ከሊጉ የ23ኛ ሳምንት ጨዋታዎች አዲስ አበባ ላይ በመጨረሻነት የተስተናገደው የደደቢት እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጨዋታ አስደናቂ ፉክክር ተደርጎበት ከ2008 በኃላ በእርስ በእርስ ግንኙነቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ድል በቀናው ኢትዮ ኤሌክትሪክ 4-3 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ሁለቱ ተጋጣሚዎች ከመጨረሻ ጨዋታዎቻቸው የአራት ተጨዋቾች ለውጥ አድርገዋል። በ22ኛው ሳምንት ከሲዳማ በሽንፈት የተመለሰው ደደቢት ከኃላ አንዶህ ኩዌኩን በከድር ኩሊባሊ ሲተካ በፋሲካ አስፋው ፣ አለምአንተ ካሳ እና ሽመክት ጉግሳ ምትክ አስራት መገርሳ ፣ አቤል ያለው እና ኤፍሬም አሻሞን ወደ መጀመሪያ አሰላለፍ አምጥቷል። ከ20ኛው ሳምንት ተላልፎ በመጣው ጨዋታ በቅዱስ ጊዮርጊስ ተሸንፎ የነበረው ኢትዮ ኤሌክትሪክም ተከላካዮቹ ግርማ በቀለ እና ስንታየሁ ሰለሞንን በሲሴይ ሀሳን እና ዘካሪያስ ቱጂ ሲቀይር አማካይ ክፍል ላይ ደግሞ በስንታየሁ ዋለጬ እና በሀይሉ ተሻገር ምትክ ኄኖክ ካሳሁን እና ተክሉ ተስፋዬ የመሰለፍ ቅድሚያውን አግኝተዋል።
ጨዋታው ከተጠናቀቀበት መንገድ ጋር ተቃራኒ በሆነ መልኩ ተቀዛቅዞ የተጀመረ ነበር። በመጀመሪያዎቹ 20 ደቂቃዎች የተደረጉት ሙከራዎችም ከሳጥን ውጪ የተገኙ እና እምብዛም አደገኛ ያልነበሩ ናቸው። በዚህ በኩል በ13ኛው እና 17ኛው ደቂቃ ጌታነህ ከበደ ከረጅም ርቀት ያደረጋቸው ሙከራዎች እንዲሁም የታፈሰ ተስፋዬ ኢላማውን ያልጠበቀ የ11ኛ ደቂቃ ቅጣት ምት ተጠቃሽ ናቸው። ከሽመክት ጉግሳ አለመኖር ውጪ በመጀመሪያው ዙር ስድስት ተከታታይ ድል ሲያስመዘግቡ ይጠቀሙበት የነበረውን አሰላለፍ እና የተጨዋቾች ስብስብ የተጠቀሙት ደደቢቶች በአቤል እንዳለ እና የአብስራ ተስፋዬ የሚመራው የአማካይ መስመራቸው ከሜዳው አስቸጋሪነት ጋር ተደምሮ በተጋጣሚ ሜዳ ላይ ክፍተቶችን መፍጠር ተቸግሮ ታይቷል። ለዚሁ ጥምረት ምላሽ ለመስጠት በሚመስል መልኩ አዲስ ነጋሽ እና ኄኖክ ካሳሁንን በተከላካይ አማካይነት ያጣመሩት ኤሌክትሪኮችም ተጋጣሚያቸውን መሀል ላይ ማፈን ቢችሉም በተሳካ የማጥቃት ሂደት መሀል ሜዳውን ማቋረጥ ተስኗቸዋል።
ከሰባቱ ጎሎች ቀዳሚ የነበረችው የካሉሻ አልሀሰን ጎል የተገኘችውም ጨዋታው በመጠኑ መሟሟቅ ሲጀምር 23ኛው ደቂቃ ላይ ነበር። ከኄኖክ ካሳሁን በረጅሙ የተላካለትን ኳስ ጋናዊው ድንቅ አማካይ በደደቢት ተከላካዮች ጫና ውስጥ ሆኖ በደረቱ በማብረድ ግሩም ጎል አስቆጥሯል። ግቧ የጨዋታውን ግለትም ከፍ ያደረገች ነበረች። በቀጣዮቹ ደቂቃዎች በውጤት ለመስተካከል ጥረታቸውን የቀጠሉት ደደቢቶች መሪነቱን ለማስጠበቅ ወደ ኃላ ያላፈገፈገው ተጋጣሚያቸው የሰራቸውን የመከላከል ስህተቶች ከወሳኙ አጥቂ ጌታነህ ከበደ በተነሱ ኳሶች ተጠቅመው የጨዋታውን መልክ ቀይረውታል። ጌታነህ ጨዋታውን ከጀመረበት የመሀል አጥቂነት ሚና ወደ ኃላ ተስቦ እና ወደ ቀኝ መስመር አድልቶ የኢትዮ ኤሌክትሪክ ቡድን የመከላከል ቅርፁን ባልያዘባቸው እና ከግብ ክልሉ ርቆ በነበረባቸው ቅፅበቶች ወደ ፊት የላካቸው ኳሶች በሁለቱ አቤሎች ልዩ አጨራረስ ወደ ግብነት ተቀይረዋል። በመጀመሪያ 35ኛው ደቂቃ ላይ ከጌታነህ በአየር ላይ ወደ ኤሌክትሪክ ሳጥን የደረሰውን ኳስ አቤል ያለው በግሩም ሁኔታ ተቆጣጥሮ በመምታት ከመረብ ሲያገናኘው ከተመሳሳይ ቦታ ከጌታነህ መሬት ለመሬት የተላከውን ደግሞ አቤል እንዳለ ወደግራ አድልቶ በመግፋት እና አክርሮ በመምታት ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል። ከነዚህ ግቦች በኃላ በ40ኛው ደቂቃ ከጌታነህ እና ኤፍሬም እንዲሁም በ42ኛ ደቂቃ ከካሉሻ እና ዲዲዬ ለብሪ ጥምረት በሁለቱም የግብ ክልሎች የተመለከትናቸው ሙከራዎች ሁለተኛውን አጋማሽ በጉጉት የሚያስጠብቁ ነበሩ።
በሁለተኛው አጋማሽ በተለየ ተነሳሽነት ወደ ሜዳ የተመለሱት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች የተነጠቁትን መሪነት መልሰው ለማግኘት 16 ደቂቃዎች ብቻ ነበሩ ያስፈለጓቸው። ከተከላካይ አማካዮቹ ፊት እንዲሁም ከታፈሰ ተስፋዬ ጀርባ የነበሩት ዲዲዬ ለብሪ ፣ አልሀሰን ካሉሻ እና ተክሉ ተስፋዬ ወደ መከላከል ሲሸጋግር በፍጥነቱ እጅግ ዘገምተኛ የነበረው ደደቢትን ሲያስጨንቁ ተስተውለዋል። ደደቢቶች የማጥቃት አጋጣሚዎቻቸው ሲበላሹ ወደ ራሳቸው አጋማሽ ከመመለሳቸው በፊት እነዚህ የኢትዮ ኤሌክትሪክ አማካዮች ኳስ ይዘው ወደ ሶስተኛው የሜዳ ክፍል የሚደርሱባቸው አጋጣሚዎችም ተደጋግመው ይታዩ ነበር። በመጀመሪያዎቹ አስር ደቂቃዎች ክሌመንት አዞንቶ እና ብርሀኑ ቦጋለን በጉዳት ሳቢያ ለመቀየር የተገደዱት ደደቢቶች በሽግግሮች ወቅት ቡድናቸው ሁለት ቦታ እየተከፈለ እና ውህደቱን እያጣ መምጣቱ በሙሉ ራስ መተማመን ከእረፍት የተመለሰው ተጋጣሚያቸውን ደካማ ጎን መልሶ ለማግኘት እንዲቸገሩ አድርጓቸዋል።
49ኛው ደቂቃ ላይ የቡድኑ አምበል አዲስ ነጋሽ ከሳጥኑ ጠርዝ ላይ አክርሮ በመታት ኳስ አቻ መሆን የቻሉት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ደጋግመው ወደ ግብ መሄዳቸውን አላቆሙም። ከግቧ በኃላ ኤፍሬም አሻሞ በቀኝ በኩል በድጋሜ ከጌታነህ ከደረሰውን ኳስ ለብቻው ሰብሮ በመግባት ሳጥን ውስጥ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ዕድሉን ካመከነ በኃላ ውጤት ወደ ኤሌክትሪኮች ፊቷን አዙራለች። እጅግ በታታሪነት ሲጫወት እና የተደጋጋሚ ጥቃቶች መነሻ ሲሆን የነበረው ዲዲዬ ለብሪ ከሚፈጥረው ተፅዕኖ በቀኝ በኩል አሁንም አሁንም ጫና ሲፈጥሩ የቆዩት ኤሌክትሪኮች 61ኛው ደቂቃ ላይ ከዚሁ ቦታ ዐወት ገብረሚካኤል አክርሮ ሞክሮት በታሪክ ጌትነት ከተመለሰ እና ከግቡ አፋፍ ላይ ካሉሻ ካስቆጠረው ግብ ጨዋታውን 3-2 መምራት ችለዋል። ሆኖም አሁንም ወደ ኃላ ሳያፈገፍጉ ወደ ቀኝ ባደላ ማጥቃታቸው የቀጠሉት ኤሌክትሪኮች በደደቢት በኩል ጎልቶ በዋለው ጌታነህ ከበደ ከመቀጣት አልዳኑም። ጌታነህ 70ኛው ደቂቃ ላይ ከአቤል ያለው በግንባር የደረሰውን ኳስ በግንባር በማስቆጠር ጨዋታውን ወደ አቻ ውጤት መልሶታል።
ድራማዊ የነበረው ጨዋታ ግን በዚህ ያበቃ አልነበረም። 72ኛው ደቂቃ ላይ ዲዲዬ ለብሪ በግሩም ሁኔታ ወደ ውስጥ አሳልፎለት ታፈሰ ተስፋዬ ለጥቂት ከሳተው ኳስ በኃላ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች የሰነዘሩት ጥቃት ወደ ግብነት ተቀይሯል። ኮከብ ሆኖ ያመሸው ካሉሻ አልሀሰን የጣለለትን ኳስ ከሳጥኑ መግቢያ ላይ አክርሮ በመምታት ያስቆጠረው ደግሞ ዘካሪያስ ቱጂን ቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው በሀይሉ ተሻገር ነበር። ቡድኑ በግራ ወገኑ ከኤፍሬም አሻሞ የደረሰበትን ጫና ለመቀነስ አዲስ ነጋሽን ወደ ግራ መስመር ተከላካይነት ወስዶ መሪ በነበረበት 64ኛ ደቂቃ ላይ በሀይሉ ተሻገርን ማስገባቱ ቢያስገርምም የኃላ ኃላ ተጠቃሚ አድርጎታል። በቀሩት ደቂቃዎች ደደቢቶች በረጅሙ ወደ ፍፁም ቅጣት ምት ክልል በሚጣሉ እና በጌታነህ ከበደ ከርቀት በሚደረጉ ሙከራዎች ግብ ለማስቆጠር ያደረጉት ጥረት የተሳካ አልነበረም። 76ኛው ደቂቃ ላይ በጨዋታ እንዲሁም 80ኛው ደቂቃ ላይ በቅጣት ምት ጌታነህ ያደረጋቸው ሙከራዎች በሱል0ማን አቡ ለጥቂት ግብ ከመሆን ድነዋል። አዝናን ሆኖ የተገባደደው ጨዋታም በውጤቱ ኢትዮ ኤሌክትሪክን ከወራጅ ቀጠናው ፈቀቅ ሲያደርገው ለደደቢት አራተኛ ተከታታይ ሽንፈት ሆኖ ተመዝግቧል።
የአሰልጣኞች አስተያየት
ም/አሰልጣኝ ቦጋለ ዘውዴ – ኢትዮ ኤሌክትሪክ
ጨዋታው ጥሩ ነበር። ነጥቡ እጅግ በጣም የሚያስፈልገን ነበር። ዛሬ ሶስት ሳይሆን ስድስት ነጥብ ነው ያገኘነው። ከወራጅ ቀጠና የሚያወጣን እና ለቀጣይ ጨዋታዎች መነሳሳት የሚፈጥርልን በመሆኑ በጣም እንፈልገው ነበር። በመሆኑም በተጨዋቾቻችን ከፍተኛ ተጋድሎ ያሰብነውን አሳክተናል። ተጨዋቾቻችን እጅግ ሊመሰገኑ ይገባል። በቀጣይ ሜዳችን ላይ ከሚኖሩ ጨዋታዎች ሙሉ ነጥቦችን በመሰብሰብ ቡድኑን ለማትረፍ እና በቀጣዩ አመት ጠንካራ ቡድን ለመገንባት እንሰራለን።
ም/አሰልጣኝ ጌቱ ተሾመ – ደደቢት
በሁለተኛው ዙር ተደጋጋሚ ሽንፈት ደርሶብናል። ይበልጥ ደሞ ዛሬ ውጤት ይዘን እንወጣለን ብለን አስበን ነበር ፤ እንዳጋጣሚ አልተሳካም። ነገር ግን አሁንም የነጥብ መቀራረብ በመኖሩ ያሉብንን ድክመቶች ማስተካከል ከቻልን በቀሩት ጨዋታዎች መፎካከር እንችላለን። በተከላካይ መስመራችን ላይ ያለው ክፍተት በቀጣይ ይስተካከላል።