጋጣሚዎች ነበሩ። በወልዲያ በኩልም አቻ ለመሆን የተቃረቡባቸው ጠንካራ የግብ እድሎች ተፈጥረዋል። በ18ኛው ደቂቃ ላይ በላይ አባይነህ ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ ኤደም በአግባቡ ተቋጣጥሮ ወደፊት በመግፋት ከግብ ጠባቂው ተገናኝቶ የመታው ኳስ በግቡ አናት ላይ የወጣበት እና በ24ኛው ደቂቃ ከማዕዘን የተሻማውን ኳስ ሐብታሙ ሸዋለም በግንባሩ ገጭቶ ፈቱዲን ጀማል ግብ ከመሆን የታደገው ኳስም ለዚህ ማሳያ የሚሆኑ ነበሩ።
ጨዋታው 30 ደቂቃ ከተሻገረ በኋላ ሲዳማዎች በራሳቸው የግብ ክልል ተወስነው ሲጫወቱ በኳስ ቁጥጥር የበላይ የነበሩት ወልዲያዎች ለአቻነት የተቃረቡባቸውን ሙከራዎች አድርገዋል። በ34ኛው ደቂቃ አንዱለም ንጉሴ ከዳንኤል የተሻገረትን ኳስ በግባቡ በመቆጣጠር የግብ ጠባቂውን መውጣት በመመልከት በአናቱ ላይ በመላክ ወደ ግብነት ተለወጠች ተብሎ ሲጠበቅ የግቡን አግዳሚ ገጭታ ወደውጭ የወጣችው ኳስ እጅግ አስቆጪ ነበረች።
ከዕረፍት መልስ ወልዲያዎች ውጤቱን ለመቀልበስ ተጭነው የተጫወቱ ሲሆን በተቃራኒው ሲዳማዋች በመልሶ ማጥቃት መንቀሳቀስን ምርጫቸው አድርገዋል። በ54ኛው ደቂቃ በግራ መስመር አዲስ ግደይ ፍጥነቱን ተጠቅሞ ወደ ፊት በመግፋት በተመሳሳይ በፍጥነት ወደ ወልዲያ የጎል ክልል ሲሮጥ ለነበረው ወንድሜነህ አይናለም ያሳለፍለትን ኳስ ወንድሜነህ በሚታወቅበት ጠንካራ ምት ወደ ግብነት ለውጦ የሲዳማን መሪነት አስፍቷል።
ከጎሉ በኋላ ወልዲያዎች ተደጋጋሚ እድሎች መፍጠር የቻሉ ሲሆን በ56ኛው እና በ57ኛው ደቂቃ መስፍን እና ኤደም ያገኛኟቸውን እድሎች ሳይጠቀሙባቸው ቀርዋል። ከሁለት ደቂቃ በኋላ በ59ኛው ደቂቃ በላይ አባይነህ በግምት ከ20 ሜትር አክርሮ የመታው ኳስ ወደ ግብነት ተለውጦ ወልዲያን ወደ ጨዋታው መመለስ ችሏል። በግቡ የተነቃቁት ወልዲያዎች ለተጨማሪ ግብ ተጭነው የተጫወቱ ሲሆን በ68ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ቢያስቆጥሩም ከጨዋታ ውጪ በሚል ሳይፀድቅ ቀርቷል። በ80ኛው ደቂቃ ላይ መስፍን ኪዳኔ ያገኘውን የግብ ማግባት ዕድል ሳይጠቀምባት ሲቀር በ83ኛው ደቂቃ ላይ በድጋሚ ጎል ቢያስቆጥሩም ከግቡ መቆጠር በፊት ኤደም ከጨዋታ ውጭ ነው በማለት ሳይፀድቅ ቀርቷል። ይህን ተከትሎም ደጋፊዎች ተቃውሟቸውን በዳኛው ላይ ከማሰማት ባለፈ ከተቃራኒ ቡድን ደጋፊዎች ጋር ግጭት ውስጥ የገቡ ሲሆን የፀጥታ ኃይል አስለቃሽ ጭስ እሰከመጠቀም ደርሶ ነበር። በዚህ ምክንያት ጨዋታው ለ13 ደቂቃ ያህል ለመቋረጥ ተገዶ ነበር።
ከዚህች ክስተት በኋላ በ86ኛው ደቂቃ ላይ ባዬ ገዛኸኝ በመጎዳቱ ለህክምና በወጣበት ቅስበት ግሩም አሰፋ የገባ ሲሆን መቀየሩን ያላየው ባዬ ወደሜዳ የገባ ቢሆንም ወዲያውኑ ግን ኳስ ሳይነካ ከሜዳ ወጥቷል። ጨዋታው ማገባደጃ ላይ በ87ኛው ደቂቃ ብርሃኔ አንለይ ከግራ መስመር ከቅጣት ምት የተሻግረትን ኳስ በግንባሩ ቢገጨውም የግቡ አግዳሚ መልሶበታል። ጨዋታውም በሲዳማ ቡና 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ውጤቱን ተከትሎ ሲዳማ ቡና በውድድር አመቱ ከሜዳው ውጪ የመጀመርያ 3 ነጥቡን በማሳካት በ24 ነጥቦች 11ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ 7 ተከታታይ ጨዋታዎች ከድል የራቀው ወልዲያ በ20 ነጥቦች 12ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
የአሰልጣኞች አስተያየት
ኃይማኖት ግርማ – ወልዲያ
በዛሬው ጨዋታ ከእረፍት በፊት እነሱ የተሻሉ ነበሩ። ከዕረፍት ባኋላ ሙሉ ለሙሉ እኛ የተሻልን ነበርን። በርግጥ ያገኘናቸውን አጋጣሚዎች አለመጠቀም ሁለተኛው ደሞ ያገባነውን ግብ አግባብ ባልሆነ ሁኔታ ስለተሻረብን ከዚህ ውጭ ደሞ 11ኛ ተጫዋች ሜዳ ውስጥ የታየበት ዳኝነት ስለታየ በጣም ነው የሚያሳዝነው። በእውነት በዚህ መልክ ቡድናችን ይቀጣል የሚል እምነት አልነበረኝም። ከዚህ ባኃላ ግን ፌደረሽኑ ምንልባት ዕልባት ባይሰጠን ሆን ተብሎ የሚደረግ ስለሚመስል በቃ ፍትህ እንፈልጋለን። ምክንያቱም ንፁህ ጎል ነው ያገባነው። ተሻረብን። ከዛ ውጭ ተቀይሮ የወጣ ተጫዋች ዳኛው እያየው በጓሮ ወጥቶ ሲሄድ ምንም አይነት ውሳኔ አልተሰጠም። ሜዳው አስቸጋሪ ነው፤ አመቺ አልነበረም ነገር ግን ለሁለታችንም እኩል ነበር።
ዘርዓይ ሙሉ – ሲዳማ ቡና
ጨዋታው ጥሩ ነበር። ከእረፍት በፊት ጥሩ ተንቀሳቅሰን ግብ ማስቆጠር ችለናል። ከእረፍት መልስ ግን ተከላክለን መውጣት መርጠናል። ምክንያቱም ሜዳው አስቸጋሪ ስለነበር ነው። እንዴት ይህ ሜዳ እንደተመረጠ አላቅም። ተጋጣሚያችን ረጃጅም ኳሶችን ስለሚጫወቱ በመጀመሪያው አጋማሽ ኳስ ይዘን ለመጫወት ሞክረን ተሳክቶልናል።