የወላይታ ድቻው ግብ ጠባቂ ወንድወሰን ገረመው በልምምድ ሜዳ ላይ ከቡድኑ ተጫዋቾች እና ቡድን መሪ ጋር በፈጠረው ግጭት ከተጫዋቾች ማረፊያ እንዲወጣ ሲደረግ የአንድ ዓመት እገዳም ተላልፎበታል። በጉዳዩ ዙርያ ተጫዋቾቹ ለሶከር ኢትዮጵያ የሰጠውን አስተያየት ማስነበባችን ይታወሳል። አሁን ደግሞ የቡድን መሪው አቶ ሐብታሙ እና የክለቡ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ጌታሁንን ምላሾች ይዘን ቀርበናል።
አቶ ሐብታሙ
“በልምምድ ጨዋታ ላይ ከበዛብህ ጋር ግጭት ውስጥ ሲገባ ቀርበን በማገላገል ልምምዱ ቀጥሏል። ከክስተቱ 20 ደቂቃ በኋላ እኔ እና የአሰልጣኞች ቡድን አባላት በቆምንበት ወደ እኔ መጥቶ ፊቱን ወደ እኔ በማስጠጋት ተገቢ ያልሆኑ ቃላት መናገር ጀመረ። እኔም እንደዚህ መነጋር የለብንም ራቅ በልና እናውራ ባልኩት ቅፅበት በቡጢ መታኝ። በአቅራቢያው የነበሩት ከገላገሉን በኋላ ይህ አልበቃ ብሎት በካምፕ ውስጥ ያሬድ ዳዊትን የፌሮ ብረት ይዞ ለመማታት ሲያሳድደው ነበር። በእናንተ ድረ-ገፅ ላይ “ቡድን መሪው በእኩል ሊያየን ሲገባ እኔን ተገቢ ያልሆነ ቃል ስለተናገረኝ ነው የተማታሁት” ብሎ የሰጠው አስተያየት በፍፁም ከእውነት የራቀ ነው።”
ዶ/ር ጌታሁን
” በነገራችን ላይ አንድ ጊዜ ብቻ የታየ አይደለም ፤ እያደገ የመጣ ችግር ነው። ከመስከረም ወር ጀምሮ ግብ ጠባቂነቴን ያለአግባብ ቀምተውኛል የሚል ቅሬታ ነበረው። ክለቡ አንዳንድ ነገሮች ከአሰልጣኞቹ ጋር በመነጋገር እያስታመመ በትዕግስት ነበር የቆየው። በቀደምም ሜዳ ውስጥ በመጀመርያ ከበዛብህ መለዮ ጋር ነበር ጥል የነበረው። በዛብህን ደብድቦታል። የቡድን መሪውን ሐብታሙ ተቀመጥ ተው ስላለው ብቻ ጨዋታው ካለቀ በኋላ ደብድቦታል። ሜዳው ውስጥ ተጨዋች ደብድበህ ከተገላገልክ በኋላ ጨዋታው 15 ደቂቃ ከተቋረጠበት ቀጥሎ ካለቀ በኋላ እንደገና ቡድን መሪን መደብደብ አሳፋሪ ተግባር ነው። በጣም የከፋው ነገር ያ ሜዳ ውስጥ ሊሆን ይችላል። ግን ከሰዓታት በኋላ ደግሞ እንደገና ካምፕ ውስጥ ያሬድን አንተ ነህ “እያቃጠርክ” ከሰው ጋር የምታጣላኝ በማለት ፌሮ ብረት ይዞ ነው ያሯሯጠው። ይህን ሲያገላግል ሙባረክ ሹክርን መቶታል። እኛ ሜዳ ላይ ዳኛ እና ከተቃራኒ ተጨዋች ጋር የሚጣላ አንታገስም ብለን ስልጠና ባዘጋጀንበት ሰዓት የራስህን ቡድን ተጨዋች የመደብደብ ተግባር አስነዋሪ ነው። ስለዚህ ክለቡ በራሱ መተዳደርያ ደንብ መሰረት የ20 ሺህ ብር እና የአንድ ዓመት ቅጣት ተጥሎበታል።