በ22ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አዲስ አበባ ስታድየም ላይ በመከላከያ እና ወልዋሎ ዓ.ዩ መሀከል የተደረገው ጨዋታ እጅግ አሳፋሪ በሆነ ተግባር 84ኛው ደቂቃ ላይ በመከላከያ 2-1 መሪነት ተቋርጧል።
በ21ኛው ሳምንት በተደረጉ ጨዋታዎች ድል የቀናቸው ሁለቱ ቡድኖች በዛሬው ስብስባቸው ላይ ብዙ ለውጥ እንደማያደርጉ የተጠበቀ ሲሆን እንደታሰበውም ወልዋሎ ዓ.ዩ አርባምንጭን የረታበትን ቡድን ሙሉ ለሙሉ ተጠቅሟል። በመከላከያ በኩልም ከሀዋሳ ሶስት ነጥብ ይዞ ከተመለሰው ቡድን የታየው ለውጥ ሁለት ብቻ ነበር። በዚህም መሰረት መሀል ተከላካይ ቦታ ላይ አዲሱ ተስፋዬ የሙሉቀን ደሳለኝን ቦታ ሲይዝ አማካዩ አቤል ከበደ ደግሞ በፊት አጥቂው ምንይሉ ወንድሙ ተተክቷል።
ለኳስ ቁጥጥር ቅድሚያ የሚሰጡት ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያው አጋማሽ ተመጣጣኝ የሆነ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ነበራቸው። ጥቂት የሚባሉ የግብ ሙከራዎች በታዩበት አጋማሽ ወልዋሎዎች የመስመር አጥቂዎቻቸውን መሰረት ባደረገ መልኩ መከላከያዎች ደግሞ የምንይሉ እና ፍፁምን ጥምረት መዳረሻው ባደረገ የማጥቃት እንቅስቃሴ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሞክረዋል። የወልዋሎ ዓ.ዩ የቀኝ መስመር አጥቂ አብዱርሀማን ፉሰይኒ ወደ አማካይ ክፍሉ ቀርቦ ሲጫወት ከቆየ በኃላ ወደ ቀኝ መስመር በተመለሰበት ቅፅበት 8ኛው ደቂቃ ላይ ወደ መሀል ያሻገረው ኳስ በሪችሞንድ አዶንጎ ተሞክሮ በይድነቃቸው ጥረት የወጣበት አጋጣሚ የጨዋታው የመጀመሪያ ሙከራ ሆኗል። በሌላኛው የቡድኑ የግራ ወገን ወደ ሚገኘው ፕሪንስ ሰቨሪንሆ ያደላው የወልዋሎዎች ጥቃት 11ኛው ደቂቃ ላይ ፕሪንስ ራሱ ወደ ውስጥ ባሻገረው ኳስ ሌላ የግብ ሙከራ ለማስገኘት ቢቃረብም ይድነቃቸው ፈጥኖ ኳሷን መቆጣጠር ችሏል። ከመከላከያው የቀኝ መስመር ተከላካይ ምንተስኖት ከበደ ጀርባ በሚጣሉ ኳሶች ላይ ትኩረት ያደረጉት ወልዋሎዎች 22ኛው ደቂቃ ላይ በተመሳሳይ እንቅስቃሴ ከተጣለ እና አጥቂው ሪችሞንድ ይዞ ወደ ውስጥ በገባው ኳስ ቀዳሚ የሚያደርጋቸውን ጎል አግኝተዋል።
ከመጨረሻ አጥቂያቸው ፍፁም ገ/ማርያም ጀርባ ለአማካይ ክፍሉ ቀርቦ ይጫወት በነበረው ሁለተኛው አጥቂ ምንይሉ ወንድሙ እንቅስቃሴ መሀል ላይ የቁጥር ብልጫን አግኝተው ለመጫወት ሲሞክሩ የነበሩት መከላከያዎች የመጨረሻ ኳሶቻቸው ስኬታማ አለመሆን ንፁህ ዕድሎችን እንዳይፈጥሩ አድርጓቸዋል። በመሆኑም ከምንይሉ ወንድሙ እና ሳሙኤል ታዬ የርቀት ሙከራዎች ውጪ አጋጣሚዎችን ሳይፈጥሩ ቆይተዋል። ሆኖም ግብ ከተቆጠረባቸው በኃላ ተጋጣሚያቸው ወደ ኃላ እንዲያፈገፍግ በማድረግ በዳዊት እስጢፋኖስ ፣ ፍፁም ገ/ማርያም እና ሳሙኤል ታዬ አማካይነት በወልዋሎ ሳጥን አቅራቢያ በፈጠሩት ቅብብል ፍፁም ገ/ማርያም ፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ከተገኘ በኃላ በፕሪንስ ሰቨሪንሆ ጥፋት ተሰርቶበት የፍፁም ቅጣት ምት እንዲያገኙ ሆኗል። ምንይሉ ወንድሙም ፍፁም ቅጣት ምቱን በማስቆጠር ቡድኑን 38ኛው ደቂቃ ላይ አቻ አድርጓል። ቀሪዎቹ ደቂቃዎች በተጨዋቾች የሜዳ ላይ ግጭት እና ከዳኛ ጋር በሚፈጠሩ ንትርኮች የተጠናቀቁ ነበሩ። በፕሪንስ ሰቨሪንሆ እና ዋለልኝ ገብሬ ከርቀት የተደረጉ ኢላማቸውን ያልጠበቁ ኳሶችም ብቸኛ የግብ አጋጥሚዎች ሆነው ታይተዋል።
ከእረፍት በኃላ ሁለቱም ቡድኖች የተከላካይ አማካዮቻቸውን በመቀየር ወደ ሜዳ ገብተዋል። በዚህም መሰረት አማኑኤል ተሾመ እና አሳሪ አልመሀዲ በበሀይሉ ግርማ እና ብርሀኑ አሻሞ ተተክተዋል። ከመጀመሪያው አጋማሽ የበረከቱ አጋጣሚዎች በተፈጠሩበት በዚህኛው አጋማሽ የጨዋታውም ፍጥነት እና አዝናኝነትም ጨምሮ ታይቷል። በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን ማግኘት የቻሉት ወልዋሎዎች ወደ ጦሩ የግብ ክልል መድረስ የቻሉባቸው አጋጣሚዎች ግን ከመልሶ ማጥቃት እና ከተቀሙ ኳሶች የተገኙ ነበሩ። በተለይ 55ኛው ደቂቃ ላይ አብዱርሀማን ፉሰይኒ ከዐወል አብደላ ቀምቶ የሰጠውን ኳስ አፈወርቅ ሀይሉ ከሳጥን ውስጥ ሞክሮት ይደነቃቸው ያዳነበት አጋጣሚ ተጠቃሽ ነው። ከሶስት ደቂቃዎች በኃላ ደግሞ ከመልሶ ማጥቃት ፕሪንስ በግራ መስመር ተከላካዮችን አታሎ ገብቶ የሞከረውን ምንተስኖት ተደርቦ አውጥቶበታል።
በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የተወሰደባቸውን ብልጫ መመለስ የቻሉት መከላከያዎች የግብ ዕድሎችን በመፍጠር ከተጋጣሚያቸው ተሽለው ታይተዋል። በዚህ ረገድ በ52 እና 56ኛው ደቂቃ ላይ ከጥሩ ቅብብሎች በኃላ ሳሙኤል ታዬ እና ምንይሉ ወንድሙ የሞከሯቸው ኳሶች ተጠቃሽ ነበሩ። ሆኖም 65ኛው ደቂቃ ላይ ምንተስኖት ከቀኝ መስመር ያሻማው እና ምንይሉ በግንባሩ ገጭቶት በግቡ አግዳሚ የተመለሰው ኳስ ጦሩ ለጎል የቀረበበት ሙከራ ነበር። ይሄውን ኳስ ፍፁም በድጋሜ አግኝቶት ሙከራው ለጥቂት በግቡ ጎን ወጥቶበታል። በእነዚህ ሙከራዎች ተጋግሎ የቀጠለው ጨዋታ 70ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ የስታድየሙ ፓውዛዎች በመጥፋታቸው ፌደራል ዳኛ እያሱ ፈንቴ 73ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታው ከዚህ በላይ መቀጠል የለበትም በሚል እንዲቋረጥ አድርጓል።
ከ16 ደቂቃዎች ቆይታ በኃላ ጨዋታው ዳግም ሲቀጥል ከመቋረጡ በፊት የነበረውን ግለት አጥቶ ታይቷል። መሀል ሜዳ ላይ ተገድቦ ይታይ በነበረው የጨዋታ እንቅስቃሴ ልዩነት የፈጠረውን ቅያሪ ያደረጉት መከላከያዎች የኃላ ኃላ ተጠቃሚ ሆነዋል። አሰልጣኝ ስዩም ከበደ መሀል ተከላካዩ አዲሱ ተስፋዬን በሳሙኤል ሳሊሶ ቀይረው በማስወጣት ቡድናቸው ከኃላ ሶስት ተከላካዮችን አስቀርቶ የመስመር ተመላላሽነት ሀላፊነት በተሰጣቸው ሁለቱ ሳሙኤሎች አማካይነት እንዲጠቀም አድርገዋል። አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያምም ለለውጡ ምላሽ በመስጠት ማናዬ ፋንቱን በአብዱርሀማን ፉሰይኒ ለውጠው ከሶስቱ የመሀል ተከላካዮ ጎን ያለውን ቦታ ለመጠቀም ያሰቡ ይመስሉ ነበር። ሆኖም 84ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር የተሻገረው ኳስ እንደ 65ኛው ደቂቃ ሁሉ በምንይሉ ተገጭቶ በፍፁም ገ/ማርያም የተጨረፈ ሲሆን ይህ አጋጣሚ ግን ወደ ግብነት የተቀየረ ነበር። ነገር ግን ጎሉ የጨዋታው የመጨረሻ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ሆኗል።
የወልዋሎው ግብ ጠባቂ በረከት አማረ ኳሱን በመያዙ ግቡ አልተቆጠረም በማለት የወልዋሎ ተጨዋቾች ፌደራል ዳኛ እያሱ ፈንቴን የከበቡት ሲሆን አርቢትሩ የማዕዘን መምቻ ባንዲራውን ዘንግ ነቅሎ ራሱን በመከላከል በሽሽት ወደ መሮጫው ትራክ ሲያመራ ሌላ ያልጠበቀው ነገር ገጥሞታል። በክስተቱም ግርግርሩን ተከትሎ ወደ ዳኛው የሮጠው የወልዋሎ ዓ.ዩ የቡድን መሪ አቶ ማሩ ገብረፃዲቅ ዳኛውን መሬት ላይ በመጣል በቡጢ ሲማታ በግልፅ ታይቷል። በተጨዋቾች መሀል በተፈጠረው ግርግርም ግብ አስቆጣሪው ፍፁም ገብረማርያምን ጨምሮ ሌሎች ተጨዋቾችም ዱላው አልቀረላቸውም።
ፌደራል ዳኛ እያሱ ፈንቴም ሆኑ ግብ አስቆጣሪው ፍፁም ገብረማርያም የከፋ ጉዳት ባይደርስባቸውም አጋጣሚው ግን እጅግ አሳፋሪ የሆነ እና የእግር ኳሳችንን ዝቅጠት ቁልጭ አርጎ ያሳየ ክስተት ሆኗል። መጨረሻው ያላማረው ጨዋታም እዚሁ ላይ እንዲቋረጥ ሆኗል።