ሶከር ሜዲካል | የፊፋ የህክምና ኮሚቴ

የህክምናው ዘርፍ በእግርኳሱም ሆነ በሌሎች የስፖርት አይነቶች ውስጥ ያለው ሚና ከጊዜ ወደጊዜ እየጎላ መጥቷል። በተለይ የእግርኳስ ደረጃቸው ከፍተኛ የሆኑ የምዕራብ አውሮፓ ሃገራት ከታዳጊዎች መሠረታዊ ስልጠና አንስተው እስከ ታላላቆቹ ክለቦቻቸው ድረስ ለስፖርት ህክምና እና በስሩ ለሚጠቃለሉ ንዑስ ክፎሎች ትልቅ ስፍራ በመስጠት እየሰሩ ይገኛሉ። ዓለምአቀፉ የእግርኳስ ማህበር (ፊፋ) በአወቃቀሩ ከሚገኙ 9 አብይ ኮሚቴዎች ውስጥ አንዱ የህክምና ኮሚቴ እንዲሆን በማድረግ እግርኳሱን በዘመናዊ የህክምና ቴክኖሎጂ ለመደገፍ፤ እንዲሁም የእግርኳስ ህክምናው ላይ ይበልጥ መሻሻሎች እንዲመጡ እየተጋ ነው።

ከእግርኳሱ ጋር ቁርኝት ያላቸው እና በስፖርት ህክምና እና ተጓዳኝ ዘርፎች ስር ያሉ ርዕሰ ጉዳዮችን የምናነሳበት የሶከር ሜዲካል አምዳችን የዛሬ ትኩረት የፊፋ የህክምና ኮሚቴ አወቃቀር እና ኃላፊነቶች ላይ ይሆናል።

በእግርኳሱ ውስጥ ያሉ ከጤና ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በሙሉ በኃላፊነት የመመምራት ስልጣኑ ያለው የፊፋ የህክምና ኮሚቴ በውስጡ ከ12 የማያንሱ አባላትን ይይዛል። በኮሚቴው ውስጥ በአባልነት የሚሰሩ ግለሰቦች በሙሉ በስፖርት ህክምናው በቂ የትምህርት ዝግጅት ያላቸው እና በተለይ በእግርኳስ ህክምና ላይ ያተኮረ ትምህርት የወሰዱ፤ በተቻለ መጠን በስፖርት ቀዶጥገና፣ ስነ-ምግብ፣ ስነ-ልቦና፣ ፊዚዮቴራፒ፣ ስፖርታዊ ምርምር እና ሌሎች የህክምናው ዘርፎች ውስጥ የሰሩ እንዲሆኑ ይጠበቃል። ይህም በኮሚቴው ስር በእነዚህ ዘርፎች መሠረት በርካታ ንዑስ ኮሚቴዎች እንዲመሰረቱ ያግዛል። ፊፋ ይህንን አወቃቀር ሲተገብር በአባል ፌዴሬሽኖቹ ለሚቋቋሙ ተመሳሳይ ኮሚቴዎች እንደ ምሳሌ እንዲያገለግል መሆኑን ልብ ይሏል።

የፊፋ የህክምና ኮሚቴ ከላይ እንደተገለፀው በእግርኳሱ ውስጥ ያሉ ከጤና ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ጉዳዮች በሙሉ የማስተዳደር ስልጣኑ አለው። በፊፋ የአስተዳደር መመሪያ የኮሚቴውን ኃላፊነቶች በአስር የተለያዩ ክፍሎች ያስቀመጠው ሲሆን ከዚህ እንደሚከተለው ሊጠቃለሉ ይችላሉ።

1. ምክር መለገስ

ህክምናን በተለመከተ ያሉ ሃሳባዊ፣ ተግባራዊ እና የክሊኒክ ጉዳዮች ላይ የህክምና ኮሚቴው ለፊፋ ወይም እገዛውን ለጠየቀው የስፖርታዊ አስተዳደር አካል ምክሩን ይለግሳል። በዚህ ኃላፊነቱ ስር የፊፋ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ለሚወስናቸው ውሳኔዎች፤ ከዚያም አልፎ እስከ ዓለምአቀፉ የስፖርት ገላጋይ ፍርድቤት ድረስ በሚደርሱ ጉዳዮች ላይ ሙያዊ አስተያየቱን በግብዓትነት ያቀርባል።

2. መመሪያዎችን ማርቀቅ

ኮሚቴው ተጫዋቾች፣ አሰልጣኞች እንዲሁም ዳኞች ሊከተሏቸው የሚገቡ የህክምና መመሪያዎችን የማዘጋጀት ኃላፊነት አለበት። አሰልጣኞች እና ሌሎች የቡድን አባላት አካል ብቃት ላይ ያተኮሩ ስልጠናዎችን ለተጫዋቾቻቸው ሲሰጡ አላስፈላጊ ጫና እና ጉዳቶችን ለመከላከል ይረዳቸው ዘንድ የህክምና ኮሚቴው መመሪያን አዘጋጅቷል። ተጫዋቾች የጤና እክል እንዳያጋጥማቸው ከሚከላከሉ መመሪያዎች በተጨማሪ በህክምናው ላይ የተመሰረቱ የተጫዋቾችን የአካል ብቃት፣ ረጅም ጊዜ የመጫወት ብርታት እና የግል ችሎታ እንዲሻሻል የሚያግዙ ጥራዞች በኮሚቴው ይዘጋጃሉ። ይህ በተጫዋቾችን የአመጋገብ ስነ-ስርዓት ዙሪያ የሚወጡ መመሪያዎችንም ይጨምራል።

አልኮል፣ ሲጋራ፣ እና ሌሎች ወደሱስ የሚወስዱ ዕፅ እና መድሃኒቶች በተጫዋቾች ሰውነት ውስጥ የሚያሳድሩት አሉታዊ ተፅዕኖን የሚገልፁ እና ተጫዋቾችም ከነዚህ ደባል ሱሶች እንዲጠበቁ የሚያሳስቡ ፅሁፎች በኮሚቴው ተዘጋጅተው በየጊዜው ይወጣሉ።

3. የውድድሮችን የህክምና ህግ ማዘጋጀት

በፊፋ ስር የሚደረጉ ውድድሮች ላይ ለሚሳተፉ ተጫዋቾች የሚደረገውን የቅድመ ውድድር የጤና ምርመራ በበላይነት የሚመራው የህክምና ኮሚቴው ነው። ከ17 እና ከ20 ዓመት በታች ባለው የዕድሜ እርከን ካሉ ውድድሮች አስቀድሞ የሚደረገውን የዕድሜ ተገቢነት ማረጋገጫ ቴክኒካዊ ዝርዝሮች የህክምና ኮሚቴው ከፊፋ የህክምና ምርምር ቡድን ጋር በመተባበር ያረቀቀ ሲሆን የምርመራዎቹ ተፈፃሚነትንም ያረጋግጣል። ከዚህ በተጨማሪ በውድድሮቹ ላይ በሚደረጉ ጨዋታዎች መኖር የሚገባውን የህክምና መገልገያ ቁሶች፣ የህክምና ባለሞያዎች እና አገልግሎቶች ዝቅተኛ ደረጃ ይወስናል።

4. ጉዳቶችን መመርመር

በተለያዩ ጨዋታዎች ላይ፤ በተለይም በፊፋ እውቅና ባላቸው በሃገራት መሃከል የሚደረጉ ጨዋታዎች ላይ ተጫዋቾች ጉዳት ካጋጠማቸው እና በጉዳቱ ምክኒያት ክለባቸውን ለረጅም ጊዜ ማገልገል ካልቻሉ ክለቦች ከፊፋ የገንዘብ ካሳ ጠይቀው ማግኘት ይችላሉ። በነዚህ ጊዜያትም የተጫዋቾች ጉዳት እና የማገገም ሂደት የሚመረመረው በህክምና ኮሚቴው ነው። ኮሚቴው ጉዳትን ለመከላከል የሚያግዙ እና ካጋጠመም በተሻለ መልኩ ህክምና ማግኘት በሚቻልበት ሂደት ላይ የሚያተኩሩ የተለያዩ መመሪያዎችን ያወጣል።

5. ፀረ-አበረታች መድሃኒት ስራዎች

የፊፋ ፀረ-አበረታች መድሃኒት ክፍል የተለያዩ ህጎችን በሚያረቅበት፣ መድሃኒት ተጠቅመው የተገኙ ስፖርተኞችን በሚመዘግብበት እና በሚከታተልበት፣ እንዲሁም ለዲሲፕሊን ኮሚቴው ለቅጣት ውሳኔ በሚያቀርብበት ሂደት የህክምና ኮሚቴውን እገዛ ያገኛል። ኮሚቴው የፀረ-አበረታች መድሃኒት ላብራቶሪዎች በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች እንዲከፈቱ በመርዳትም ይሰራል።

የህክምና ኮሚቴው ከላይ ከተገለፁት የስራ መደቦች በተጨማሪ የስፖርት ህክምናው ከእግርኳሱ ጋር ይበልጥ እየተቆራኘ በመጣ ቁጥር አድማሱን እያሰፋ በተለያዩ ስራዎች ላይ እየተሳተፈ ይገኛል። በሃገራችን በቅርብ ዓመታት በተለይ በታዳጊዎች እና በወጣቶች ውድድሮች ላይ የሚሳተፉ ተጫዋቾችን የዕድሜ ተገቢነት በማረጋገጥ በኩል የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የህክምና ኮሚቴ ይበል የሚያሰኝ ስራ እየሰራ ቢሆንም ከዚህ ውጪ ባሉ ሃላፊነቶች ላይ ያለው እንቅስቃሴ ግን እምብዛም ነው። እኛም እግርኳሳችንን ዓለም ወደደረሰበት በቴክኖሎጂ የተደገፈ እና ዘመናዊ ጨዋታ ለማስጠጋት የስፖርት ህክምናው ሚና ቀላል ስለማይሆን ይበልጥ ትኩረት ሊደረግበት ይገባል ስንል አስተያየታችንን እንገልፃለን።