በግብፅ ዋንጫ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎች ሰኞ እና ማክሰኞ ሲደረጉ ለፍፃሜ ያለፉ ሁለት ክለቦችም ታውቀዋል፡፡ የኢትዮጵያዊው ኢንተርናሽናል ኡመድ ኡኩሪ ክለብ የሆነው ስሞሃ ከዛማሌክ ጋር ለዋንጫው ክብር ይፋለማል፡፡
ማክሰኞ በተደረገ ጨዋታ ስሞሃ በሩብ ፍፃሜው ኃያሉ አል አህሊን ጥሎ የመጣው አል አስዮትን በመለያ ምት 4-3 በማሸነፍ ለፍፃሜ ሲደርስ በጨዋታው ላይ ኡመድ ለ80 ደቂቃዎች በሜዳ ላይ ቆይቶ ከሜዳ ተቀይሮ ወጥቷል፡፡ በጨዋታው ላይ ተመጣጣኝ ፉክክር የታየበት ሲሆን በመጀመሪያው 45 ስሞሃ በተሻለ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን አድርጓል፡፡ ኡመድ ከቅጣት ምት የተሻገረለትን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ለጥቂት የወጣበት ሙከራ በስሞሃ በኩል በመጀመሪያው አጋማሽ የሚጠቀስ ሙከራ ነበር፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ክለቦች ሙከራ ለማድረግ ሲቸገሩ ቢስተዋልም የአሌክሳንደሪያው ክለብ በተሻለ ያገኛቸውን ያለቀላቸው ጥቂት እድሎች ሲያመክን አምሽቷል፡፡
በ70ኛው ደቂቃ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው አህመድ ተምሳ ስሞሃን ቀዳሚ ሲያደርግ ጨዋታው ሊጠናቀቅ ደቂቃዎች ሲቀሩት ናሚቢያዊው ቤንሰን ሺሎንጎ ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ራሱ መቶ አስዮትነረ አቻ አድርጓል፡፡ ቡድኖቹ በተጨማሪው 30 ደቂቃዎች ግብ ባለማስቆጠራቸው ወደ መለያ ምት አምርተዋል፡፡ በመለያ ምቱም ስሞሃ 4-3 በማሸነፍ ወደ ፍፃሜ ማለፉን አረጋግጧል፡፡ ሰኞ ምሽት በተጠበቀው ጨዋታ ዛማሌክ ኤስማኤሊን 4-1 በሆነ ሰፊ ውጤት አሸንፎ ለፍፃሜው አልፏል፡፡
ስሞሃ ለግብፅ ዋንጫ ፍፃሜ ሲደርስ ይህ ከ2014 በኃላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡ በ2013 ሳላዲን ሰዒድ ከዋዲ ደግላ ጋር ለግብፅ ዋንጫ ፍፃሜ ተፋላሚ ከሆነ በኃላ ደግሞ ኢትዮጵያዊ ተጫዋች የተገኘበት ክለብ ለፍፃሜ ሲደርስ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡ የዋንጫ አሸናፊ የሚሆነው ክለብ በ2019 የቶታል ካፍ ኮንፌድሬሽን ዋንጫ ተሳታፊ ይሆናል፡፡