በክረምቱ ሲዳማ ቡናን ተቀላቅለው የነበሩትና በውድድር ዘመኑ ዝቅተኛ ተሳትፎ ያደረጉት ጋናዊው ኬኔዲ አሺያ እና ኢኳቶሪያል ጊኒያዊው ቤን ማማዱ ኮናቴ ከክለቡ ጋር ተለያይተዋል፡፡
ከፕሪምየር ሊጉ ከፍተኛ ተከፋይ ከሆኑ ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው ኬኔዲ በሁለት ጨዋታዎች ብቻ የመጀመርያ ተሰላፊ ሆኖ ወደ ሜዳ የገባ ሲሆን ጥቂት ጨዋታዎችን በተጠባባቂ ወንበር ላይ ተቀምጦ ከማሳላፍ ውጪ በተደጋጋሚ ከ18 ተጫዋቾች ዝርዝር ውጪ ሲሆን የነበረ ተጫዋች ነው። ኢኳቶርያል ጊኒያዊው አማካይ ማማዱ ኮናቴ በአንፃሩ ከኬኔዲ በተሻለ የመጀመርያዎቹ ተከታታይ ሳምንታት ላይ የመሰለፍ እድል ቢያገኝም በጉዳት እና አቋም መውረድ ምክንያት ከቡድኑ ዝርዝር ርቆ ቆይቷል።
ሁለቱ ተጫዋቾች ከዚህ ቀደም ከልምምድ በተደጋጋሚ በመቅረት የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው እንደነበር የሚታወስ ሲሆን የቡድኑ አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉም የተጫዋቾቹ የመጫወት ፍላጎት የወረደ እንደሆነ ገልጿል። “ተጫዋቾቹ የጨዋታ ፍላጎታቸው የወረደ ነው። ለክለቡ ውጤት ማጣት ተጠያቂ ከሆኑት መካከልም ናቸው። ልምምድ ካቆሙ ከ10 ቀናት በላይ ሆኗቸዋል። በአቋማቸው ደስተኛ ባለመሆናችንም ለመለያየት ከውሳኔ ደርሰናል። የተጫዋቾቹ ሁኔታ በቀጣይ ትምህርት ይሆነናል” ብሏል፡፡
ሲዳማ ቡና በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ በ27 ነጥቦች 10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።