በየሜዳዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ መልኩን እየቀያያየረ ተባብሶ የሚገኘው የስርአት አልበኝነት ጉዳይ አሳሳቢነት ከመቼውም ጊዜ የከፋ ደረጃ ላይ ደርሷል። እየተፈጠረ ባለው ለችግሩ ዙርያ ካላቸው ልምድ በመነሳት መደረግ ስለሚገባቸው የመፍትሄ ሀሳቦች የተለያዩ የስፖርቱ ባለ ድርሻ አካላትን በማናገር የችግሮችን መንስኤ እና የመፍትሄ ሀሳቦች በመያዝ በቀጣይ ቀናቶች ይዘን እንቀርባለን። ለዛሬ በ16 አመት የእግርኳስ ህይወቱ ስሙ በመልካም ስነምግባር ከሚነሱ ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው የሀዋሳ ከተማ ም/አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት እየተፈጠሩ በሚገኙ ችግሮች ዙርያ እና በቀጣይ መስተካከል ስለሚገባቸው ነገሮች ለሶከር ኢትዮዽያ የግል አስተያየቱን ሰጥቷል።
እግርኳስን ለማቆም የተገደድኩበት ምክንያት ይሄው ነው። በየቦታው በየአከባቢው የሚነሱ ችግሮች እጅግ የሚያስፈሩ ናቸው። በተለይ ተጫዋቾች በየጨዋታዎቹ የምናደርጋቸው ከስርአት ውጭ የሆኑ ተግባሮች እየተባባሱ መምጣታቸው እኔን ኳስ ለማቆም መንስኤ ሆኖኛል። የሀገራችን እግርኳስ እንዳያድግ ትልቁ ጠንቅ የሆነው ስርአት አልበኝነት ነው። በክልል ሜዳዎች የሚፈፀሙት ድርጊቶች በጣም አሳፋሪ ናቸው። እከሌ ከእከሌ ብለህ የምትመርጠው አካል የለም ሁሉም ለችግሩ መባባስ ተጠያቂ መሆን አለበት። አዲስ አበባ ላይ የተሻለ ነው በሚባለው ሜዳ እንኳን ሳይቀር አሳፋሪ ተግባር እየተፈፀመበት ይገኛል ። ለዚህ ተጠያቂ ደግሞ እግርኳሱ የሚመለከታቸው አካላት መንግስት ፣ የኢትዮዽያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፣ የክለብ አመራሮች ፣ አሰልጣኞች ፣ ተጨዋቾች እና ሚዲያዎች ናቸው።
እግርኳሱን በጣም እየጎዳነው እንገኛለን። ዛሬ ላይ የሰው መድማት ነው እያየነው ያለነው። ነገ ደግሞ ሰው ይሞታል ማለት ነው። ቀስ እያልን ከእግርኳሱ እንወጣለን፤ ይህ ደግሞ ከባድ ውድቀት ነው። የኢትዮዽያ እግርኳስን መታደግ ካለብን እያንዳንዳችን ችግሮችን ለመሸፋፈን ከመሞከር ይልቅ የስራ ድርሻችንን ወስደን እግርኳሱ በሚፈልገው መንገድ ብንሰራ የተሻለ ነው። እኔ ደስ ያለኝ አሁን ይህንን ስናገር ምንም ወደ ኋላ የምለው ነገር የለም ። ለምን ተጨዋች ሆኜ አይቼዋለው ፣ አሁን ደግሞ አሰልጣኝ ሆኜ አይቼዋለው ። በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ ለስነ ምግባር ተገዢ ሆኜ ኖሬያለሁ።
በቀጣይ ሁላችንም በተለይ ተጨዋቾች ራሳችንን ለዲሲፒሊን ተገዢ ማድረግ አለብን። በእንዲህ አይነት መልኩ መቀጠል የለብንም ፤ ራሳችንን ማረም ያስፈልጋል። ፌዴሬሽኑም እግርኳሱን በአግባቡ በደንቡ መሰረት ሊመራው ይገባል። ዳኞችም ከምንም ነገር ነፃ ሆነው ሊዳኙና አስፈላጊው ከለላ ሊደረግላቸው ይገባል። በአለም እግርኳስ እኛ ኢትዮዽያውያን በምንም ነገር አናንስም። ሆኖም ከአለም የምንለየው ለዲሲፒሊን ተገዢ ባለመሆናችን ብቻ ነው። ስለዚህ ሁላችንም ዲሲፒሊን ሊኖረን ይገባል።