ሀዋሳ ከተማ በ2008 ከተስፋ ቡድን ያሳደጋቸው ሰባት ወጣቶች ለመጪዎቹ ሁለት አመታት የሚያቆይ ኮንትራት ሲያራዝም ዘንድሮ ላሳደጋቸው ሶስት ተጨዋቾች ደግሞ ከፍተኛ የደሞዝ ማሻሻያን አድርጓል፡፡
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ ወጣቶችን ከታችኛው ቡድን በማሳደግ ስማቸው ከሚጠሩ ክለቦች መሀከል አንዱ የሆነው ሀዋሳ ከተማ በ2008 ከ20 አመት በታች የተስፋ ቡድኑ ውስጥ ካሳደጋቸው ስምንት ተጨዋቾች መሀከል ያለፈውን ሁለት አመት ተኩል ብቃታቸውን በጉልህ ማውጣት የቻሉ ሰባት ተጨዋቾችን ውል አራዝሟል። ተጨዋቾቹ ቀሪ ስድስት ወራት እያላቸው ነው ለቀጣዮቹ ሁለት አመታት በክለቡ የሚያቆያቸውን አዲስ ኮንትራት እንዲፈርሙ ነው የተደረገው።
ለቀጣይ ሁለት የውድድር አመታት በሀይቆቹ መለያ እንደምናያቸው የሚጠበቁት እነዚህ ተጨዋቾች ግብ ጠባቂው አላዛር መርኔ ፣ ተከላካዮቹ መሳይ ጳውሎስ ፣ ወንድማገኝ ማዕረግ እና ዮሀንስ ሴጌቦ የአማካይ ስፍራ ተጨዋቾቹ ሄኖክ ድልቢ እና ነጋሽ ታደሰ እንዲሁም የፊት የአጥቂው እስራኤል አሸቱ እንደሆኑ ማወቅ ተችሏል።
በተያያዘ ዜና ደግሞ በዘንድሮው የውድድር ዘመን በተመሳሳይ ከሀዋሳ ተስፋ ቡድን ላደጉት ቸርነት አውሽ ፣ ፀጋአብ ዮሴፍ እና ዳዊት ታደሰ ደግሞ ከፍተኛ የደሞዝ ማሻሻያ እንደተደረገላቸው ክለቡ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጿል፡፡