ኢትዮጵያዊው አማካይ ቢንያም በላይ በአልባንያ የመጀመርያ አመት ቆይታው ከስከንደርቡ ኮርሲ ጋር የአልባንያ ሱፐር ሊጋ ቻምፒዮን ሆኗል። ተጫዋቹ በአልባንያ እያሳለፈ ስለሚገኘው የእግርኳስ ህይወት፣ ቀጣይ እቅድ እና ተያያዥ ጉዳዮች ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርጓል።
በዚህ እድሜ ከቤተሰብ ርቆ መኖርን እንዴት እየለመድከው ነው ?
በመጀመርያ ደረጃ እኔን አስታውሳቹ አክብራቹ ስለጋበዛችሁኝ አመሰግናለው። ይሄ ዓመት ስጀምረው ቀላል አልነበረም፤ ምክንያቱም ከሀገር ወጥተህ ስትጫወት የለመድከው ባህል ፣ ቤተሰብ ፣ ማህበረሰብ እና ያደክበት አካባቢ ብዙ ብዙ ነገር አለ። ከዚህ አንፃር በመጣሁበት ወቅት በጣም ቀላል አልነበረም። ናፍቆት እየበዛብኝ “ኧረ ወደ ሀገሬ ልመለስ” እል ነበር። ያው ከጊዜ በኋላ የማያልፉት ነገር የለም ትንሽ እየቆየው ስመጣ እየለመድኩ መጣሁ። ግን መጀመርያ ላይ ቀላል አልነበረም።
ከኢትዮዽያ ሊግ ወጥቶ በአውሮፓ በሚገኝ ሊግ ውስጥ መጫወት እንዴት ይገለፃል?
ከኢትዮዽያ ወጥተህ በአውሮፓ መጫወት በጣም አስቸጋሪ ነው። ማለቴ ለሁላችንም ቀላል ነው ብዬ አላስብም። በአውሮፓ ውስጥ መጫወት እና ራስህን ማሳየት ቀላል አይደለም። እኔ የፈረምኩበት አሁን ያለሁበት ክለብ አልባንያ ውስጥ የመጀመርያው ሊግ ውስጥ የሚጫወት እና ብዙ አመታቶችን የውድድሩ አሸናፊ በመሆን የሚታወቅ ከሴሪ አ እና ከሌሎች ሀገራት ተጨዋቾችን የሚያስመጣ ክለብ ነው። እንደዚህ ባለ ክለብ ውስጥ ተቀላቅለህ መጫወት በጣም አስቸጋሪ ነው። ሲቀጥል የሀገራችን የእግርኳስ ደረጃ ሁሉም ሰው የሚያውቀው ነው ። እንደዚህ ነው ብዬ መናገር አልችልም አስቸጋሪ ነው ። ምክንያቱም ለሀገራችን የሚሰጡት ግምት አነስተኛ ነው። በመቀጠል ደግሞ እኛ ተጨዋቾች እንዴት ነው በታክቲክ ላይ ያለን ግንዛቤም ሆነ ቴክኒካል ላይም ሙሉ አይደለንም። ስራ ያስፈልጋል። ያ ያ ነገር ተደራርቦ ከባድ ነው። አስቸጋሪ ጊዜያትን ነው ያሳለፍኩት፤ ግን ትዕግስተኛ መሆን አለብህ። እኔ ያለሁት አሸናፊ ቡድን ውስጥ ነው። ምን አልባት ሌላ ቡድን ውስጥ ብሆን በተደጋጋሚ የመሰለፍ እድል ላገኝ እችል ነበር። እዚህ ከጣልያን ቡድኖች የመጡ ብዙ ዓመት በአልባንያ ብሔራዊ ቡድን የተጫወቱ ናቸው ያሉት። አስቸጋሪ እና ቀላል የማይባል ጊዜ ነበር። ያው ዮሀኪም ፊከርት ብዙ ነገሮችን እዚህ ሳልመጣ ትምህርት ይሰጠኝ የነበረው እውነት እንደ አባት ሆኖ ነው የረዳኝ።
በዩሮፓ ሊግ የተጫወተ የመጀመርያው ኢትዮዽያዊ መሆንህ ምን አይነት ስሜት ፈጠረብህ?
በዩሮፓ ሊግ መጫወት ትልቅ ነገር ነው። እኔ በኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ ሳልጫወት ገና በፊት ራሱ ሳላዲን ሰዒድ ፣ አዳነ ግርማ ፣ ጌታነህ ከበደ እና ሽመልስ በቀለ በስም ነበር የማቃቸው እና ፕሪምየር ሊግ ሲጫወቱ በጣም ነበር የምገረመው እና እኔም ለመጫወት አስብ ስለነበር ለቤተሰቦቼ አንድ ቀን እንደምጫወት እናገር ነበረረ። እንደሚታወቀው ድሬደዋ ነው ተወልጄ ያደኩት። የሚያቀኝ ይናገራል ፤ ልምምድ በጣም ሲበዛ ነበር የምሰራው። እንዳንዴ ስለሰራህ ብቻ ሳይሆን ፈጣሪም ልፋትህን ይቆጥርልሀል። አሁን የውድድሩ አሸናፊ ነን ፤ በቀጣይ አመት ከፈጣሪ ጋር የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ነው የምንጫወተው። ያን ሳስበው በጣም ነው የሚገርመኝ። ምክንያቱም በኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ በመጫወቴ እገረም የነበረውን ፈጣሪ ያላሰብኩትን ሰጠኝ።
በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ከተጫወትክ ሌላ ታሪክ ነው የሚሆነው። ይህንን ለማሳካት ምን ታስባለህ?
አሁን ተጀምሯል እንጂ አላለቀም። እዚህ መድረሴ ፈጠዝያ ውስጥ የሚከተኝ ደረጃ ውስጥ ነኝ ብዬ አላስብም ፤ ይሄ የመጀመርያዬ ነው ። ፈጣሪ ነው ይሄን ያደረገው ፤ ቶሎ ይሳካ እንጂ ሊዘገይም ይችል ነበር። አሁን ላይ መስራት አለብኝ አንድ እና አንድ የተሻለ ደረጃ ለመድረስ መስራት ይጠይቃል። ክለቡ ከሚሰጠኝ ልምምድ ውጭ በትርፍ ጊዜዬ መስራት ካልቻልኩ ሁልጊዜ የተሻለ ደረጃ እደርሳለው ብለህ ትመኛለህ እንጂ የትም አትደርስም። ስለዚህ የተሻለ ደረጃ መድረስ ካሰብክ መስራት ያስፈልጋል የ። ለምሳሌ ያሉበት ደረጃ በቂ ቢሆን ኖሮ የአምስት ጊዜ የአለም ኮከብ የሆኑት ሮናልዶ እና ሜሲ ልምምድ አይሰሩም ነበር። አሁን ስራ ነው የሚጠብቀኝ። አሁን ባለኝ ነገር ጥሩ ሰርቼ ክለቡ ከዚህ በተሻለ በእኔ የሚደሰትበት ጊዜ ፣ እኔም የራሴ ብቃት የተሻለ እንዲደርስ እማራለው እሰራለው ስህተቴን እየቀነስኩ እሄዳለው ።
የጥንካሬህ ሚስጢር ምንድነው?
በፕሪምየር ሊግ ለባንክ ስጫወት ማንም ሰው እንደሚያውቀው በቀን ሁለት ጊዜ ነበር ልምምድ የምሰራው። አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪ/ማርያም ቀጥሎም በአሰልጣኝ ስር እነሱ በሚያወጡት ፕሮግራም መሰረት እሰራና በመቀጠል በጂም እሰራ ነበር። የተሻለ ደረጃ ለመድረስ ልምምድ በትርፍህ ጊዜ ካልሰራህ ሁልጊዜ የተሻለ ደረጃ አትደርስም። የተሻለ ደረጃ እንደምደርስ አውቅ ነበር። ቀላል አይደለም ዓመቱን ሙሉ ሁለት ጊዜ ልምምድ እየሰራህ እረፍት ሳይኖርህ የዛ ልፋት ውጤት ነው። እንዲሁም በብሔራዊ ቡድን ዮሐንስ ሳህሌ ከመጣ በኋላ ከታች ጀምሮ ስለሚያውቀኝ ሁልጊዜ ድጋፍ ያደርግልኝ ነበር። ምን ምን ማስተካከል እንዳለብኝ ከፊከርት ጋር በመሆን ይረዳኝ ነበር። የእነዚህ ነገሮች ድምር እየረዳኝ መጥቷል። እኔም ስህተቴን እየቀነስኩ የመጫወት እድል እያገኘው ስሄድ የተሻለ ነገር ማሳየት ቻልኩ። እነሱ ቢረዱኝም እኔ በጣም ነበር የምሰራው ፤ ፕሮፌሽናል መሆን ካሰብክ ትልቁ ነገር ስህተት መቀነስ ነው። ከስራ የመጣ ነው ብዬ የማስበው ። በመቀጠል የተመቻቸ ኑሮ ካለው ቤተሰብ ጋር አይደለም ያደኩት። አባቴም እናቴ በጤና ነው ያሉት። የቻሉትን አድርገው አሳድገውኛሁ። አንዳንዴ ችግር ያስተምራል እና ለጥንካሬዬ እሱ ነው ሚስጢሩ።
የሀገራችንን ሊግ ፣ የተጫዋቾችን አቅም ፣ የፌዴሬሽን አደረጃጀት እና አጠቃላይ ስርዓቱ ከአውሮፓ ጋር ሲነፃፀር እንዴት ይገለፃል?
እዚህ ለመድረስ በጣም ብዙ ስራ ይጠይቃል። ይሄ ምንም ጥያቄ የለውም። እዚህ ለመድረስ እኛ እንኳን አውሮፓ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር እንኳ መፎካር አይደለም በፊት የምናሸንፈቸው ክለቦች እና ሀገሮች ከአመት አመት እየተሻሻሉ ፣ ከጊዜው ጋር ራሳቸውን እያራመዱ ነው። አሰልጣኞች እንዴት ማሰልጠን እንዳለባቸው ይማራሉ ፣ ተጫዋቾችም እንዲሁ እየሰሩ ነው ፣ በማቴሪያል እየተሟሉ በፌዴሬሽን ደረጃ አደረጃጀታቸውን እያስተካከሉ ነው። በእርግጥ ሁሉም ሀገር ችግር አለ ችግር የለም አይባልም። ግን እኛ ሀገር አሁን ለምሳሌ በዚህ ኳሳችን ላይ በፌዴሬሽን ደረጃ በቀላሉ ምርጫ አልተካሄደም። እኛ በስፔን ፣ በእንግሊዝ ወይስ በየትኛው ደረጃ ሆነን ነው እንዲህ የሚደባደቡት? ስልጣን ለመያዝ ብቻ ከሆነ ጥሩ አይደለም። በዚህ ሰዓት ካለንበት ዝቅተኛ ደረጃ አንጻር አንዱ ከአንዱ ጋር ተጋግዞ ተገቢ የሆነ ሰው ስልጣኑን ይዞ ነበር ወደ ስራ መግባት የነበረብን። አንዱ ተነስቶ ተጫዋች ሲሰድብ እና ሲዘልፍ አያለሁ። አይተች አይደለም ሲናገርም ፕሮፌሽናል መሆን አለበት። ሚዲያ መስተካከል አለበት ፤ ፌዴሬሽኑም መስተካከል ይገባዋል። በአጠቃላይ ብዙ ችግሮች መስተካከል አለባቸው። ተጫዋቹም ለምድነው የማይለወጠው የተሻለ ደረጃ ለመድረስ መስራት አለበት። ተመሳሳይ ጊዜዎችን ማሳለፍ የለበትም። ሁሉም ተጨዋች የራሱ ክህሎት አለው ፤ ግን ስራ ይጠይቃል። በመቀጠል ኢንተርናሽናል ጨዋታ የለም። ብሔራዊ ቡድኑ ልምድ አያገኝም፤ ቀጥታ ወደ ውድድር ነው የሚገቡት። ልምድ ከሌለህ ደግሞ ትሸነፋለህ ። ስለዚህ እንደዚህ ያሉ ነገሮች ሊስተካከሉ ይገባል ። እዚህ የሀገራት የወዳጅነት ጨዋታ ላይ አትሄድም እንዴ ይሉኛል። ሁሉም ሰው ባለበት የስራ ድርሻ መሰረት መስራት ይጠበቅበታል።
ቀጣይ እቅድህ ምንድነው? ስለ አልባንያ ዋንጫ ምን ታስባለህ? ወደ አአ መቼ ትመጣለህ?
ሁለት ጨዋታ እየቀረን ነው የዋንጫ አሸናፊ የሆነው በቀጣይ የአልባንያ ዋንጫ ጨዋታ ይቀረናል። ከፈጣሪ ጋር የድርብ ቻምፒየን ለመሆን ነው የምፈልገው። በተሰጠኝ ጊዜያት ጥሩ ነገር እያሳየሁ ነው። በተከታታይ ቻምፒዮን ስለመሆን አስበለው። አዲስ አበባ ቤተሰቤን ለማየት እመጣለው ፤ ከዚህ በፊት ግን አንዳንድ ጉዳዮች አሉኝ። ፈጣሪ ካለ የተሻለ አጋጣሚ ይኖራል። የተሻለ ነገር ካለ ከፊከርት እና ከወኪሎቼ ጋር ተነጋግሬ እሄዳለው ብዬ አስባለው ። እረፍትን ቀዳሚ አላደርግም ስራ ነው የሚበልጠው። የሚሻል ቦታ የሚገኝ ከሆነ እሄዳለው ካልሆነ እዚሁ የምቀጥል ይሆናል። ከዚህ በኋላ በግንቦት መጨረሻ ውድድሮች ሲጠናቀቁ ቤተሰቤን ለማየት ወደ ኢትዮጵያ የምመጣ ይሆናል ።
በመጨረሻም ማመስገን የምፈልጋቸው አካላት አሉ። ከሚዲያ ሰዒድ ኪያር እና መኳንንት በርኼ እንደ ወንድም እየደወሉ ይጠይቁኛል ፤ እነሱን ማመስገን እፈልጋለው። እዚህ ስመጣ ዮርዳኖስ አባይ ከእኔ ጋር ነበር ይደውልልኛል እሱን ላመስግን። ብዙ ያልጠራኋቸው ሰዎች አሉ እዮብ ተዋበ ፣ፀጋዬ ኪ/ማርያም ፣ ሲሳይ ከበደን ማመስገን እፈልጋለው ። ዮሐንስ ሳህሌ እና ዮሀኪም ፊከርት አባቶቼን ማመስገን እፈልጋለው።