በ2018 የፊፋ እና የካፍ ኢንተርናሽናል ዳኝነት ባጅ ያገኙት አራቱ ኢትዮዽያውያን ዳኞች ዛሬ ለስልጠና ወደ ካይሮ ሲያቀኑ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ተመስገን ሳሙኤል የA ደረጃ ኤሊት ዳኛ ሆኗል።
በዚህ ዓመት የኢንተርናሽናል ዳኝነት ባጅ ለመጀመርያ ጊዜ ባጅ ያገኙት በወንድ ዳዊት አሳምነው እና ቴዎድሮስ ምትኩ ፤ በሴት ፀሀይ አበበ እና አስናቀች ገብሬ ካፍ ባዘጋጀው የአንድ ሳምንት ስልጣና ላይ ለመካፈል ዛሬ ወደ ካይሮ ያቀናሉ። በእንግሊዝኛ እና ፈረንሳይኛ ሁለት ቦታ ተከፍሎ የሚሰጠው ስልጠና የአንድ ሳምንት ቆይታ ሲኖረው በአዳዲስ እና የተሻሻሉ ህጎች ፣ በአካል ብቃት እንዲሁም በሌሎች መሰረታዊ ጉዳዮች ዙርያ ስልጠና ያገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በተያያዘዘ ዜና ያለፉትን ዓመታት በአፍሪካ መድረክ እንዲሁም በአለም ከ17 አመት ዋንጫ ላይ ውድድሮችን እየመራ የሚገኘው ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ተመስገን ሳሙኤል በግብፅ ሲሰጥ የነበረውን ከፍተኛ የA ኤሊት ዳኞች ስልጠናን በአግባቡ ተከታትሎ በማጠናቀቅ የA ኤሊት ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛነት ባጅን በማግኘት ወደ አአ ተመልሷል። ተመስገን ሳሙኤል ይህን የዳኝነት ደረጃ ማግኘቱ በቀጣይ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተመለከትናቸው እንደሚገኙት ባምላክ ተሰማ እና ሊዲያ ታፈሰ ትልልቅ ውድድሮችን ለመምራት ያስችለዋል።