የመሰረት ማኒ ድንቅ ውሳኔ ድሬዳዋ ከነማን ወደ ግማሽ ፍፃሜ አሳልፎታል

የዛሬ የመጨረሻ የሩብ ፍፃሜ ጨዋታ አስተናጋጁን ከተማ ክለብ ወደ ግማሽ ፍፃሜ አሳልፏል፡፡ ድሬዳዋ ከነማ አዲስ አበባ ከነማን በመለያ ምቶች አሸንፎ በ2003 ወደተሰናበተው ፕሪሚየር ሊግ ለመመለስ ተቃርቧል፡፡

መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የተጠናቀቀው 2-2 በሆነ አቻ ውጤት ሲሆን ግብ በማስቆጠር ቅድሚያውን የያዙት አዲስ አበባ ከነማዎች ናቸው፡፡ የድሬዳዋ ከነማው ተከላካይ ሽመልስ አበበ በራሱ ላይ ያስቆጠረው ግብ አዲስ አበባን መሪ ሲያደርግ በ40ኛው ደቂቃ ፍቃዱ ወርቁ ድሬዳዋ ከነማን አቻ የምታድር ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ድሬዳዋ ከነማዎች በበላይ አባይነህ አማካኝነት መሪ መሆን ችለው ነበር፡፡ በላይ የህ ግቡ በውድድሩ 5ኛው ሆና ተመዝግባለታለች፡፡ ውድድሩንም በኮከብ ግብ አግቢነት ለብቻው መምራት ጀምሯል፡፡ ከ9 ደቂቃዎች በኋላ አማኑኤል ተሾመ በቅጣት ምት ግብ አዲስ አበባን አቻ አድርጎ መደበኛው 90 ደቂቃ በ2-2 አቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡

image-c507feb6c50cadf0f4b9da4cb2df2b1fbf8b626ac19d146c2e518b25e4fc79bc-V
ሁለት መለያ ምቶችን ያዳነው ወርቅነህ

 

ጨዋታው በውጥረት እና ውዝግብ የተሞላ ሲሆን በተደጋጋሚ ሲቋረጥና ማስጠንቀቅያ ካርዶች በተደጋጋሚ ሲመዘዙ ታይታዋል፡፡

የድሬዳዋ ከነማዋ አሰልጣኝ መሰረት ማኒ ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሲል ግብ ጠባቂው አሸናፊ ማሞን አስወጥተው የተሻለ ፍፁም ቅጣት ምት የማዳን ብቃት አለው ብለው ያመኑበትን ወርቅነህ ዲባባን በማስገባት የመለያ ምቶቹን በተጠባባቂው ግብ ጠባቂ ብቃት አሸንፈው ሊወጡ በቅተዋል፡፡

ድሬዳዋ ከነማ በመለያ ምት 3-1 በማሸነፍ ወደ ግማሽ ፍፃሜው ሲያልፍ ወርቅነህ ከተመቱት የመለያ ምቶች ሁለቱን በማዳን ከፍተኛውን ሚና ተጫውቷል፡፡ በላይ አባይነህ ደግሞ የመጨረሻዋን የመለያ ምት ወደ ግብ ቀይሯል፡፡

q
አሰልጣኝ መሰረት ማኒ

በአሰልጣኝ መሰረት ከጨዋው ፍፃሜ በኋላ በሰጡት አስተያየት የግብ ጠባቂ ለውጡን ምክንያት አስረድተዋል፡፡ ‹‹ ግብ ጠባቂ የለወጥኩት የወርቅነህ ፍፁም ቅጣት ምት የማዳን ብቃቱን ስሉልታ ከነማ እያለ ጀምሮ ስለማውቀው ነው፡፡ ›› ብለዋል፡፡ አሰልጣኟ አክለውም ስለ ጨዋታው እና ስለ ቀጣዩ ጨዋታ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ ጨዋታውን ተቆጣጥረናል፡፡ በርካታ የግብ እድል ብንፈጥርም ወደ ግብ መቀየር አልቻልንም፡፡ በግብ ጠባቂ ላይ (በጨዋታው) የተወሰኑ ክፍተቶች ነበሩብን፡፡ ይህንንም ማሻሻል ይጠበቅብናል፡፡ ውጤት እንድናመጣ ከጀርባችን ሲያበረታታን የነበረውን ደጋፊም አመሰግናለሁ፡፡

ዛሬ ቡድኔ እንደጠበቅኩት አልተንቀሳቀሰም፡፡ ቢሆንም ለቀጣይ ጨዋታ የሚቀረን አንድ ቀን ብቻ በመሆኑ ብዙ የምንለውጠው ነገር አይኖርም፡፡ በስነ-ልቡናው ራሳችንን አዘጋጅተን ወደ ፍፃሜው ለማለፍ እንጥራለን፡፡ አሁን ላይ ሆኜ ማሰብ የምችለውም ስለ ፕሪሚየር ሊጉ ሳይሆን ስለ ቀጣዩ የጅማ አባ ቡና ጨዋታ ነው፡፡ ›› ብለዋል፡፡

ድሬዳዋ ከነማ በግማሽ ፍፃሜው ጅማ አባ ቡናን የሚገጥም ሲሆን ማሸነፍ ከቻለ ከ4 የውድድር ዘመን በኋላ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ይመለሳል፡፡

image-39cd244f6db3fbc20b8acc212c4fc30d1421f79aa8c1fbbec7bc3d895d03f177-V
ውድድሩን በኮከብ ግብ አግቢነት የሚመራው በላይ

 

-እዚህ ድረ-ገፅ ላይ የሚወጡ ፅሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሰ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ ፅሁፉን ሲጠቀሙ ምንጭ በመጥቀስ ለስራችን ዋጋ ይስጡ፡፡


 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *