ፕሪምየር ሊግ | የ23ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቅድመ ዳሰሳ – ክፍል 1

ባሳለፍነው ሳምንት በተስተካካይ ጨዋታዎች ከተቋረጠበት የቀጠለው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ነገ የ23ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ይስተናገዱበታል። ከነዚህ ጨዋታዎች መሀከል ጅማ ፣ አዳማ እና ሀዋሳ ላይ የሚደረጉትን ሶስት ጨዋታዎች በክፍል አንድ ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳችን ተመልክተናቸዋል።

ጅማ አባ ጅፋር ከ አርባምንጭ ከተማ

የሊጉ መሪ ጅማ አባ ጅፋር በቅርበት ከሚከተሉት ተፎካካሪዎቹ ለመራቅ አርባምንጭ ከተማም በአንድ ነጥብ ልዩነት ብቻ ከወጣበት የወራጅ ቀጠና መልሶ ላለመገኘት እርስ በእርስ ወሳኙን ጨዋታ ጅማ ላይ ያደርጋሉ። ከሊጉ መቋረጥ አስቀድሞ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ነጥብ ተጋርቶ የተመለሰው ጅማ አባ ጅፋር ሜዳው ላይ ያሉ ጨዋታዎችን ለማሸነፍ ሲቸገር አይታይም። በቀሪ ሳምንትታም በሻምፒዮንነት ፉክክሩ ውስጥ ጅማ ላይ ከሚደረጉ ጨዋታዎች ሙሉ ነጥቦችን ለመሰብሰብ ያቀደም ይመስላል። በአንፃሩ ከደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ተነስቶ ከፍ ለማለት ያስቻሉትን ውጤቶች በሙሉ ሜዳው ላይ ያስመዘገበው አርባምንጭ በሊጉ ለመቆየት ከሜዳው ውጪም ውጤት ይዞ መመለስ የግድ ስለሚለው እና የሊጉን መሪ መርታት ከሚያስገኘው የስነልቦና የበላይነት አንፃር በቀላሉ እጅ እንደማይሰጥ ይጠበቃል። 

ባለሜዳው ጅማ አባጅፋር ከጉዳት እና ቅጣት ነፃ የሆነ ሙሉ ስብስቡን ይዞ ለጨዋታው የሚደርስ ሲሆን ጉዳት ላይ የሚገኘው ምንተስኖት አበራ እና በወልዋሎ ዓ.ዩው የኢትዮጵያ ዋንጫ ጨዋታ የቀይ ካርድ የተመለከተው ገዛሀኝ አበራ ጨዋታው የሚያመልጣቸው የአርባምንጭ ተጨዋቾች ናቸው።

የጨዋታው አጠቃላይ መልክ ባለሜዳው የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን ለማግኘት እምብዛም የማይቸገርበት እና እንግዳው ቡድን ደግሞ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን በመጠበቅ ለጥንቅቄ ቅድሚያ የሚሰጥበት እንደሚሆን ይጠበቃል። ፊት ላይ የሚሰለፈው ኦኪኪ አፎላቢንም ሆነ ሁለተኛውን አጥቂ ተመስገን ገ/ኪዳንን በቅብብሎች ለማግኘት ሰፊ ክፍቶተችን ላያገኝ የሚችለው አባ ጅፋር ከዮናስ ገረመው እና ኄኖክ ኢሳያስ በተጨማሪ ይሁን እንዳሻውም ከአሚኑ ነስሩ ጋር በሜዳው ቁመት በመጣመር ለአጥቂ መስመሩ ቀርቦ ከሚያደርገው እንቅስቃሴ የመጨረሻ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር እንደሚሞክር ይገመታል። የቡድኑ የመስመር ተከላካዮች የማጥቃት ስሳትፎ እና ተሻጋሪ ኳሶቻቸውም ለአርባምንጭ የመሀል ተከላካዮች ተጨማሪ የቤት ስራ የመሆን አቅም አላቸው። እነዚህን የማጥቃት መስመሮች በምንተስኖት ምትክ የመሰለፍ ዕድልን ሊያገኝ ከሚችለው አለልኝ አዘነ እና አማኑኤል ጎበና ጥምረት መዝጋት የሚጠበቅበት አርባምንጭ ከተማ ደግሞ የማጥቃት ሽግግሩን ፍጥነት እና የቅብብል ስኬቱን ጥራት በመጨመር የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር በነእንዳለ ከበደ ብቃት ላይ ዕምነቱን ይጥላል። ሆኖም አሁንም ቡድኑ በየሳምንቱ ግብ የሚያስቆጥርለት እና ወጥ የሆነ ብቃት ያለው አጥቂ አለማግኘቱ በቁጥር ካነሱ ሙከራዎች ግቦችን የማግኘት ዕድሉ ፍሬ ላያፈራ እንደሚችል ያሰጋል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– በመጀመሪያው ዙር የተገናኙበት የአርባምንጩ ጨዋታ በአዲስ አዳጊው ጅማ አባ ጅፋር 3-1 አሸናፊነት የተጠናቀቀ ነበር።

– በሁለተኛው ዙር በሜዳው ያደረጋቸውን አራት ጨዋታዎች በሙሉ በድል የተወጣው አባ ጅፋር 9 ግቦችን አስቆጥሮ አንድ ጊዜ ብቻ መረቡ ተደፍሯል።

– ከሜዳው ውጪ አስከፊ ሪከርድ ያለው አርባምንጭ በሁለተኛው ዙር ከሜዳው በወጣባቸው አራት ጨዋታዎች በሙሉ ሲሸነፍ አንድም ጊዜ ግብ ማስቆጠር አልቻለም። 

ዳኛ

– ኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሰ ጨዋታውን በመሀል ዳኝነት ለመምራት ተመድቧል።

       
ሀዋሳ ከተማ ከ ፋሲል ከተማ

በሊጉ ሰንጠረዥ አጋማሽ ተከታታይ ደረጃ ላይ የሚገኙት ሁለቱ ክለቦች ሁነኛ የዋንጫ ተፎካካሪ ለመሆን ተቸግረዋል። በነጥብ ከመሪዎቹ ተስፋ በሚያስቆርጥ መልኩ ባይርቁም በተከታታይ ሙሉ ነጥቦችን መሰብሰብ አለመቻላቸው መሀል ላይ እንዲቆዩ አድርጓውዋል። የመጨረሻ ጨዋታዎቻቸውን በአቻ ውጤት የጨስሱት ሀዋሳ እና ፋሲል ወቅታዊ አቋማውቸውም ተመሳሳይነት የሚታይበት ነው። ከአቻ ውጤቱ ባለፈ በመከላከያ እና ወላይታ ድቻ የደረሰባቸው ከባባድ ሽንፈቶች እንዲሁም በ20ኛው ሳምንት በሜዳቸው ያሳኳቸው ድሎች ሌሎች የሚመሳሰሉባቸው ነጥቦች ናቸው። በመሆኑም ቡድኖቹ በነገው ጨዋታ ከሁለት የውድድር ሳምንታት በኃላ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ እና ከፉክክሩ ርቆ ላለመቀመጥ ጥረት የሚያደርጉበትን ጨዋታ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

የሀዋሳ ከተማዎቹ ዮሐንስ ሴጌቦ እና ቸርነት አወሽ ጉዳት ላይ የሚገኙ ሲሆኑ የጂብሪል አህመድ እና ዳንኤል ደርቤ መድረስም አጠራጣሪ ነው። በፋሲል ከተማ በኩል ደግሞ በጉዳት ለጨዋታው የማይደርሱት የመሀል ተከላካዮቹ ያሬድ ባየህ እና ዓይናለም ኃይለ ናቸው።

ሜዳው ላይ በሚደረጉ ጨዋታዎች ረጅም ደቂቃ በተጋጣሚው ሜዳ ላይ የሚያሳልፈው ሀዋሳ ከተማ ከሚነጠቁ ኳሶች መነሻነት በፍጥነት ወደ ግብ የመድረስ ባህሪን ከተላበሰው ፋሲል ከተማ ጋር የሚገናኝ መሆኑ በጨዋታው እንዲፈተን ሊያደርገው ይችላል። በመሆኑም በታፈሰ ሰለሞን የሚመራው የባለሜዳዎቹ የአማካይ ክፍል መሀል  ሜዳ ላይ ሰፊ የሜዳ ክልል ከሚያካልሉት ያስር ሙገርዋ እና ኄኖክ ገምቴሳን ከመሰሉ ነጣቂ የመሀል ሜዳ ተሰላፊዎች የሚደርስበትን ጫና ተቋቁሞ ለመስመር አጥቂዎቹ ቀጥተኛ ሩጫዎች የተመቹ ኳሶችን ማድረስ ይጠበቅበታል። በዛው ልክ ደግሞ የፋሲል ከተማ የመስመር አጥቂዎች በሁለቱም ኮሪደሮች ለድንገተኛ ጥቃት የተመቸ አቋቋምን በመያዝ የሚደርሷቸውን ኳሶች ወደ ግብ ዕድልነት ለመቀየር የማጥቃት ባህሪ ካላቸው የተጋጣሚያቸው የመስመር ተከላካዮች ጀርባ ለመግባት ዝግጁ መሆን ይገባቸዋል። በጥቅሉ ከሜዳው ምቹነት እና ከቡድኖቹ የማጥቃት ፍላጎት አንፃርም ጭምር ከፍ ያለ ፍጥነት ያለው እና በርከት ያሉ ሙከራዎች የሚደረጉበት ጨዋታ እንደሚሆን ይገመታል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ሁለቱ ቡድኖች አምና በመጀመርያው ዙር ጎንደር ላይ ተገናኝተው 1-1 ሲለያዩ በሁለተኛው ዙር ሀዋሳ ላይ ሀዋሳ ከተማ 2-0 አሸንፏል። በያዝነው የውድድር አመት አንድኛ ዙር ደግሞ ጎንደር ላይ 2-2 ተለያይተዋል።

– ሀዋሳ ከተማ ሜዳው ላይ ካስተናገዳቸው የመጨረሻ አምስት ጨዋታዎች አራቱን ሲያሸንፍ አንዴ ደግሞ ሽንፈት ገጥሞታል። 

– ፋሲል ከተማ ደግሞ በተቃራውኒ ከሜዳው ውጪ ካደረጋቸው አምስት የመጨረሻ ጨዋታዎች በአራቱ ተሸንፎ በአንዱ ድል ቀንቶታትል።

ዳኛ

– ጨዋታውን በመሀል ዳኝነት የሚመራው ፌደራል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ ነው።

 አዳማ ከተማ ከ መቐለ ከተማ

 
በደረጃ ሰንጠረዡ በእኩል ነጥብ በግብ ልዩነት ተበላጠጥው ሶስተኛ እና አራተኛ የሆኑትን ክለቦች የሚያገናኘው ይህ ጨዋታ በዚህ ሳምንት ከሚደረጉ ጨዋታዎች መሀከል ከፍተኛ ግምት የተቸረው ሆኗል። ከምንም በላይ በሜዳው የረጅም ጊዜ ያለመሸነፍ ሪከርድ ያለው እና ከሜዳው ውጪ እጅግ ጠንካራ የሆነ ቡድን የሚገናኙበት በመሆኑ ብርቱ የመሸነፍ ፉክክር እንደሚደረግበት ይጠበቃል። ከበላያቸው ያሉት ሁለት ክለቦች የሚያስመዘግቡት ውጤት እንዳለ ሆኖ ወደ ላይ ከፍ ለማለት ከሚያደርትጉት ፍልሚያ ባሻገር አዳማ ከተማ ሁለተኛ ተከታታይ ድል ለማሳካት መቐለ ከተማ ደግሞ ከቅዱስ ጊዮርጊሱ የአቻ ውጤት ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የሚጫወቱ ይሆናል። 

የጉዳት ዜና ያልተሰማበት አዳማ ከተማ በዚህ ጨዋታ መጠቀም የማይችለው ቅጣት ላይ የሚገኘው ሲሳይ ቶሊን ብቻ ይሆናል። በመቐለ ከተማ በኩል ግን የፊት አጥቂው ቢስማርክ ኦፖንግ በጉዳት ከጨዋታው ውጪ መሆኑ ተሰምቷል። 

በዚህ ጨዋታ ዋነኛ ትኩረት የሚስበው መሀል ሜዳ ላይ የሚጠበቀው ፍልሚያ ነው። በዐመለ ሚልኪያስ እና ሚካኤል ደስታ ጥምረት መሀል ለመሀል ለሚሰነዘርበት ጥቃት ክፍተት የማይሰጠው የመቐለ አማካይ ክፍል በልምድ እና በተሰጥኦ ሀብታም ከሆነው የአዳማ አማካይ ሙስመር ጋር ይገናኛል። የሜዳውን ስፋት በሚገባ ለመጠቀም እና በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች አሸናፊ በመሆን ወደተጋጣሚ ሳጥን ለመግባት ወሳኝ የሆነው በረከት ደስታም እምብዛም ለማጥቃት ቦታቸውን ከማይለቁት የመቐለ የመስመር ተከላካዮች ጋር ይፋጠጣል። ተጋጣሚያቸው ካለው ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት አንፃር ከሁለቱ አማካዮች ግራ እና ቀኝ ያሉትን ቦታዎች መጠቀም እና ከሳጥን ውጪ በቀጥታ የሚሞከሩ ኳሶች ላይ ትኩረት ማድረግ የሚኖርባቸው አዳማዎች ራሳቸውን ለመልሶ ማጥቃት አለማጋለጥም ይጠበቅባቸዋል። መቐለዎች ቢስማርክን ቢያጡም እጅግ ወሳኝ የሆነው አጥቂያቸው አማኑኤል ገ/ሚካኤል ጀርባውን ለጎል ሳይሰጥ በአዳማ ሳጥን ውስጥ ሆኖ ኳሶችን እንዲያገኝ ማድረግ ተጠቃሚ ያደርጋቸዋል። በዛው ልክ ደግሞ ግዙፎቹ የአዳማ ተከላካዮች ኳስ አጥቂው እግር ስር ከመግባቷ በፊት አስቀድመው ርምጃ መውሰድ ያስፈልጋቸዋል። በዳዋ ሆቴሳ እና በመቐለ ተከላካዮች መሀል የሚኖረው ፍልሚያም ተጠባቂ ሲሆን ጨዋታው በተለያዩ የሜዳው ክፍሎች ላይ ወሳኝ የአንድ ለአንድ ግንኙነቶችም የሚታዩበት ይሆናል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– በስምንተኛ ሳምንት መርሀ ግብር በሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙበት የመቐለው ጨዋታ 1-1 የተጠናቀቀ ነበር።

– አዳማ ከተማ በሜዳው ከ11 ጨዋታዎች ግብ ሳያስቆጥር የወጣው በሁለት ጨዋታዎች ብቻ ሲሆን መቐለ ከተማ ደግሞ ከሜዳው ውጪ ካደረጋቸው 10 ጨዋታዎች በአምስቱ ግብ አልቀናውም።

– በሜዳው ከፍተኛ ነጥብ በመሰብሰብ ከሊጉ ቀዳሚ የሆነው አዳማ ከተማ በጠቅላለው ከሰበሰባቸው 36 ነጥቦች 25ቱን አዳማ ላይ ነበር ያገኘው።

– ከሜዳው ውጪ በሰበሰባቸው ነጥቦች ከሊጉ ክለቦች የበላይ የሆነው መቐለ ከአጠቃላይ 36 ነጥቦቹን 16ቱን ያገኘው ከመቐለ ውጪ ነበር።

ዳኛ

– ፌደራል ዳኛ ኢብራሂም አጋዥ ጨዋታውን በመሀል ዳኝነት ለመምራት ተመድቧል።