በ23ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አዳማ አበበ በቂላ ስታዲየም ላይ የተደረገውን ጨዋታ መቐለ ከተማ በሜዳው አይበገሬ የነበረውን አዳማ ከተማን 2-0 አሸንፏል፡፡ አዳማ ከተማ በሚያዚያ 2008 በኢትዮጵያ ቡና ከተሸነፈ በኃላ ከ2 ዓመታት በላይ ይዞ የቆየውንየ በሜዳው ያለመሸነፍ ሪከርድ ዛሬ ከሰዓት ተገትቷል፡፡
የአዳማ ከተማ የቀድሞ ተጫዋች አሸናፊ ክለቡ እና ደጋፊዎች ያዘጋጁትን ሽልማት እና መለያ በማስጠት ነበር ጨዋታው የተጀመረው፡፡ የአዳማ ከተማ ቀጥተኛ አጨዋወት እና እምብዛም ክፍተቶች የማይሰጠው የመቐለ ከተማ አደረጃጀት በጨዋታው ላይ እንደሚታይ የተጠበቀ ነበር፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽም አነስተኛ ቁጥር ያላቸው የግብ እድሎች እንዲፈጠሩ ያደረገው የሁለቱ ቡድኖች አጨዋወት በመሃል ሜዳ መገደቡ እና በማጠቃቱ ወረዳ ላይ የሚፈጠሩ እድሎች ትንሽ በመሆናቸው ነበር፡፡ ጨዋታው በተጀመረ በ7ኛ ደቂቃ ሱራፌል ዳኛቸው ከመሃል ያሾለከለትን ኳስ ቡልቻ ሹራ ከመጠቀሙ በፊት ጋናዊው አሞስ አቼምፖ ደርሶ አውጥቶበታል፡፡ ከዚህኛው እድል በኃላ አዳማዎች በተደጋጋሚ በከነዓን ማርክነህ እና ሱራፌል ፈጣን እንቅስቃ ወደ ግብ የሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች በቀር እንደቡድን ስኬታማ የማጥቃት ሽግግር አይታይባቸውም ነበር፡፡
በአንፃሩ አደጋዎችን እንዳይፈጠሩበት ክፍተቶች ባመስጠት ጠንካራ የነበሩት እንግዶቹ በ26ኛው ደቂቃ በግራ መስመር የተገኘውን ቅጣት ምት አማኑኤል ገብረሚካኤል አሻምቶ የአዳማ ከተማ ተከላካዮች ሳይዙት ነፃ የነበረው ያሬድ ከበድ በግንባሩ በመግጨት መቐለን መሪ ማድረግ ችሏል፡፡ ያልተጠበቀ መሪነትን የጨበጡት እንግዶቹ በራስ መተማመናቸው እያደገ ሲመጣ ባለሜዳዎቹ በበኩላቸው ቀሪዎቹን የአጋማሹን ደቂቃዎች በጥሩ ብልጫ አጠናቀዋል፡፡ ሆኖም በረከት ደስታ ከሳጥን ውጪ አክርሮ መቶ ወደ ውጪ ከወጣበት ሙከራ በስተቀር ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ሙሉ 45 ደቂቃውን ሳያደርጉ የመጀመሪያው 45 ተጠናቋል፡፡
በሁለተኛው 45 የመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ላይ ኤፍሬም ዘካሪያስ እና ኮትዲቯራዊውን ኢስማኤል ሳንጋሪ ቀይረው ያስገቡት አዳማዎች የመሃል ሜዳ ብልጫን በመውሰድ የግብ እድሎችን መፍጠር ዋነኛ አላማቸውን ነበር፡፡ ነገር ግን እምብዛም ወደ ሜዳው የመሃል ክፍል ተጠግቶ የማይጫወተው የመቐለ የተከላይ ክፍል እና ኳስን በተጋጣሚው ሜዳ አፍኖ በማስቀረት የተዋጣለት የነበረው የአማካይ ክፍሉ ጨዋታውን ለባለሜዳዎቹ አስቸጋሪ እንዲሆን አድርገውታል፡፡ በረከት ከሳጥኑ ውጪ ያገኘውን ኳስ በቀጥታ ሞክሮ በግብ አናት ወደ ውጪ ሲወጣበት በአንፃሩ መቐለዎች በጋቶች ፓኖም እና ፉሴኒ ኑሁ አማካኝነት ሁለት ያልተሳኩ ሙከራዎችን ከርቀት አድርገዋል፡፡ በ66ኛው ደቂቃ ዳዋ ሆቴሳ የመታውን ቅጣት ምት የመቐለው ግብ ጠባቂ ፊሊፕ ኦቮኖ በቀላሉ ሲይዝበት በ71ኛው ደቂቃ አዳማዎች አቻ የመሆን እድላቸውን አበላሽተዋል፡፡ በሳጥን ውስጥ ሳይጠበቅ ከነዓን ኳስ ቢያገኝም ኢቮኖን ለማለፍ በመሞከሩ ኳስ ወደ ውጪ ወጥታለች፡፡ ከዚህ አስቆጪ እድል በኃላ እንግዶቹ በአማኑኤል፣ ሚካኤል ደስታ እና ጋቶች ጥምረት ያገኙትን እድል ኮንጎዊው ጃኮብ ፔንዜ ግብ ከመሆኑ በፊት ይዞታል፡፡
በ79ኛው ደቂቃ በመልሶ ማጥቃት አማኑኤል ከቀኝ መስመር ያሻገረለትን ኳስ ተቀይሮ የገባው ካርሎስ ዳምጠው ከግቡ አፋፍ አግኝቶ ቢሞክርም ፔንዜ በድንቅ ሁኔታ አምክኖታል፡፡ የእንግዶቹ የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት እየተጠናከረ መጥቶ ከደቂቃ በኃላ መድሃኔ ታደሰ ከተመሳሳይ መስመር ያሸገረውን ኳስ ምኞት ደበበ ደርሶ ወደ ውጪ አውጥቷል፡፡ በ84ኛው ደቂቃ ለሶስተኛ ግዜ በቀኝ መስመር ኳስን ይዘው ወደ አዳማ የግብ ክልል የደረሱት መቐለዎች አማኑኤል በቀላሉ ባስቆጠራት ግብ 2-0 መምራት ችለዋል፡፡ መድሃኔ ለአማኑኤል ኳስ ግብ እንድትሆን አመቻችቶ በማቀበል ትልቁን ሚና ተጫውቷል፡፡
ጨዋታው ከዚህች ግብ በኃላ የተጠናቀቀ ሲመስል አዳማዎች በመጨረሻው ደቂቃ ላይ የዳዋ ቅጣት ምት ሙከራን ኢቮኖ ያዳነው ብቻ ለግብነት የቀረበ ሙከራቸው ነበረች፡፡ ጨዋታውም በመቐለ ከተማ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
ድሉን ተከትሎ መቐለ ከተማ በ39 ነጥብ 3ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ አዳማ ከተማ በ36 ነጥብ በኢትዮጵያ ቡና በግብ ክፍያ ተበልጦ 5ኛ ደረጃ ላይ ተገኝቷል፡፡
የአሰልጣኞች አስተያየት
የአዳማ ከተማ ምክትል አሰልጣኝ አስቻለው ሀ/ሚካኤል
እንደምታውቁት ይህ እግርኳስ ነው፡፡ ያለመሸነፍ ሪከርዳችን ጥሩ ሆኖ ሳለ በዛሬው ጨዋታ ሽንፈት ተጎጭትናል፡፡ በሽንፈቱ ተስተካክለን እንመጣለን፡፡ ጨዋታው የተመጣጠነ ነው፡፡ ትንሽ መዘናጋት ነው ውጤት እንድናጣ ያደረገን፡፡ ጨዋታው ግን ተመጣጣኝ ነበር፡፡ ለዋንጫው ገና 7 ጨዋታ ይቀራል፡፡ ስለዚህ ይህ ምንም ተፅዕኖ የለውም፡፡ እስከመጨረሻው እንጓዛለን ብለን ነው ተስፋ የምናደርገው፡፡
የመቐለ ከተማ አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ
ጨዋታው በስርዓት በኩል ጥሩ ዲስፕሊን የተመለከትንበት ነው፡፡ እኛ በፍላጎት የበለጥናቸው ይመስለኛል፡፡ ብዙ የመንቀሳቀስ እና የማሸነፍ ፍላጎቱ እኛ የተሻልን ነበርን፡፡ አዳማ በሜዳው ሁለት አመት ሙሉ አለመሸነፉን አሁን ገና ነው የማውቀው ፤ አላውቅም ነበር፡፡ እንግዲህ ይህ ለቡድኑ ሌላ ነገር ይሆናል። እኛ ግን ውጤቱን ነበር የምንፈልገው፡፡ የምንፈልገውን ውጤት አግኝተናል፡፡ የአዳማ አጨዋወት ቀጥታ መሆኑ ለእኛ ተከላካዮች ሊቀል ይችላል፡፡ ያንንም በመልሶ ማጥቃት ለመጠቀም ሞክረናል፡፡