የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ በአፍሪካ ክለቦች ውድድር ምክንያት ባልተደረጉ ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች ሲቀጥል መቐለ ላይ በቻምፒዮንነት ፉክክሩ ዋና ተዋናይ የሆኑት መቐለ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስን ያገናኘው ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ከመጀመሩ በፊት የልምድ ልውውጥ እና እውቅና የመስጠት አላማን ሰንቆ በተካሄደው የቀድሞ የጉና ንግድ እና ትራንስ ኢትዮጵያ ተጫዋቾች ጨዋታ አሸናፊ ለነበረው ጉና ንግድ የሽልማት ስነስርዓት ተካሂዷል። ከዚህ በተጨማሪም ለተሻለ ህክምና ወደ ውጭ አገር ለተጓዙት አንጋፋው አሰልጣኝ ስዩም አባተ መቐለ ከተማ ስፖርት ክለብ የ50 ሺ ብር ድጋፍ አድርጓል።
በጨዋታው የመጀመርያ አጋማሽ ሁለቱም ክለቦች በተመሳሳይ ደካማ እና ያልተጠና የማጥቃት አጨዋወት በመምረጣቸው እና ሁለቱም በተመሳሳይ መሃል ሜዳ ላይ ያተኮረ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ለመውሰድ በማሰብ ሙከራ በማድረጋቸው በተጠጋጋው የ ተጫዋቾች አቋቋም ምክንያት ጥሩ የኳስ ፍሰት ልንመለከት አልቻልንም።
በ2ኛው ደቂቃ ላይ መቐለ ያገኘውን ቅጣት ምት ጋይሳ ቢስማርክ በቀጥታ ወደ ግብ መትቶ ኦዶንካራ ያዳነበት ኳስ የጨዋታው የመጀመሪያ ሙከራ ነበር። በመጀመርያዎቹ 18 ደቂቃዎች ባለሜዳዎቹ መቐለ ከተማዎች በ ጊዮርጊስ ግብ ክልል አካባቢ 4 የሚደርሱ የቆሙ ኳሶችን አግኝተው ወደግብ ቢያሻሙም አንዳቸውም ግብጠባቂው ሮበርት ኦዶንካራን ሳይፈትኑ ከሽፈዋል። እንግዶቹ ቅዱስ ጊዮርጊሶችም በመሃሪ መና እና አብዱልከሪም ኒኪማ በኩል ሙከራ ያደረጉ ሲሆን በተለይም ኒኪማ ከሳጥን ውጭ ካደረጋቸው ሙከራዎች አንዱ ለግብ የቀረበ ነበረ።
ደቂቃዎች እየገፉ በሄዱ ቁጥር ከአጭር ኳስ ባለፈ ረጃጅም ኳሶችን እና ቀጥተኛ አጨዋወት የመረጡት መቐለ ከተማዎች ሁለቱ የመሃል አማካዮቻቸው አመለ ሚልክያስ እና ሚካኤል ደስታ በተመሳሳይ የሜዳ ክፍል ትይዩ መጫወታቸው ከመስመር አማካዮቹ እና ከፊት ጥሩ ሲንቀሳቀስ ከነበረው ኣማኑኤል ገ/ሚካኤል ጋር በአግባቡ መገናኘት ተስኗቸው ታይትዋል። በዚህ መሃል ግን የ መቐለ ከተማዎች የረጅም ኳስ ኣጨዋወት ፍሬ አፍርቶ አመለ ሚልክያስ ከ መሃል ሜዳ አጋማሽ የላከውን ኳስ አማኑኤል በደረቱ አብርዶ ቢመታም ኦዶንካራ አድኖበታል።
በጊዮርጊሶች በኩል ናትናኤል ዘለቀ ወደ ራሱ የግብ ክልል ተጠግቶ በሁለቱ ተከላካዮች መሃል በመጫወት ቡድኑን ሲያግዝ ኳስ በሚመሰርትበት ግዜ ተጨማሪ የቅብብል አማራጭ ከመፍጠሩም ባለፈ ለመስመር ተከላካዮቹ ነፃነት ቢሰጥም ተከላካዮቹ ወደ ፊት በሄዱባቸው አጋጣሚዎች እምብዛም ውጤታም አልነበሩም። በሌላ በኩል የመቐለ መስመር አማካዮች የጊዮርጊስ የመስመር ተከላካዮች ከኋላ የፈጠሩትን ክፍተት ተጠቅመው ለማጥቃት አለመሞከራቸው በርካታ የግብ ዕድሎችን መፍጠር አልቻሉም።
በመጀመርያው አጋማሽ በነበረው ያልተጠና አጨዋወት አንፃር እና ተደጋጋሚ በሚሰማው የዳኛ ፊሽካ ምክኒያት ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ጥቂቶች ነበሩ።
ሁለተኛው አጋማሽ በጨዋታ ፍሰት እና ወደ ተጋጣሚ ግብ ክልል በመድረስ የተሻለ ነገር የታየበት፤ በተለይም የቅዱስ ጊዮርጊሶች ብልጫ የተስተዋለበት ነበር። በተለይም ኣሜ መሃመድ ከዣቭየር ኦስቫልዶ ጋር የቦታ ለውጥ ካረገ በኋላ እንግዶቹ የተሻለ መንቀሳቀስ ችለዋል።
የዣቭየር ኦስቫልዶ እና ኣሜ መሃመድ ቅንጅትን በግራ መስመራቸው እንደ ዋነኛ የማጥቃት አማራጭ ሲጠቀሙ የነበሩት ጊዮርጊሶች በሁለቱ ተጫዋቾች አማካኝነት ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች አድርገው ነበር። በተለይም ኦስቫልዶ ከመስመር ኳስ ይዞ ገብቶ አክርሮ መትቶ ኦቮኖ ያዳነበት ሙከራ የሚያስቆጭ ነበረ።
በመቐለ ከተማ በኩልም የሚካኤል ደስታ እና አመለ ሚልክያስ ወደ ተከላካዮቹ ቀርቦ መጫወት የጊዮርጊስ የማጥቃት አጨዋወትን በአግባቡ መመከት ቢያስችላቸውም አማካዮቹ በማጥቃት ሽግግሩ ባላቸው አናሳ አስተዋፅኦ ምክንያት የቡድኑ የማጥቃት ሃላፊነት በ አማኑኤል ላይ ብቻ የተንጠለጠለ ነበር። በ59ኛው ደቂቃም አማኑኤል ገ/ሚካኤል በግል ጥረቱ በሚያስደንቅ ብቃት የጊዮርጊስ ተከላካዮች ቢያልፍም ኦዶንካራ ከግብ መስመሩ በመውጣት ይዞበታል።
መቐለ ከተማ በብቸኛ አጥቂነት ያሰለፈው አማኑኤል ቡድኑ አልፎ አልፎ የሚፈጥራቸው የግብ ዕድሎችን ተጠቅሞ ከጊዮርጊስ ተከላካዮች ጋር የ 1ለ1 ፍልሚያዎችን በተደጋጋሚ ቢያሸንፍም ጥረቱ በቡድን አጋሮቹ የተደገፈ ባለመሆኑ ፍሬያማ መሆን አልቻለም። ሆኖም በጉዳት የወጣውን ጋይሳ ቢስማርክ ቀይሮ የገባው እያሱ ተስፋዬ በረጅሙ ያሻማውን ኳስ በደረቱ ኣብርዶ በመምታት ወደግብ ቀይሮ ባለሜዳዎቹን መሪ ማድረግ ችሏል::
ግቡ ከተቆጠረ በኋላ የአጨዋወት እና የተጫዋቾች ለውጥ ያደረጉት ጊዮርጊሶች የተሻለ መንቀሳቀስ ችለዋል። አብዱከሪም ኒኪማ ከርቀት መትቶ የግቡ ቋሚ ሲመልስበት የተመለሰው ኳስ ኣብዱልከሪም መሃመድ አክርሮ በመምታት ግሩም የአቻነት ግብ አስቆጥሮ ክለባቸውን ለማበረታታት የተጓዙትን ደጋፊዎች ኣስፈንድቋል::
መቐለ ከተማዎች ግብ ካስተናገዱ በኋላ የተሻለ ኣጥቅተው የተጫወቱ ሲሆን በካርሎስ ዳምጠው እና ጋቶች ፓኖም ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ማድርግ ችለው ነበር። በተለይም አሞስ ያሻማውን ጋቶች መትቶ አስቻለው ተደርቦ ያወጣው ኳስ የመቐለ ደጋፊዎችን ያስቆጨ ነበር።
በጨዋታው መገባደጃ ላይ አብዱልከሪም ያሻገረውን ኳስ የ መቐለ ተከላካዮችን ትኩረት ማነስ ተጠቅሞ ነፃ አቋቋም ላይ የነበረው አዳነ ግርማ በግንባሩ ቢሞክርም ኳሱ ከግብ ጠባቂው ፊሊፕ ኦቮኖ ፊት ለፊት በመሆኑ ተመልሶበታል።
ጨዋታው 1-1 በሆነ አቻ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ37 ነጥብ በነበረበት 2ኛ ደረጃ ሲቀጥል 36 ነጥብ ያለው መቐለ ከተማ በግብ ክፍያ አዳማ ከተማን በመብለጥ 3ኛ ደረጃን ይዟል። ፕሪምየር ሊጉ በአጓጊ የቻምፒዮንነት ፋክክር ታጅቦ በሚቀጥለው ሳምንት አጋማሽ ሲቀጥል ረቡዕ ዕለት ቅዱስ ጊዮርጊስ አዲስ አበባ ላይ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲን ያስተናግዳል። መቐለ ከተማ ወደ አዳማ ተጉዞ ሌላኛውን የዋንጫ ተፎካካሪ አዳማ ከተማ የሚገጥምበት ጨዋታም ከወዲሁ ትልቅ ግምት አግኝቷል።