በሩዋንዳ አስተናጋጅነት በዚህ ሳምንት ይጀመራል ተብሎ ቢጠበቅም ሴካፋ ለሩዋንዳ መስጠት የሚገባውን ገንዘብ አለመስጠቱን ተከትሎ አዘጋጅ ሀገር የሆነችው ሩዋንዳ የጠየቅነው ጥያቄ እስካልተሟላ ድረስ ውድድሩን እንደማትጀምር መግለጿ ይታወሳል። ለዚህ የሩዋንዳ ምላሽ አፋጣኝ ምላሽ የሰጠው ሴካፋ ውድድሩ እንዲጀመር ሩዋንዳ የጠየቀችውን ገንዘብ ገቢ እንደሚያደርግ በመግለፁ የሴካፋ ዋንጫ ከግንቦት 10 – 20 በሩዋንዳ እንደሚዘጋጅ ተረጋግጧል።
ይህን ተከትሎ ሉሲዎቹ የቡድን አመራሮች ዛሬ ማምሻውን ከፌዴሬሽኑ ጋር ባደረጉት ምክክር በሴካፋ ዋንጫ ላይ መሳተፉ ኢትዮዽያ በአፍሪካ ዋንጫ የመጨረሻ የማጣሪያ ደርሶ መልስ ጨዋታ ከአልጄሪያ ጋር ላለባት ወሳኝ ጨዋታ ጠቀሜታው የጎላ በመሆኑ እንደሚሳተፉ ከስምምነት በመድረሳቸው ልምምዳቸውን አጠናክረው በመቀጠል የፊታችን ሐሙስ 20 ተጨዋቾችን በመያዝ ወደ ሩዋንዳ የሚያቀኑ ሲሆን ከሩዋንዳ መልስ ከጥቂት ቀናት በኋላ ለማጣርያው የመጀመርያ ጨዋታ ወደ አልጄሪያ የሚጓዙ ይሆናል።
የተሳታፊ ሀገራት ብዛት እና የምድብ ድልድል ያልታወቀ በመሆኑ ሴካፋ በዚህ ሁለት ሦስት ቀናት የተሳታፊ ሀገራት እና የምድብ ድልድሉን ይፋ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።
በሴካፋ እና የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታዎች ምክንያት 12ኛ ሳምንት ላይ የደረሰው የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ በቀጣይ ከአንድ ወር በላይ ሊቋረጥ እንደሚችል ተነግሯል ።