ደደቢት ጌታቸው ዳዊትን በይፋ የክለቡ አሰልጣኝ አድርጎ ሾሟል

ደደቢት አዲስ የሾማቸውን አሰልጣኞች ዛሬ በኢትዮጵያ ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስተዋውቋል፡፡ ክለቡ ለወንዶቹና ለሴቶቹ ቡድን አዲስ አሰልጣኝ የሾመ ሲሆን የወልዋሎው አሰልጣኝ ጌታቸው ዳዊት የወንዶቹ ዋና አሰልጣኝ ሆነው ሲሾሙ የሴቶቹ ደግሞ ፍሬው ኃ/ገብርኤል ሆነው ተሾመዋል፡፡

ስለ አሰልጣኞቹ

የደደቢት ቴክኒካል ዳይሬክተር አቶ ሚካኤል አምደመስቀል አሰልጣኞቹን ባስተዋወቁበት ወቀት አሰልጣኞቹ የተመረጡበትን ምክንያት አስረድተዋል፡፡ ‹‹ አሰልጣኝ ጌታቸው በተጫዋችነት ከፍተኛ ልምድ ነበረው፡፡ በደደቢትም በረዳት አሰልጣኝነት ሰርቷል፡፡ ስለዚህም የደደቢት አጨዋወት እና ፍልስፍናን ይረዳል፡፡ ከከልባችን አሰራር ጋርም እኩል ይራመዳል ብለን እናስባለን፡፡ የ1ኛ ደረጃ የአሰልጣኝነት ፍቃድ ስላለው የሰጠነውን ኃላፊነት ይወጣል ብለን እናምናለን፡፡ ለአሰልጣኑ የ1 አመት ኮንትራት የተሰጣቸው ሲሆን በሂደት እየታየ ኮንትራታቸው ይታደሳል፡፡ ዳንኤል ፀሃዬ እና ኤልያስ ኢብራሂም ደግሞ ረዳት አሰልጣኝ ሆነው ይቀጥላሉ፡፡ ››

‹‹ አሰልጣኝ ጌታቸውን መቅጠር የፈለግነው የ2007 የውድድር አመት ሲጀመር ነበር፡፡ ነገር ግን ንጉሴ ደስታ ከኛ ጋር በመቀጠላቸው አልተሳካም፡፡ አሁን በቀጥታ አምጥተነዋል፡፡ ስለ ደደቢትም ሆነ ስለ ኢትዮጵያ እግርኳስ በቂ እውቀት አለው ብለን እናስባለን፡፡ ››

michael
ሚካኤል አምደመስቀል

 

‹‹ የፍሬው ኃ/ገብርኤልን በተመለከተ የ2ኛ ደረጃ የማሰልጠን ፍቃድ ያላቸው ሲሆን በስፖርት ሳይንስም የመጀመርያ ዲግሪ አለው፡፡ የስፖርቱን ሳይንስ በሚገባ ስለሚያውቀው የተሰጠውን ኃላፊነት ይጣል ብለን እናስባለን፡፡ በቅርቡም ረዳት አሰልጣኝ ይመደብለታል››

የቡድን ስብስብ

‹‹ በክለቡ ቀሪ ኮንትራት ያላቸው 10 ተጫዋቾች አሉን፡፡ ውላቸውን ያራዘሙት ደግሞ 6 ናቸው፡፡ አዳዲስ 9 ተጫዋቾችን ያስፈረምን ሲሆን አንድ ናይጄርያዊ አጥቂ እና አንድ ጋናዊ አማካይ እናስመጣለን፡፡ በቀጣይ ሳምንትም (ነሃሴ 20) አዳዲሶቹን ያካተተ የቅድመ ውድድር ዝግጅት በደብረ ዘይት እንጀምራለን፡፡ ››

የቀጣይ አመት እቅድ

የደደቢት የ2008 እቅድ በዲሲፕሊንም ሆነ በውጤት ተፎካካሪ መሆን ነው፡፡ በ2007 በሁለቱም ፆታዎች የፀባይ ዋንጫ ተሸላሚ እንደነበርነው ሁሉ በቀጣይ አመትም ይህንን መድገም እንፈልጋለን፡፡ በውጤት ደረጃ ከፍተኛው ዋንጫ ዝቅተኛው ደግሞ እስከ 3ኛ ደረጃ ባለው የማጠናቀቅ እቅድ አለን፡፡

frew d
ፍሬው ኃ/ገብርኤል

 

‹‹ ደደቢትን የማሰልጠን እድል በማግኘቴ ደስተኛ ነኝ ›› ጌታቸው ዳዊት

አዲሱ አሰልጣኝ ጌታቸው ዳዊት ስለ ሹመቱ የተሰማቸው ስሜት እና ቀጣይ ሁኔታዎች አጠር ያለ ማብራርያ ሰጥተዋል፡፡

‹‹ ደደቢትን የማሰልጠን እድል በማግኘቴ ደስተኛ ነኝ፡፡ በእኔ ላይ ትልቅ እምነት ጥለው ኃላፊነት ስለሰጡኝም ደደቢትን አመሰግናለሁ፡፡ ደደቢት ትልቅ ክለብ ነው፡፡ ተፎካካሪ ቡድንና ጠንካራ የአሰልጣኞች ቡድን አለን፡፡ ይህንን ጥንካሬ ይዘን ወደፊ ለመጓዝ ጥረት እናደርጋለን፡፡ ››

‹‹ ከግል ስራ ይልቅ በቡድን ስራ ላይ ትኩረት አደርጋለሁ፡፡ እኔ ከማለት እኛ ማለትን እመርጣለሁ፡፡ ስለዚህ ተጫዋቾችን በጋራ ተከታትለን አስፈርመናል፡፡ ውሳኔዎቹም የሚደረጉት በጋራ ነው፡፡ ››

‹‹ ከብሄራዊ ሊግ ክለብ ስለመጣሁ ብዙዎች እምነት ላይጥሉብኝ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን በብሄራዊ ሊጉ እና ፕሪሚየር ሊጉ መካከል ያለው ልዩነት እምብዛም ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ጠንካራ የአሰልጣኝ ቡድን ስላለን ለመልመድ አልቸገርም፡፡››

ያጋሩ