በአዲስ አበባ ከተማ በሚደረገው የአንደኛ ዲቪዚዮን ውድድር ላይ ተሳታፊ ለሆነው ካልዲስ ኮፊ በአጥቂ መስመር ስፍራ ሲጫወት የነበረው በለጠ ሰይፈ ረቡዕ ጠዋት በአልማዝዬ ሜዳ ቡድኑ ልምምድ እየሰራ በነበረበት ወቅት በድንገት ተዝለፍልፎ በመውደቁ የተደናገጡት የቡድን አጋሮቹ ወደ አሜን ሆስፒታል ይዘውት ቢሄዱም ለሁለት ቀናት በሆስፒታል ህክምናውን ሲከታተል ቆይቶ ዛሬ ማለዳ ላይ የማረፉ ዜና ተሰምቷል።
የክለቡ አሰልጣኝ ማርቆስ በቀለ ክለባቸው በበለጠ ህልፈት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ገልፀው በሁኔታው እንደተደናገጡ የተናገሩ ሲሆን በለጠ የዲቪዚዮኑ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ እና ቁልፍ ተጨዋቻቸው እንደነበረ እንዲሁም የውድድሩ የዋንጫ አሸናፊ ለመሆን አንድ ጨዋታ እየጠበቁ እንዲገኙ ካስቻሏቸው ዋነኛ ተጨዋቾች መካከል እንዱ የነበረ በጨዋታ አዋቂነቱም ጭምር የሚታወስ ተጨዋች መሆኑን ጨምረው ተናግረዋል።
በስትሮክ ምክንያት ለሞት መዳረጉ የተነገረው በለጠ ከዚህ ቀደም በቅዱስ ጊዮርጊስ ተስፋ ቡድን ፣ ጅማ ከተማ ፣ አዲስ አበባ ፖሊስ እና አዲስ አበባ ከተማ እንደተጫወተ የተገለፀ ሲሆን ነገ ኮልፌ ቀራንዮ በሚገኘው ፊሊዾስ ቤተክርስቲያን 06:00 ላይ ስርአተ ቀብሩ የሚፈፀም ይሆናል ።
ሶከር ኢትዮጵያ በተጨዋቹ ዕለፈት የተሰማትን ጥልቅ ሀዘን እየገለፀች ለቤተሰቦቹ ፣ የሙያ አጋሮቹ ፣ አድናቂዎቹ እና ለመላው የእግር ኳሱ ቤተሰቦች መፅናናትን ትመኛለች።