በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 23ኛ ሳምንት አዲስ አበባ ላይ በ09፡00 የጀመረው ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስን እና ወልዋሎ ዓ.ዩን አገናኝቶ በአሜ መሀመድ ብቸኛ ጎል በባለሜዳዎቹ አሸናፊነት ተጠናቋል።
ሁለቱም ቡድኖች ከመጨረሻው የሊጉ ጨዋታቸው የአንድ ተጨዋች ቅያሪን በማድረግ ነበር ጨዋታውን የጀመሩት። ቅዱስ ጊዮርጊስ በተስተካካይ ጨዋታ መቐለ ላይ ወደ ሜዳ ይዞ ከገባው ቡድኑ ውስጥ ከቅጣት የተመለሰው አቡበከር ሳኒን በበሀይሉ አሰፋ ምትክ ሲያሰልፍ ወልዋሎ ዓ.ዩ ደግሞ በተቋረጠው የመከላከያ ጨዋታ ቅጣት የተላለፈበት ግብጠባቂው በረከት አማረን በዮሀንስ ሽኩር ተክቷል።
በመጀመሪያዎቹ አምስት ደቂቃዎች ሁለት ጊዜ አስደንጋጭ የሚባሉ ሙከራዎችን ያስመለከተን የመጀመሪያው አጋማሽ በዛው ፍጥነት የቀጠለ አልነበረም። በ1ኛው ደቂቃ አሜ መሀመድ የወልዋሎን መሀል ተከላካይ ተስፋዬ ዲባባን አታሎ እና ነፃ ሆኖ ያደረገው ሙከራ ኢላማውን ቢጠብቅም ግብ ሳይሆን ቀርቷል። ከደቂቃዎች በኃላ ደግሞ በግራ መስመር ሰብሮ የገባው ፕሪንስ ሰቨሪንሆ ወደ ጎል የላካት ኳስ የተጠቀመባት አላገኘችም እንጂ ወደ ግብ መቀየር የምትችል ጥሩ አጋጣሚ ነበረች። ቅዱስ ጊዮርጊሶች በዋነኝነት የመስመር አጥቂዎቻቸውን መዳረሻ ካደረጉ ኳሶች ጥቃት ለመሰንዘር ወልዋሎዎች ደግሞ በተለመደው አጨዋወታቸው በአጫጭር በቅብብሎች ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ለመድረስ የሚያደርጉትን ሙከራ ያስመለከቱን ቀጣይ ደቂቃዎች ግን ሙከራዎች በብዛት የተደረጉባቸው አልነበሩም። ይልቁንም መሀል ሜዳ ላይ የታጨቀ የተጨዋቾች አቋቋም ነገሮችን ለሁለቱም ቀላል አላደረገላቸውም።
21ኛው ደቂቃ ላይ አብዱልከሪም ኒኪማ ከሳጥን ውጪ አክርሮ የሞከረውን ኳስ የወልዋሎ ተከላካዮች ሲደረቡ አግኝቶ ሁለተኛ ሙከራ ያደረገው አሜ መሀመድ ቅዱስ ጊዮርጊስን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል። ዮሀንስ ኳሷን ለማዳን ተቃርቦ የነበረ ቢሆንም ጥረቱ ከንክኪ ያለፈ አልነበረም። ከግቡ መቆጠር በኃላ በነበረው እንቅስቃሴ የተሻለ የመጫወቻ ክፍተቶች እና የተረጋጉ ቅብብሎችን በሁለቱም ቡድኖች በኩል መመልከት ቢቻልም የግብ ሙከራዎችን በማድረግም ሆነ በእንቅስቃሴ ተጋጣሚን ከማስጨነቅ አንፃር ቅዱስ ጊዮርጊሶች የተሻሉ ነበሩ። በተለይም ሙሉአለም እና ናትናኤል የወልዋሎን አማካዮች በመቆጣጠር ቡድኑ ከሚቀማቸው ኳሶች በቶሎ ወደ ግብ እንዲደርስ ጥሩ አስተዋፅኦ አበርክተዋል። በዚህም ከ25ኛው እስከ 30ኛው ደቂቃ ድረስ ቅዱስ ጊዮርጊሶች አቡበከር ከሳጥን ውስጥ መሬት ለመሬት ወደ ውስጥ በላከው ፣ ሙሉአለም ከሳጥን ጠርዝ ላይ ሞክሮት በዮሀንስ በታየዘበት እና መሀሪ መና ከግራ መስመር ወደ ውስጥ አሻምቶት አሜ መሀመድ ሳይደርስበት በቀረው ኳሶች የተሻለ የግብ ዕድሎችን ፈጥረዋል።
የዋለልኝ ገብሬ እና አፈወርቅ ኃይሉ ጥምረት በቅዱስ ጊዮርጊሶች ሰው በሰው የመያዝ ዘዴ ፍሬ እንዳያፈራ የሆነባቸው እና ከግባቸው ኳስ ለመጀመር ሲጥሩ የቅብብል አማራጮቻቸው የተያዙባቸው ወልዋሎዎች የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን አሳክቶ ሙከራዎችን ለማድረግ ያሰቡት መንገድ ስኬታማ አልሆነላቸውም። የተከላካይ አማካዩ ብርሀኑ አሻሞ እና ከበስተዋላው ያሉት ተከላካዮች ጨዋታን ከጥልቅ ቦታዎች ለማስጀመር ሲቸገሩ ተስተውለዋል። ከዛ ይልቅ በእጅጉ ወደ መሀል ሜዳ ከተተጋው የጊዮርጊስ የተከላካይ ክፍል ጀርባ ለመግባት በመጨረሻዎቹ አምስት ደቂቃዎች ያደረጉት ጥረት የተሻለ ነበር። በዚህ ሂደት ውስጥ ቡድኑ ከፈጠረው የመጨረሻ የግብ ዕድል ፕሪንስ ከሪቻርድ ኦዶንጎ የደረሰውን ኳስ ይዞ ከአብዱልከሪም መሀመድ ጀርባ መግባት ቢችልም ወደ ውስጥ ለማሻማት ያደረገው ጥረት ግን ውጤታማ አልነበረም።
የሁለተኛው አጋማሽ በአመዛኙ ከቆሙ ኳሶች በሚደረጉ ሙከራዎች የተጀመረ ነበር። ወደ ማዕዘን መምቻው የቀረቡት የቅጣት ምቶች ግን በሁለቱም በኩል ወደ ጥሩ የግብ ዕድሎች የተቀየሩ አልነበሩም። ሆኖም በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ኦስካር ታቫሬዝ ከእንየው ቀምቶ ያደረገው ሙከራ እና የወልዋሎው አፈወርቅ ኃይሉ ከሳጥን ውጪ በቀጥታ መቶት በግቡ አግዳሚ የወጣው ሙከራ ተጠቃሽ ነበሩ። በእንቅስቃሴ ደረጃ ከመጀመሪያው ተነቃቅተው የቀረቡት ወልዋሎዎች የአማካይ መስመር ተጨዋቾቻቸው ነፃነት ተሻሽሎ በታየባቸው የመጀመሪያዎቹ 29 ደቂቃዎች የፕሪንስ ሰቨሪንሆ ሚና ጎልቶ ይታይ ነበር። ያለኳስ ለአማካይ ክፍሉ ቀርቦ የቁጥር ብልጫ ለማስገኘት ጥረት ያደርግ የነበረው ፕሪንስ ከኳስ ጋር ደግሞ በግራ መስመር መሀሪ መናን በተደጋጋሚ ሲፈትን ተስተውሏል። ፕሪንስ ከመሀል አጥቂው ሪቻርድ ኦዶንጎ እና አፈወርቅ ኃይሉ ጋር የፈጠረው ጥምረት በተደጋጋሚ በጊዮርጊስ ሳጥን ውስጥ እንዲገኝ አድርገውት የነበረ ቢሆንም ያለቀለትን የግብ ዕድል መፍጠር አልቻለም። ወልዋሎ አግኝቶት የነበረው የጨዋታ የበላይነትም ደቂቃዎች ሲገፉ እና ዝናቡ ሲበረታ እየቀዘቀዘ መጥቷል።
የተጋጣሚያቸው የቀኝ መስመር ጥቃት ጫና ውስጥ ከቷቸው የነበሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ወደ ራሳቸው የግብ ክልል ለማፈግፈግ ቢገደዱም በዛው መጠን ደግሞ የወልዋሎ የኃላ መስመር ወደ ፊት መቅረቡን ተከትሎ ንፁህ የሚባሉ የመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን ማግኘት ችለዋል። ቡድኑ እጅግ ለጎል በቀረበበት የ57ኛው ደቂቃ ሙከራ ግን ሳላዲን ባርጌቾ ከማዕዘን የመጣችን ኳስ በግንባሩ ሞክሮ ኳስን ከዮሀንስ ጀርባ ቢያሳልፍም አፈወርቅ ከመስመር ላይ አውጥቶበታል። ከዚህ ውጪ ግን ቅዱስ ጊዮርጊሶች ያገኟቸው ንፁህ ከሚባሉ የመልሶ ማጥቃት ቅፅበቶች የተገኙ ሙከራዎች ወደ ግብ ሳይቀየሩ ቀርተዋል። ከነዚህ ውስጥ 78ኛው ደቂቃ ላይ አዳነ ግርማ ለአማራ ማሌ አሳልፎለት አማራ ከሳጥኑ መግቢያ ላይ አክርሮ መቶት ወደ ውጪ የወጣው እንዲሁም 89ኛው ደቂቃ ላይ ከቅያሪዎች በኃላ ወደ ቀኝ መስመር አጥቂነት የሄደው አብዱልከሪም ኒኪማ ወደ ውስጥ ይሻማው እና አማራ ያልደረሰበት እንዲሁም በተጨማሪ ደቂቃ ራሱ ኒኪማ ያደረገው ኢላማውን የጠበቀ የርቀት ሙከራ በባለሜዳዎቹ በኩል ተጠቃሽ ነበሩ። ሆኖም ከዝናቡ መክበድ ጋር መቀዛቀዝ የታየበት ጨዋታ ተጨማሪ ግብ ሳያስተናግድ በቅዱስ ጊዮርጊስ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
የአሰልጣኞች አስተያየት
አሰልጣኝ ቫስ ፒንቶ – ቅዱስ ጊዮርጊስ
በሁለቱ አጋማሾች ጨዋታው የተለያየ መልክ ነበረው። በመጀመሪያው አጋማሽ እጅግ የተሻልን ነበር ፤ ከአንድ በላይ ጎል ለማስቆጠር የሚረዱ የግብ ዕድሎችንም ፈጥረን ነበር። በሁለተኛው አጋማሽም ዕድሎችን ብንፈጥርም በዝናቡም መበርታት ሳቢያ እንፈጥረው የነበረው ጫና ቀንሷል። ለተጋጣሚያችንም የመጫወቻ ክፍተት ሰጥተን ነበር። በጥቅሉ ግን ጥሩ ነበርን በማሸነፋችንም ተደስተናል።
አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም – ወልዋሎ ዓ.ዩ
ተረጋግተን ቡድናችንን እየሰራን ጨዋታውን አልጠበቅንም። በተጨዋቾቼ አዕምሮ ላይ ብዙ ጉዳቶች ነበሩ። የመጨረሻውን ውሳኔም ለጨዋታው አንድ ቀን ሲቀረው ነበር የሰማነው። በመሆኑም ቡድኑን ለማዘጋጀት ተቸግረን ነበር። ጨዋታው ግን ተመጣጣኝ ነበር ፤ ተጨዋቾቻችንም አቅማቸው የፈቀደውን አድርገዋል። ሆኖም በተደረበው ኳስ ጎል ሊገባብን ችሏል። በሁለተኛው አጋማሽ ግን የተሻለ ነገር ለመስራት ሞክረናል። በቀሪዎቹ ጨዋታዎች ቡድናችንን በሊጉ ለማቆየት እንሰራለን።