ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ኢትዮጵያ ቡና

ትናንት እና ከትናንት በስትያ ያልተጠበቁ ውጤቶችን እና በርከት ያሉ ግቦችን ሲያስመለክተን የቆየው የሊጉ 21ኛ ሳምንት ዛሬ ደግሞ 10፡00 ሰዐት ላይ ተጠባቂውን የሸገር ደርቢ ያስተናግዳል። እኛም የዕለቱን ብቸኛ ጨዋታ በዳሰሳችን ተመልክተነዋል።

ቦታ | አዲስ አበባ ስታድየም

ቀን | ሰኞ ሚያዚያ 15 2010

ሰዐት | 10፡00

ዋና ዳኛ – ኢ/ዳ በላይ ታደሰ

ረዳት ዳኞች – ረዳት ኢ/ዳ ክንዴ ሙሴ እና ረዳት ኢ/ዳ ሀይለራጉኤል ወልዳይ

የቅርብ ጊዜ የሊግ ውጤቶች

ቅዱስ ጊዮርጊስ | አሸ-አሸ-አቻ-ተሸ-አቻ

ኢትዮጵያ ቡና | አሸ-ተሸ-አሸ-አሸ-አሸ


Hulusport.com | ሊንኩን ተጭነው ይወራረዱ


እንደወትሮው ሁሉ የመዲናዋን ሁለት የድጋፍ ሀብታም ክለቦች የሚያገናኘው የሊግ ጨዋታ ለሳምንታት ተጠብቆ ለጨዋታው ቀን ደርሷል። በዛሬው 38ኛ የሊግ ግንኙነታቸው ለሁለቱም ክለቦች ተቀናቃኛቸውን በድል ማንበርከክ ከሚያጎናፅፋቸው ደስታ ባለፈ የሚገኙት ነጥቦች በተጧጧፈው የዋንጫ ፉክክር ውስጥ ከፍ ብሎ ለመገኘት ያላቸው ትርጉም ከሌላው ጊዜ የተለየ ነው። ከመሪው እምብዛም ያልራቁት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና የሻምፒዮንነት ጉዟቸውን ለማሳመር በቀሪዎቹ ሳምንታት ሙሉ ነጥቦችን ማግኘት ግድ ይላቸዋል። ይህን ለማድረግ ደግሞ እርስ በእርስ የሚገናኙበትን የዛሬውን የሸገር ደርቢ በድል ማጠናቀቅ ከምንም በፊት ቅድሚያ ይሰጠዋል።

ከአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የተሰናበተው ቅዱስ ጊዮርጊስ ሙሉ ትኩረቱን ወደ ሊጉ በሚመልስበት ወቅት ነው ወደ ደርቢው የሚመጣው። በአሁጉራዊው ውድድር ምክንያት በሁለተኛው ዙር ሶስት ጨዋታዎችን ብቻ ያደረገው ቅዱስ ጊዮርጊስ ሰባት ነጥቦችን መሰብሰብ ችሏል። ፈረሰኞቹ ከመሪው ጅማ አባ ጅፋር የ8 ነጥብ ልዩነት ቢኖራቸውም የዛሬውን ጨዋታ ማሸነፍ ከቻሉ ከሁለቱ ተስተካካይ ጨዋታዎች ሙሉ ነጥቦችን በማግኘት የደረጃ ሰንጠተዡን ስለመምራት ያልማሉ። ይህ ከሆነም እንደአምናው ሁሉ የመጨረሻ ጨዋታዎቻቸውን በድል በመወጣት ታሪካቸው ታግዘውም ለአምስተኛ ተከታታይ አመት የሊጉን ዋንጫ የማንሳት ዕድላቸው ሰፊ ይሆናል።

ከመጀመሪያው ዙር ማሳረጊያ ጨዋታዎች ጀምሮ ትልቅ መሻሻልን እያሳየ እና ተደጋጋሚ ድሎችን እያገኘ የመጣው ኢትዮጵያ ቡና በሁለተኛው ዙር ጨዋታዎች አርባምንጭ ላይ ከገጠመው ሽንፈት በቀር ከሌሎቹ ሙሉ ሶስት ነጥቦችን አሳክቷል። በጥሩ ብቃት ተጋጣሚዎችን ከመርታት ጀምሮ ባለቁ ደቂቃዎች በተቆጠሩ ግቦች ድሎችን ሲያጣጥሙ የሰነበቱት ቡናማዎቹ የ2003ቱን የሻምፒዮንነት ታሪካቸውን ለመድገም የተነሱ ይመስላሉ። የዛሬውን የሸገር ደርቢ በድል ከተወጡ ደግሞ ሳምንት አዲስ አበባ ላይ የሚያስተናግዱት መሪው ጅማ አባ ጅፋርን በሶስት ነጥቦች ርቀት መከተል ይጀምራሉ።

የቅዱስ ጊዮርጊሶቹ የፊት አጥቂዎች ሳላዲን ሰይድ እና አማራ ማሌ እንዲሁም የመሀል ተከላካዩ ደጉ ደበበ ጉዳት ላይ የሚገኙ ሲሆን ወደ ልምምድ የተመለሱት አስቻለው ታመነ እና ታደለ መንገሻም ለጨዋታው መድረሳቸው አጠራጣሪ ነው። በተቃራኒው በኢትዮጵያ ቡና ቤት ምንም የጉዳት ዜና ባይኖርም በመከላከያው ጨዋታ ቀጥታ ቀይ ካርድ የተመለከተው አስናቀ ሞገስ እና በወልዋሎ ዓ.ዩው ጨዋታ በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ የወጣው ወንድይፍራው ጌታሁን በቅጣት የዛሬው ጨዋታ ያልፋቸዋል።


Hulusport.com | ሊንኩን ተጭነው ይወራረዱ


በቅርብ ሳምንታት የተደረጉትን ጨዋታዎች ከተመለከትን በሁለቱም ቡድኖች ውስጥ የተሻሻሉ ነጥቦችን ማንሳት እንችላለን። በመጀመሪያው ዙር በስድስት ጨዋታዎች ግብ ሳያስቆጥር የወጣው ቅዱስ ጊዮርጊስ በግብ ፊት የተሻለ ጊዜን እያሳለፈ ይገኛል። የመጨረሻ የግብ ዕድል የሚፈጥርባቸውም መንገዶች ወደ ቀደመው አጨዋወቱ አድልተው በቁጥርም ተበታክተው እየታዩ ይገኛሉ። በተመሳሳይ መልኩ ግቦችን በማስቆጠር የተሻሻለው ኢትዮጵያ ቡናም ተሻጋሪ እና ከተጋጣሚ ጀርባ የሚጣሉ ኳሶችን መጠቀም መጀመሩ እንዲሁም ውጤት ማስጠበቅ ሲኖርበት ከሌላው ጊዜ በተለየ የመሀል ክፍል አደረጃጀት ለተጋጣሚ ክፍተትን ባለመስጠት እና ለመልሶ ማጥቃት ዝግጁ በመሆን አዲስ አይነት ባህሪን እየተላበሰ ነው።

በዛሬው ጨዋታ ከኳስ ጋር በሚኖረው እንቅስቃሴ አማካይ ክፍል ላይ በቁጥር ተመጣጣኝ ሆነው የሚገናኙት ሁለቱ ቡድኖች ትልቅ ፍልሚያ ይጠብቃቸዋል። ከኳስ ውጪ የሚኖረውን የተጋጣሚያቸው የማርኪንግ ስርዐት ተከትሎ ክፍተቶች በማይገኙባቸው ወቅቶችም ከመሀል ተከላካዮቻቸው በቀጥታ ወደ ፊት የሚጣሉ ኳሶች የሚኖራቸው ፋይዳ የጎላ ይሆናል። አብዱልከሪም ኒኪማ ከ አማኑኤል ዮሀንስ ፣ ኤልያስ ማሞ ከ ሙሉአለም መስፍን የሚገናኙባቸው ቅፅበቶች ደግሞ ቡድኖቹ መሀል ሜዳ ላይ የሚኖራቸውን የበላይነት ወደ መጨረሻ ተከላካይ ሰንጣቂ ኳሶች ለመቀየር ከመሞከራቸው በፊት የሚጠበቁ ፍልሚያዎች ይሆናሉ።

በአማካይ ክፍል የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን አግኝቶ የግብ ዕድሎችን ከመፍጠር ባለፈ በሽግግሮች ወቅት የቡድኖቹ ተሰላፊዎች የሚኖራቸው ፍጥነት እና እይታ እንዲሁም የተሻጋሪ ኳሶቻቸው ጥራት ከዛሬው ጨዋታ ውጤት የሚያገኙባቸው ሌሎቹ መንገዶች ናቸው። ኢትዮጵያ ቡና ወደ ራሱ ግብ በሚሳብበት እና ኳስ በቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ስር በምትሆንበት አጋጣሚዎች ከሚቀሙ ኳሶች ወደ መሀል ሜዳ ከሚጠጋው የፈረሰኞቹ የተከላካይ መስመር ጀርባ የሚጣሉ ኳሶች ለሳሙኤል ሳኑሚ ጥሩ ዕድሎችን መፍጠራቸው አይቀርም። በተመሳሳይ ግን ደግሞ ለመስመሮች ትኩረት በሚሰጠው የቅዱስ ጊዮርጊስ የማጥቃት ሽግግር ደግሞ ከኢትዮጵያ ቡና የተጋጣሚ ሜዳ የኳስ ፍሰት የሚነጠቁ ኳሶች በፍጥነት ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ የመስመር አጥቂዎች የሚደርሱበትም ሂደት ተጠባቂ ነው። ከፍተኛ የማጥቃት ተሳትፎን ከሚያሳዩት የኢትዮጵያ ቡና የመስመር ተከላካዮች እንዲሁም እንደተጋጣሚያቸው ባይሆንም ወደ ፊት ለመጠጋት የሚሞክሩት የፈረሰኞቹ ተመሳሳይ ሀላፊነት ያላቸው ተጨዋቾች ለኳስ ቁጥጥር የበላይነቱ ካልቸው ፋይዳ ባለፈ ከላይ በተጠቀሱት መንገዶች ተጋጣሚያቸው ዕድሎችን እንዳያገኝ የመሀል ተከላካዮቹን ማገዝ ይጠበቅባቸዋል። ከዚህ ውጪ በተለይ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ለባቲስታዬ ፋዬ እና አዳነ ግርማ ለመሳሰሉ ጥሩ የግንባር ኳስ አጠቃቀም ላላቸው ተጨዋቾች የሚጣሉ ኳሶች ውጤት የመቀየር ዕድላቸው ሰፊ እንደሚሆን ይጠበቃል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ከ1991 የውድድር አመት ጀምሮ 37 ጊዜ የተገናኙት ሁለቱ ቡድኖች 72 ግቦችን ሲያስቆጥሩ 48ቱ 17 ጨዋታዎችን ድል ባደረገው ቅዱስ ጊዮርጊስ 24ቱ ደግሞ 6 ጨዋታዎችን ባሸነፈው ኢትዮጵያ ቡና አማካይነት የተመዘገቡ ነበሩ። 14 የሸገር ደርቢዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል።