04፡00 ላይ በተደረገው ጨዋታ ሀላባ ከነማ አውስኮድን 1-0 በማሸነፍ ወደ ግማሽ ፍጻሜው ተቀላቅሏል፡፡ የጨዋታውን ብቸኛ ግብ ከመረብ ያሳረፈው እያሱ ታምሩ በ68ኛው ደቂቃ ነው፡፡ ግብ አስቆጣሪው እያሱ የጨታዋው ኮከብ ተብሎም ተመርጧል፡፡
ከጨዋታው በኋላ የሀላባ ከነማው አሰልጣኝ ተመስገን ይልማ የደስታ እንባ እያነቡ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ፈጣሪያቸውንም አመስግነዋል፡፡
‹‹ ከሁሉም በፊት ያረፍንበት ሆቴል አካባቢ ያለው ህብረተሰብ ይሰጠን የነበረውን ድጋፍ ማንሳትና ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡ ጨዋታው በጣም ጥሩ ነበር፡፡ ጥሩ የተጫወተው ቡድን አሸንፏል፡፡ በድሉ በጣም ደስተኞች ነን፡፡ ለዚህም ፈጣሪዬን አመሰግናለሁ፡፡ በግማሽ ፍፃሜው የምንገጥመው ሆሳእና ከነማ የደቡብ ክለብ እንደመሆኑ እነሱም አሸነፉ እኛ የደቡብ ክለብ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ በመግባቱ ደስተኛ ነኝ፡፡ ›› ብለዋል፡፡
የአውስኮዱ አሰልጣኝ ደግያደርጋል ይግዛው በበኩላቸው ለማሸነፍ የነበራቸው ከመጠን ያለፈ ጉጉት ዋጋ እንዳስከፈላቸው ተናግረዋል፡፡ ‹‹ ጨዋታው ጥሎ የማለፍ እንደመሆኑ መጠን ከፍተኛ ፉክክር ተደርጎበታል፡፡ ውጤቱን ለማግኘት ከነበረን ጉጉት የተነሳ የፈለግነውን ማሳካት አልቻልንም፡፡ ሃላባ ከነማ ኳስ ይዞ መጫወት የሚችል ጥሩ ቡድን ነው፡፡ ማሸነፍ አይበዛባቸውም፡፡ ድክመቶቻችንን አርመን በቀጣይ የውድድር ዘመን ወደ ፕሪሚየር ሊግ ለመግባት እንጥራለን›› ብለዋል፡፡
የግማሽ ፍፃሜው ጨዋታ በሁለቱ የደቡብ ክቦች ሆሳእና ከነማ እና ሀላባ ከነማ መካከል ይደረጋል፡፡ ሁለቱ ቡድኖች እርስ በእርስ የሚጫወቱ በመሆናቸው አንድ የደቡብ ክለብ ፕሪሚየር ሊግ ከመግባቱ በተጨማሪ ከሁለቱ አንዳቸው በፕሪሚየር ሊጉ የተሳተፉ 43ኛው ክለብ ይሆናሉ፡፡
ፎቶ – ከላይ የሃላባ ተጫዋቾች ከድሉ በኋላ ፣ መካከል – የሃላባው አሰልጣኝ ተመስገን ፤ ከታች የጨዋታው ኮከብ ተብሎ በድሬዳዋ ስፖርት ኮሚሽን እና ወጣቶች ቢሮ በጋራ የተመረጠው እያሱ ታምሩ