የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 23ኛ ሳምንት መርሃግብር ዛሬ ሲካሄድ በቅጣት ምክንያት የሜዳው ሁለተኛ ጨዋታውን በሰበታ ስታድየም ያደረገው ወልዲያን ከኢትዮጽያ ቡና ያገናኘው የ09:00 ፍልሚያ በኢትዮጵያ ቡና 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ወልዲያ በኢትዮጵያ ዋንጫ በዛሬው ተጋጣሚው ኢትዮጵያ ቡና በመለያ ምቶች ከተሸነፈው ቡድን የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ግብ ጠባቂው ደረጄ አለሙን በቤሊንጋ ኤኖህ፣ በአማካይ ቦታ ላይ ከቅጣት የተመለሰው ምንያህል ተሾመ በሐብታሙ ሸዋለም ምትክ ወደ ሜዳ አስገብቷል። ኢትዮጵያ ቡና በበኩሉ ከኢትዮጽያ ዋንጫው ጨዋታ ስብስቡ መካከል ተከላካዩ ትዕግስቱ አበራን በቶማስ ስምረቱ እንዲሁም አማካዮቹ አክሊሉ ዋለለኝ እና ኤልያስ ማሞን በማሳረፍ ሳምሶን ጥላሁን እና አዲስ ፍሰሀ (ለመጀመርያ ጊዜ) የመጀመሪያ አሰላለፍ ዕድል ሰጥቷቸዋል።
በመጀመሪያዎቹ አምስት ደቂቃዎች ውስጥ ምንም አይነት የግብ ሙከራ ያላደረጉት ሁለቱ ቡድኖች ኳስን በመሀል ሜዳ በማንሸራሸር እና ከግብ እስከ ግብ በሚለጉ ኳሶች ያሳለፉ ሲሆን በ7ኛው ደቂቃ ከተለመደው የአሰላለፍ ሚና ውጭ በቀኝ መስመር የተጫወተው ቢያድግልኝ በቀኝ በኩል እየገፋ የወሰደውን ኳስ የመጀመሪያው ቀላል የግብ ሙከራ አድርጎል። በተቃራኒው አቅጣጫ ደግሞ ከንታምቢ ከርቀት የተሻገረውን ኳስ ነፃ አቋቋም ላይ የነበረው ሳኑሚ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። በ11ኛው ደቂቃ ዳንኤል ደምሴ ከመሀል ሜዳ ኳስ ለማውጣት ሲል የመታው ኳስ በቡና ተጨዋች ተደርቦ ወደወልድያ የግብ ክልል ሲያመራ ተከላካዩ ብርሃኔ በግንባሩ በመግጨት ለግብ ጠባቂው ለማቀበል ቢሞክርም ከተከላካዩ ጀርባ የነበረው አቡበከር ናስር ኳሷ ላይ በመድረስ ወደ ግብነት ለውጦ ኢትዮጵያ ቡናን ቀዳሚ አድርጓል።
የተቆጠረባቸውን ጎል በፍጥነት ለማካካስ ጥረት ማድረግ የጀመሩት ወልድያዎች በመስፍን ኪዳኔ ለግብ የቀረበ ሙከራ ሲያደርጉ በ16ኛው ደቂቃ ያሬድ ሀሰን በቀኝ መስመር እየገፋ የገባውን ኳስ ወደ ግብ አክርሮ ቢመታውም ሀሪሰን አድኖበታል። ከ20ኛው ደቂቃ በኋላ መልሶ የተቀዛቀዘው ጨዋታ እስከ እረፍት ድረስ ምንም አይነት የግብ ሙከራ ሳይከናውንበት ቀርቷል። በ28ኛው ደቂቃ የወልዲያው ተከላካይ ብርሃኔ በመጎዳቱ በምትኩ አልሳዲቅ አልማሒ ወደ ሜዳ ከገባበት እና ቅያሪውን ተከትሎ ቢያድግልኝ ወደ መሀል ተከላካይነት ከተመለሰበት ክስተት ውጪም በእነዚህ ደቂቃዎች ውስጥ የሚጠቀስ ክስተት አልነበረም።
በኢትዮጽያ ቡና መሪነት ወደ መልበሻ ክፍል ያመሩት ሁለቱ ቡድኖች ከዕረፍት መልስ የተሻለ ፉክክር ቢያደርጉም የበላይነቱ የግብ እድሎችን በአግባቡ በመጠቀም ረገድ ስኬታማ ወደነበረው ኢትዮጵያ ቡና አጋድሏል። በ47ኛው ደቂቃ ላይ አንዱዓለም ንጉሴ ከርቀት የመታው ኳስ በግቡ ቀኝ መስመር የወጣችበት የሁለተኛው አጋማሽ የመጀመርያ ሙከራ የነበረ ሲሆን በ55ኛው ደቂቃ ሚኪያስ መኮንን ያሻገረውን ኳስ በነፃ አቋቋም ላይ የነበረው ሳኑሚ ኳስ ወደግብ አክርሮ በመምታት ለኢትዮጽያ ቡና ሁለተኛ ጎል አስቆጥሯል። ከግቡ በኃላ የተነቃቁት ቡናዋች በኳስ ቁጥጥር የተሻሉ የነበሩ ሲሆን ከ10 ደቂቃዎች በኋላም ሦስተኛውን ጎል ማስቆጠር ችለዋል። በ65ኛው ደቂቃ ሳምሶን ጥላሁን በተጫዋቾች መሐል ያሾለከለትን ኳስ ሳኑሚ ይዞ በመግባት ወደግብ አክርሮ ሲመተመው ተከላካዩ አዳሙ መሐመድ ለማውጣት ቢሞክርም ኳስ አቅጣጫውን ለውጣ ወደ ግብነት ተለውጣለች።
ከግቡ መቆጠር በኋላ የግብ ልዩነቱን ለማጥበብ ወደፊት እየተሳቡ ሲጫወቱ የነበሩት ወልዲያዎች በሒደቱ የተከላካይ ክፍላቸው ለተጨማሪ ግብ ተጋልጦ ነበር። በ69ኛው ደቂቃ ንታምቢ በረጅሙ ለሚኪያስ መኮንን ያሻገረለትን ኳስ ግብ ጠባቂው ቀድሞ በመውጣት ያዳነበት፣ በ73ኛው ደቂቃ እያሱ ታምሩ ከግብ ጠባቂው ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ቤሌንጋን ለማለፍ ሲሞክር የተጨናገፈበት፣ በ78ኛው ደቂቃ ሚኪያስ መኮንን ከኤልያስ ማሞ ያገኘውን ኳስ አዳሙ እና ግብ ጠባቂውንም ማለፍ ቢችልም ኳስ በመርዘሙ ስይደርስበት የቀረው እንዲሁም በ84ኛው ደቂቃ አቡበከር የተሻረገለትን ኳስ ሳይደርስበት ቤሊንጋ ቀድሞ ያወጣበት ሙከራዎች ኢትዮጵያ ቡና በተጋለጠው የተከላካይ መስመር ተጠቅሞ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ላደረገው ጥረት ማሳያዎች ነበሩ። በተቃራኒው ወልዲያዎች ውጤት ለመቀልበስ የሚያስችለ ተደጋጋሚ ሙከራዎች ማድረግ አልቻሉም። በ83ኛው ደቂቃ መስፍን ኪዳኔ ይዞ ወደ 16 ክልል ውስጥ ሲገባ ንታምቢ ደርሶ ያገደው እና በ90ኛው ደቂቃ ኤደም በግንባሩ የገጨውን ኳስ ሀሪሰን ያዳነበት ብቸኛ ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ።
ጨዋታው በዚህ መልኩ በኢትዮጵያ ቡና 3-0 አሸናፊነት ሲጠናቀቅ ኢንተርናሽናል ዳኛ ብሩክ የማነብርሃን በአግባቡ ጨዋታውን በመምራት አጠናቀዋል። በውጤቱ መሠረትም ኢትዮጵያ ቡና ነጥቡን 36 በማድረስ ወደ 4ኛ ከፍ ሲል ወልዲያ በ20 ነጥቦች በሰንጠረዡ ወለል ላይ ለመቀመጥ ተገዷል።