ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ እራሱን ከግብፅ ዋንጫ አግልሎ የነበረው የአሌክሳንደሪያ ከተማው ክለብ ስሞሃ በፍፃሜ ጨዋታው ላይ ለመሳተፍ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
የስሞሃ ቦርድ እሁድ ምሽት በጉዳዩ ላይ ከመከረ በኃላ የክለቡ ፕሬዝደንት ፋራግ አምር ክለቡ ከዛማሌክ ጋር ማክሰኞ በሚደረገው የፍፃሜ ጨዋታ እንዲጫወት መወሰናቸውን አረጋግጠዋል፡፡ በክለቡ ውስጥ እየተጫወተ የሚገኘው ኡመድ ኡኩሪም በግብፅ ዋንጫ ፍፃሜ የተጫወተ ሁለተኛው ኢትዮጵያዊ የመሆኑ እድል ዳግም ለምልሟል፡፡
የግብፅ እግርኳስ ማህበር የፍፃሜው ጨዋታን የሚመሩ አርቢትሮችን ከውጪ ሃገራት ለማምጣት አለመፈለጉን ተከትሎ ስሞሃ እራሱን ከውድድሩ ለቀናት አግልሎ ቆይቷል፡፡ ሆኖም በግብፅ ወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስቴር ግፊት ወደ ውድድር ስሞሃ መመለሱ ታውቋል፡፡ አምር ባለፉት ጥቂት ቀናት የክለባቸው መብት መገፋቱን አውስተው በህግ አግባብ ተጠያቂ ናቸው ያሏቸውን እንደሚጠይቁ ተናግረዋል፡፡
ስሞሃ በፍፃሜው ጨዋታ ላይ የመሳተፉ ፍንጭ የታየው ቅዳሜ ሲሆን ቡድኑ ሳይበተን ልምምድ ሲሰራ መቆየቱ እራስን እስከማግለል የሚደርስ ውሳኔ ላይ መፅናቱን እንዲያጠራጥር አድርጓል፡፡ ኡመድም ቅዳሜ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረገው ቆይታ ማክሰኞ ዛማሌክን እንደሚገጥሙ ብቻ እንደሚያውቅ እና ልምምዳቸውን አጠናክረው መስራት መቀጠላቸውን ገልፆ ነበር፡፡
የስሞሃን ውሳኔን ተከትሎ መሃመድ ፋሩክ ጨዋታውን እንዲመሩ ተመርጠዋል፡፡ ጨዋታው ማክሰኞ የሚደረግ ሲሆን በ2014 በተመሳሳይ ውድድር ተገናኝተው ዛማሌክ ማሸነፉ ይታወሳል፡፡