ዛሬ የጀመረው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 22ኛ ሳምንት ነገ በይርጋለም ፣ ድሬደዋ እና ሀዋሳ በሚደረጉ ሶስት ጨዋታዎች የሚቀጥል ይሆናል። እኛም እንደተለመደው በነዚሁ ጨዋታዎች ላይ ቅድመ ዳሰሳችንን እነሆ ብለናል።
ሲዳማ ቡና ከ ደደቢት
ሰባት ግቦችን ያስተናገደው የመጀመሪያው ዙር የአዲስ አበባ ስታድየም የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በብዙዎች ዘንድ የሚታወስ ነው። አቤል ያለው እና ደደቢት ደምቀው ከታዩበት ከዚያ ጨዋታ በኃላ ሰማያዊዎቹ የማይረሳውን የአሸናፊነት ጉዟቸውን ቀጥለው ለረጅም ሳምንታት ሊጉን የመሩ ቢሆንም አሁን ላይ ግን በተቃራኒ ጎዳና ላይ ናቸው። በንፅፅር የተሻለ ወቅታዊ አቋም ላይ ያለው ሲዳማ ቡናም ራሱን ከመውረድ ጭንቀት ነፃ ለማድረግ እየታገለ ነው የሚገኘው። በርግጥም ሲዳማ ቡና ከበርካታ ሽንፈቶቹ መሀል የቅርብ ተፎካካሪዎቹ ወልዋሎ እና ወልዲያ ላይ ያገኘው ድል መጠነኛ እፎይታ ሰጥቶታል። መከላከያ ላይ አራት ግቦች ካዘነበ በኃላ ግብ ማግኘት ፈተና የሆነበት ደደቢት በበኩሉ የመጀመሪያውን ዙር በ29 ነጥቦች መሪነት ጨርሶ አሁን ላይ ግን የሚገኘው 33 ነጥቦች ላይ ብቻ ነው። በሰንጠረዡ ለመንሸራተትም ተከታዮቹ ቡድኖች ተስተካካይ ጨዋታቸውን እስኪያደርጉ እየጠበቀ ይመስላል።
በሁለቱም ተጋጣሚዎች በኩል የተሰማ የጉዳት ዜና የሌለ ሲሆን የደደቢቶቹ ኤፍሬም አሻሞ እና ከድር ኩሊባሊ በአምስት ቢጫ ካርድ እና የቀይ ካርድ ቅጣት ምክንያት ይህ ጨዋታ የሚያልፋቸው ይሆናል። ከዚህ ውጪ የሲዳማ ቡናዎቹ አሻዬ ኬኔዲ እና መሀመድ ኮናቴ ከክለባቸው ጋር የነበረው አለመግባባት በመፈታቱ ለጨዋታው እንደሚደርሱ ተነግሯል።
በውጤት ብቻ ሳይሆን በሜዳ ላይ በሚታየው የቡድን አወቃቀራቸውም እየተዳከሙ የሄዱት ሁለቱ ቡድኖች የነበራቸውን ጠንካራ ጎኖች መልሰው ማግኘት የተቸገሩ ይመስላሉ። ለመልሶ ማጥቃት የተመቹ ፈጣን የመስመር አጥቂዎች የታደለው ሲዳማ ቡና ሌላውን የቡድኑን መዋቅር ይህን ጠንካራ ጎኑን ባማከለ መልኩ መገንባት አለመቻሉ በተጋጣምዎቹ ላይ የበላይነት ለመውሰድ የሚችልበትን መንገድ አጥብቦታል። በነገውም ጨዋታ ሲዳማዎች በተለይ ከኳስ ቁጥጥሩ ውጪ በሚሆኑባቸው ቅፅበቶች በራሳቸው ሜዳ በተቻለ ፍጥነት ኳስ በመቀማት የመስመር አጥቂዎቻቸውን የማጥቃት ባህሪ ካላቸው የተጋጣሚያቸው የመስመር ተከላካዮች ጀርባ እንዲገቡ ለማድረግ መስራት ይጠበቅባቸዋል። በተናጠል የተጨዋቾች አቋም መውረድ ምክንያት ግቦችን እንደልብ ማስቆጠር ዳገት የሆነበት ደደቢት የኃላ መስመር ስህተቶች እና የተዳከመ የአማካይ ክፍል ጥምረት ተጨማሪ ችግሮች ሆነውበታል። ቡድኑ ድንቅ በነበረባቸው የመጀመሪያ ዙር ሳምንታት እጅግ የተዋጣለት የነበረው የአማካይ መስመር ተሰላፊዎቹ ቦታ አያያዝ ለተሳካው ማጥቃቱ የነበረውን እገዛ አሁን ላይ አጥቶታል። በኳስ ቁጥጥሩ የተሻለ ድርሻን ወስዶ ለማጥቃት በሚሞክርበት በእንደነገው አይነት ጨዋታ ላይ ደግሞ በቅርፅ እና በተጨዋቾች ለውጥ ምክንያት ያልተረጋጋውን የመሀል ክፍሉን በእጅጉ ማስተካከል ይጠበቅበታል።
የእርስ በእርስ ግንዝኙነት እና እውነታዎች
– በ2002 የውድድር አመት አንድ ላይ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ያደጉት ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን 17 ጊዜ ተገናኝተዋል። በነዚህ ጊዜያት ሲዳማ ቡና 8 ጊዜ በማሸነፍ የበላይ ሲሆን 5 ጊዜ አቻ ሲለያዩ ደደቢት በ4 አጋጣሚዎች ድል ቃንቶታል።
– በ17 ጨዋታዎች 46 ግቦችን ባስተናገደው የእርስ በእርስ ግንኙነታቸው ሁለቱም እከል 23 ግቦችን አስቆጥረዋል። የእርስ በእርስ ግንኙነታቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ ግቦች የተቆጠሩበትም ነው።
– ደደቢት በሲዳማ ቡና ሜዳ አሸነፎ የማያውቅ ሲሆን ሲዳማ ቡና ከ8 ጨዋታዎች 6ቱን ድል አድርጓል።
– በ2002 ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲሁም በዘንድሮው የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኙባቸው ሁለት ጨዋታዎች በደደቢት 5-2 አሸናፊነት የተጠናቀቁ ነበሩ።
– ደደቢት ካለፉት አራት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ ሲያሳካ ማስቆጠር የቻለውም አንድ ግብ ብቻ ነበር።
– ሲዳማ ቡና በሜዳው ለመጨረሻ ጊዜ ካስተናገዳቸው ሶስት ጨዋታዎች ሁለቴ ሽንፈት ሲቀምስ አንዴ አሸንፏል።
ዳኛ
– ይርጋለም ላይ የሚደረገውን ይህን ጨዋታ ፌደራል ዳኛ ሚካኤሌ አርአያ የሚመራው ይሆናል።
Hulusport.com | ሊንኩን ተጭነው ይወራረዱ
ድሬዳዋ ከተማ ከ ሀዋሳ ከተማ
አምና አስልጣኝ ውበቱ አባተን ለቅጣት ዳርጎ የነበረው ይህ ጨዋታ ዘንድሮ ሁለቱ ቡድኖች ከሽንፈት መልስ የሚገናኙበት ሆኗል። 20ኛው ሳምንት ላይ ከወላይታ ድቻ ጋር የነበረው ጨዋታ በስተካካይነት ተይዞለት የነበረው ድሬደዋ ካተማ ባሳለፍነው እሁድ በሁለተኛው ዙር ሁለተኛው የሆነውን ሽንፈት አዳማ ላይ አስተናግዷል። ሀዋሳ ካተማ ደግሞ ባልተጠበቀ መልኩ በመከላከያ የ4-0 ሽንፈት እንደገጠመው ያሚታወስ ነው። ድሬደዋ ከተማዎች የነጥብ መቀራረብ ከሚታይበት የወራጅ ቀጠና ለመውጣት እና ነጥባቸውንም ከ 20 ለማሻገር ሀይቆቹን የሚያስተናግዱበትን ይህን ጨዋታ ማሸነፍ ይኖርባቸዋል። አሁንም ራሱን ወደ ዋንጫ ፉክክሩ ውስጥ ማስገባት የተሳነው ሀዋሳ ከተማም ይህን ጨዋታ ማሸነፍ ከቻለ ሌላ ከሰንጠረዡ ወገብ ሊላቀቅበት የሚችልበትን ዕድል ያገኛል።
በጨዋታው ድሬደዋ ከተማ አትራም ኩዋሜ ፣ ዘነበ ከበደ ፣ ዮሴፍ ዳሙዬ እና ጀማል ጣሰውን ከጉዳት መልስ ሲያገኝ ለ20 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን ተመርጠው የነበሩት ዮሀንስ ሴጌቦ እና መሳይ ጳውሎስ እንዲሁም ጉዳት ላይ የከረሙት ጂብሪል አህመድ እና ታፈሰ ሰለሞን ዳግሞ በሀዋሳ ስብስብ ውስጥ የተካተቱ ተጨዋቾች ናቸው። ሆኖም የሀዋሳው ሁለገብ አማካይ ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን በመከላከያው ጨዋታ በተመለከተው የቀይ ካርድ ቅጣቱን በዚህ ጨዋታ ይጀምራል።
በሳውሪል ኦልሪሽ እና ኢማኑኤል ላርያ የተከላካይ አማካይ ጥምረት የሚቆጠርበትን የግብ መጠን መቀነስ የቻለው ድሬደዋ በነገው ጨዋታ ከሀዋሳ ከተማ የአማካይ ክፍል ብርቱ ፉክክር እንደሚገጥመው ይጠበቃል። ቁልፍ አማካዮቻቸውን ከጉዳት መልስ የሚያገኙት ሀዋሳዎች መሀል ሜዳ ላይ በሚያደርጓቸው ቅብብሎች በተለይ ተጠጋግተው በመጣመር በሜዳው መሀል ለመሀል የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን በመመከት ላይ ትኩረት ከሚያደርጉት ላርያ እና እልሪሽ ጎን በሚገኙ ክፍተቶች ተጠቅመው የመስመር አጥቂዎቻቸውን ለማግኘት በሚያደርጉት ጥረት የሚኖሩ ፍልሚያዎችም በጨዋታው ተጠባቂ ናቸው። በኩዋሜ አትራም መመለስ የተሻለ ጥንካሬን እንደሚላበስ የሚጠበቀው የድሬደዋ ከተማ የፊት መስመርም የማጥቃት ባህሪ ባላቸው ሶስት አማካዮች በመታገዝ የሶሆሆ ሜንሳህን የግብ ክልል እንደሚፈትኑ ይጠበቃል። ሆኖም በቡድኑ ከወገብ በላይ ባለው ክፍል ውስጥ ሀላፊነት የሚሰጣቸው ተጨዋቾች በተጋጣሚ ሳጥን ውስጥ የሚወስኗቸው የመጨረሻ ውሳኔዎች እጅግ ተሻሽለው መቅረብ ይኖርባቸዋል።
የእርስ በእርስ ግንዝኙነት እና እውነታዎች
– ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን በሊጉ 13 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን በእኩል 4 አጋጣሚዎች ተሽናንፈው 5 ጊዜ አቻ ተለያይተዋል። በ13 ጨዋታዎች ድሬዳዋ ከተማ 14 ሀዋሳ ከተማ 12 ግቦችን አስቆጥረዋል።
– በ6 አጋጣሚዎች ድሬደዋ ላይ ሲገናኙ ባለሜዳዎቹ ድሬዎች 4 ጊዜ አሸንፈዋል። ቀሪዎቹ 2 ጨዋታዎችም በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ በመሆኑ ሀዋሳ ከተማ የነገ ተጋጣሚውን ከሜዳው ውጪ አሸንፎ አያውቅም።
– ሀዋሳ ከተማ ለመጨረሻ ጊዜ ከሜዳው ውጪ ካደረጋቸው ሶስት ጨዋታዎች ሶስት ነጥቦችን ይዞ ሲመለስ በሁሉም አጋጣሚዎች ያስመዘገበው የ1-1 ውጤት ነበር።
– ድሬደዋ ከተማ በሁለተኛው ዙር ከሰበሰባቸው 5 ነጥቦች 4ቱን በሜዳው ካደረጋቸው 2 ጨዋታዎች ያገኘ ሲሆን ግብ ሳያስተናግድም ጭምር ነበር መውጣት የቻለው።
ዳኛ
– ፌደራል ዳኛ ይርጋለም ወ/ጊዮርጊስ በዚህ ጨዋታ ላይ በመሀል ዳኝነት ተመድቧል።
Hulusport.com | ሊንኩን ተጭነው ይወራረዱ
ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ወልዲያ
በሰንጠረዥዡ የታችኛው ክፍል ዋነኛ ተቀናቃኝ ከሆኑ ክለቦች መሀከል የሚጠቀሱት ሁለቱ ክለቦች ከሽንፈት መልስ ነው የሚገናኙት። ጅማ ላይ የ4-0 ሽንፈት ገጥሞት የተመለሰው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከቅርብ ተፎካካሪዎቹ አርባምንጭ ከተማ እና ወልዋሎ ዓ.ዩ እንዳሳካቸው አራት ነጥቦች ሁሉ ከዚህም ጨዋታ ከወራጅ ቀጠናው ቀና የሚልበትን ውጤት ይፈልጋል። ከአሸናፊነት ርቆ ከሜዳ ውጪ ባሉ ጉዳዮች ትኩረቱ የተወሰደው ወልዲያም ከተጋጣሚው ወቅታዊ አቋም አንፃር ነገሮችን ወደ ነበሩበት ለመመለስ ከነገው የተሻለ አጋጣሚ የሚያገኝ አይመስልም። በሳምንቱ አጋማሽ ተጥሎበት የነበረው ቅጣት በይግባኝ ከቀነሰለት በኃላ የመጀመሪያ የሊግ ጨዋታውን የሚያደርገው ወልዲያ ከዚህ ጨዋታ ሙሉ ነጥብ አግኝቶ ድምር ነጥቡን 23 ካደረሰ መጠነናኛ እፎይታ የሚያገኝ ሲሆን ድሉ ለኢትዮ ኤሌክትሪክ የሚሆን ከሆነ ደግሞ ቀያዮቹ ከደረጃው ሰንጠረዥ ግርጌ የመላቀቅ ዕድል ይኖራቸዋል።
በጨዋታው እንደማይሰለፉ የተረጋገጠው የአምስተኛ ቢጫ ካርድ ቅጣት ላይ የሚገኘው የኢትዮ ኤሌክትሪኩ በሀይሉ ተሻገር እና ድሬደዋ ላይ ቀጥታ ቀይ ካርድ በመመልከቱ አራተኛ ጨዋታው በቅጣት የሚያሳልፈው ምንያህል ተሾመ ናቸው።
ከጨዋታው የሚገኙት ነጥቦች ለሁለቱም ቡድኖች ካላቸው ፋይዳ አንፃር ጥንቃቄ የታከለበት አቀራረብ እና ግብ ከተገኘም ውጤት ለማስጠበቅ የሚደረግ መከላከል የጨዋታው ተጠባቂ መገለጫዎች ናቸው። ግብ የማስቆጠር ግዴታ ሲኖርበት ለቡድኑ ዋነኛ የፈጠራ ምንጭ ካሉሻ አልሀሰን ወደ ፊት ተጠግቶ የመጫወት ነፃነት የሚሰጠው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከመጨረሻ አጥቂው ታፈሰ ተስፋዬ በተጨማሪም ለዲዲዬ ለብሪ በጣሙን ወደ መስመር ከሚወጣ ሚና ይልቅ ለታፈሰ ቀርቦ እንዲጫወት የማድረግ ዕቅድ እንደሚኖረው ይገመታል። በዋነኝነት ካሉሻ አልሀሰንን ማዕከል በማድረግ መድረሻቸውን ሁለቱ አጥቂዎች ጋር ከሚያደርጉ ኳሶች ቡድኑ የግብ ዕድሎችን እንደሚፈጥር ይጠበቃል። በወልዲያዎች በኩል ደግሞ ለኤዶም ኮድዞ እና አንዷለም ንጉሴ የሚላኩ ከመስመር አማካዮች የሚነሱ ኳሶች ለቡድኑ ዋነኛ ጥቃት መሰረት እንደሚጥሉ ሲጠበቅ ሐብታሙ ሸዋለም ወልዲያ አማካይ ክፍል ላይ ብልጫ እንዳይወሰድበት ከአጥቂዎቹ እስከ ተከላካይ አማካዩ በሚገኘው ቦታ ላይ የተመጣጠነ እንቅስቃሴ ማድረግ ይጠበቅበታል።
የእርስ በእርስ ግንዝኙነት እና እውነታዎች
– ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን በተገናኙባቸው አምስት አጋጣሚዎች 8 ግቦችን ያስቆጠረው ኢትዮ ኤሌክትሪክ 5 ጊዜ ያሸነፈ ሲሆን አንዴም ድል ያልቀናው ወልዲያ ያስቆጠረው 3 ግቦችን ነበር።
– አዲስ አበባ ላይ በተደረጉት ሁለት ጨዋታዎች ኢትዮ ኤሌክትሪክ የተመሳሳይ 2-0 አሸናፊ ነበር።
– ኢትዮ ኤሌክትሪክ ዘንድሮ አምስት ጊዜ የክልል ክለቦችን ያስተናገደ ሲሆን ሁለቴ የማሸነፍ ሁለቴ ደግሞ የመሸነፍ ውጤት ገጥሞታል።
– ወልዲያ ዘንድሮ ወደ አዲስ አበባ ስታድየም ከመጣባቸው አራት አጋጣሚዎች ሁለት ነጥቦችን አሳክቷል።
ዳኛ
ይህ ጨዋታ በመጀመሪያ ለፌደራል ዳኛ ኢብራሂም አጋዥ የተሰጠ ቢሆንም አልቢትሩ በ21ኛው ሳምንት ከዳኘው የወልዋሎ ዓ.ዩ እና አርባምንጭ ከተማ ጨዋታ መልስ ከገጠመው የመኪና አደጋ እያገገመ የሚገኝ በመሆኑ ኢንተርናሽናል ዳኛ ብሩክ የማነብርሀን ሀላፊነቱን ተረክቧል።