– “የህክምና ኮሚቴው አልተበተነም” ሰብሳቢው ዶ/ር ነስረዲን
የዲሲፕሊን ኮሚቴ የሚወስናቸውን የቅጣት ውሳኔዎች በተደጋጋሚ በመቀልበስ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ቅሬታ እና ውዝግብ ሲያስነሳ የቆየውና በሦስት የህግ ባለሙያዎች የተዋቀረው የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ መፍረሱ ይታወሳል።
በዚህም መሰረት በተበተኑት የቀድሞ አባላት ምትክ የህግ ባለሙያ የሆኑ ፤ ስለ እግርኳስ ህግና ደንብ ያላቸው እውቀት እና ልምድን ከግምት በማስገባት ስራውን በአግባቡ ፣ በኃላፊነት እና በብቃት ይወጣሉ በማለት የተዘጋጀውን ልዩ ፎርም በመሙላት ሦስት ግለሰቦች ተመርጠው ተሹመዋል። በነገው ዕለትም የዕውቅና ደብዳቤ ከደረሳቸው በኋላ በገቡ የይግባኝ ጥያቄዎች ስራቸውን በይፋ ይጀምራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በሌላ ዜና የፌዴሬሽን ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የህክምና ኮሚቴው እንዲበተን ተወስኗል ስለተባለው ጉዳይ የህክምና ኮሚቴ ሰብሳቢ እና የስራ አስፈፃሚ አባል የሆኑት ዶ/ር ነስረዲን ማስተባበያ ሰጥተዋል። ” ምንም የተበተነ ነገር የለም። እኔም እንደ እናተው ከሚዲያ ነው የሰማሁት ፤ ጉዳዮንም ወደሚመለከታቸው ኃላፊዎች ደውዬ አጣርቻለው። ምንም የተወሰነ ነገር የለም። ሆኖም ” ዶ/ር አያሌው ጥላሁን ለአንድ ሚዲያ ፌዴሬሽኑን አጥላልተዋል ፤ ይህ ከምን የመነጨ ነው ይጣራ” የሚል ጥያቄ ለእኔ እንደቀረበ ነው የሰማሁት ። አሁን እንደ አጋጣሚ አአ አይደለሁም። ስመጣ የምናየው ይሆናል እንጂ ስንት ለሀገር የሰሩ ባለሙያዎችን እንዲሁ ተነስተህ አትበትንም” ብለዋል።