ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርስቲ ክለቡን ለአንድ ሳምንት ያልተቀላቀለው ሙሉዓለም ጥላሁን የመጨረሻ ማስጠቀቅያ መስጠቱን በደብዳቤ አሳውቋል።
በዚህ የውድድር ዓመት መጀመርያ መከላከያን ለቆ ወልዋሎን የተቀላቀለውና በሊጉ በስሙ 5 ጎሎች ማስቆጠር የቻለው አጥቂው ወልዋሎ በ20ኛው ሳምንት ወደ አዲስ አበባ አምርቶ በኢትዮጵያ ቡና 2-1 ከተሸነፈ በኋላ ባልታወቀ ምክንያት ወደ ዓዲግራት አልተመለሰም። ክለቡም እንዲመለስ በደብዳቤ ቢያሳውቅም ተጫዋቹ መልስ ለመመለስ ፍቃደኛ ባለመሆኑ ምክንያት ለፌዴሬሽኑ ማሳወቃቸው ገልፀው ይህን ተመልክቶም በአፋጣኝ ወደ ክለቡ ካልተመለሰ እርምጃ እንደሚወስዱ የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ይትባረክ ገ/ስላሴ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል።
በጉዳዩ ዙርያ ሙሉዓለም ጥላሁን ለሶከር ኢትዮጵያ ሰፊ ማብራርያ ለመስጠት ፍቃደኛ ባይሆንም ቅዳሜ ከክለቡ አመራሮች ጋር ከተነጋገረ በኋላ ምላሽ እንደሚሰጥ ገልጿል።