የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዝዮን 11ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ትላንት በተካሄዱ ሁለት ጨዋታዎች ፍፃሜውን ሲያገኝ ንግድ ባንክ እና ድሬዳዋ ከተማ አሸንፈዋል።
08:00 ላይ ከሸገር ደርቢ ጨዋታ በፊት የተካሄደው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና መከላከያ የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ በንግድ ባንክ አሸናፊነት ተጠናቋል። ጠንካራ ፉክክር ይስተናገድበታል ተብሎ የተገመተው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በታሰበው መልኩ መልካም ነገር መመልከት የቻልን ሲሆን መከላከያዎች ኳሱን ተቆጣጥረው በተደራጀ መልኩ ኳሱን በመያዝ ወደ ፊት በመሄድ የጎል እድሎችን ለመፍጠር ጥረት ሲያደርጉ ከንግድ ባንክ በጥንቃቄ በረጃጅም ኳሶች በመጠቀም ወደ ፊት በመሄድ በሚፈጥሩት አደጋ ከመከላከያ የተሻሉ ነበሩ።
በ20ኛው ደቂቃ የንግድ ባንክ ተከላካዮች ከግብ ክልላቸው ኳሱን ለማራቅ በማሰብ የመቱት ኳስ በራሳቸው ተጨዋች ተደርቦ በመቅረቱ መዲና አወል አግኝታው ወደፊት ገፍታ በመሄድ ጦረኞቹን ቀዳሚ ማድረግ ስትችል ተጨዋቾቹም በወታደራዊ ሰላምታ ሰብሰብ ብለው ደስታቸውን ገልፀዋል ። ብዙም ሳይቆይ በ22ኛው ደቂቃ ላይ ንግድ ባንክ አቻ ማድረግ የምትችል አጋጣሚ አጥቂዋ ረሂማ ዘርጋው አግኝታ ግብ ጠባቂዋ ማርታ በቀለ እንደምንም ያወጣችው ጎል መሆን የሚችል ነበር። ረሂማ በዘንድሮ የውድድር አመት ለንግድ ባንክ ጥንካሬ ትልቁን ድርሻ እየተወጣች ሲሆን 31ኛው ደቂቃ ላይ ንግድ ባንክ አቻ የምታደርግ ጎል ከማዕዘን ምት የተሻገረውን በግንባሯ ገጭታ ጎል አስቆጥራ ጨዋታው የበለጠ ውጥረት ወደ ተሞላበት ፉክክር ውስጥ ከታዋለች። ኳሱን ተቆጣጥሮ ለመጫወት ቢችሉም የጎል አጋጣሚ መፍጠር ላይ ድክመት የነበረባቸው መከላከያዎች በሚነጠቁት ኳስ በራሳቸው ላይ አደጋ እየፈጠረ ዋጋ አስከፍሏቸዋል ። ንግድ ባንኮች ሌላ ጎል መሆን የሚችል ኳስ በ42 ኛው ደቂቃ ላይ ረሂማ ዘርጋው አግኝታ ሳትጠቀምበት የቀረችው ኳስም የሚያስቆጭ ነበር።
ከእረፍት መልስ ሙሉ ለሙሉ መከላከያዎች ተዳክመው ሲቀርቡ በአንፃሩ ንግድ ባንኮች ተሻሽለው በመምጣት መልካም እንቅስቃሴ ማድረግ ችለዋል ። ከእረፍት መልስ የአቻነቱን ጎል ለንግድ ባንክ ያስቆጠረችው ረሂማ ዘርጋው ሌላ ጎል መሆን የሚችል ነፃ ኳስ 52ኛው ደቂቃ ላይ አግኝታ አገባችው ሲባል ግብጠባቂዋ ማርታ በቀለ እንደምንም አድናባታለች ። ንግድ ባንኮች በተከታታይ በ5 ደቂቃ ልዩነት ሁለት ጎል ማስቆጠር በመቻል ጨዋታውን የበለጠ መቆጣጠር የሚችሉበትን አጋጣሚ ፈጥረዋል። 58 ኛው ደቂቃ ላይ ታደለች አብርሃም በጥሩ ሁኔታ ጎል ስታስቆጥር 63 ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ከማዕዘን ምት የተሻገረውን ህይወት ደንጊሶ በግንባሯ ገጭታ በማስቆጠር የጎሉን መጠን ወደ ሦስት ማስፋት ችላለች። አሰልጣኝ ብርሃኑም ጎሎቹ ሲቆጠሩ ደስታቸውን የገለፁበት መንገድ አግርሞትን የሚጭር ነበር ።
ከሁለቱ ተከታታይ ጎሎች በኋላ ጨዋታው እስኪጠናቀቅ ድረስ ቀዝቀዝ ብሎ የቀጠለ ሲሆን መከለከያዎች ተቀይራ የገቃችው ብሩክታዊት በ76ኛው ደቂቃ ካመከነችው የጎል ሙከራ ውጭ ሌላ የሚጠቀስ የጎል እድል አልፈጠሩም። ጨዋታው መጠናቀቂያ ላይ ጥሩአንቺ መንገሻ ኳስ በእጅ በመንካቷ የተሰጠውን ፍ/ቅ/ምት እመቤት አዲሱ መከላከያን ከመሸነፍ ያላዳነች ጎል አስቆጥራ ጨዋታው በንግድ ባንክ 3 – 2 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ውጤቱን ተከትሎ ንግድ ባንክ ከመሪው ደደቢት ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ ሶስት በማጥበብ በቻምፒዮንነቱ ፉክክር ላይ ነፍስ ሲዘራ መከላከያ ወደ ሶስተኝነት ወርዷል።
ትላንት ረፋድ ላይ ድሬዳዋ ላይ ሲዳማ ቡናን ያስተናገደው ድሬዳዋ ከተማ 3-1 በሆነ ውጤት አሸንፏል። ስራ ይርዳው አንድ መቅደስ ማስረሻ ደግሞ በጨዋታ እና ፍፁም ቅጣት ምት ሁለት ጎሎችን ስታስቆጥር ለሲዳማ ቡና ረድዔት አስረሳኸኝ ብቸኛዋን ጎል አስቆጥራለች።
እሁድ በተካሄደ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ኢትዮ ኤሌክትሪክን 5-2 ማሸነፍ ችሏል። የዘንድሮው ክስተት የሆነችው ቤተልሔም ሰማን በጨዋታው ሶስት ጎሎች አስቆጥራ ሐት-ትሪክ በመስራት በከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ፉክክሩ ሎዛ አበራን መጠጋት ችላለች።
በቅዳሜ መርሀ ግብሮች አዳማ ከተማ በሴናፍ ዋቁማ (4) ፣ ሰርካዲስ ጉታ እና አስካለ ገብረፃድቅ ጎሎች ጌዴኦ ዲላን 6-2 ሲረታ ደደቢት ከ ሀዋሳ ከተማ 2-2 ተለያይተዋል። መሳይ ተመስገን እና ትርሲት መገርሳ ለሀዋሳ፣ ሰናይት ቦጋለ እና ሎዛ አበራ ለደደቢት ግቦቹን ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ናቸው።