ደደቢት 8 ተጫዋቾችን እየተካሄደ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሊግ ክለቦች ማስፈረሙን ዛሬ አዲሱን አሰልጣኝ ለማስተዋወቅ በጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አስታውቋል፡፡
ደደቢት ያስፈረማቸው ተጫዋቾች ሰለሞን ብሩክ ከወሎ ኮምቦልቻ ፣ ሚኪያስ ከመድን ፣ ወግደረስ ታዬ ፣ ተስሎን ሳይመን እና ሄኖክ መኮንን ከሼር ኢትዮጵያ ፣ ዮሃንስ ፀጋዬ እና ያሬድ ብርሃኑ ከመቐለ ፣ መብራህቱ ኃ/ስለሴ ከ ወልዋሎ ናቸው፡፡
የክለቡ ቴክኒክ ዳይሬክተር አቶ ሚካኤል አምደመስቀል እንደተናገሩት በዝውውር መስኮቱ ወጣቶች ላይ ትኩረት ያደረጉት በፋይናንስ ጉዳዮች እና በርካታ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች በቡድኑ ስለሚገኙ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
‹‹ በብሄራዊ ሊጉ ተጫዋቾች ላይ ያተኮርነው በሁለት ምክንያቶች ነው፡፡ የመጀመርያው በክለቡ ኮንትራት የሚቀራቸው እና ኮንትራታቸውን ያደሱ 16 ነባር ተጫዋቾች አሉን፡፡ የቀድሞ ተጫዋቻችን አይናለም ኃይለንም መልሰን አስፈርመነዋል፡፡ 2ኛው ደግሞ ከቁጥጥራችን ውጪ እየሆነ የሚገኘው ለተጫዋቾች የምንከፍለው ገንዘብ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በብሄራዊ ሊጉ ተጫዋቾች እና በፕሪሚየር ሊጉ ተጫዋቾች መካከል ያለው ልዩነት እምብዛም ነው፡፡ ወጣቶች ስለሆኑም በረጅም ጊዜ ክለቡን ይጠቅማሉ ብለን እናምናለን፡፡ ››
ክለቡ በታደለ መንገሻ ላይ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታም አስረድተዋል፡፡ ‹‹ ክለቡ ለታደለ ያቀረበው ገንዘብ በክለቡ ከፍተኛ ነው፡፡ የክለቡ አንደኛ ተከፋይ ተጫዋች ለመሆን ባለመፈለጉ ሌላ አማራጭ ልንመለከት ተገደናል፡፡ አገኘው ያለውን እድል እንዲጠቀምም ፈቅደንለታል፡፡ አሁን ያለውን ሁኔታ በዝርዝር ለሚድያ መናገር አያስፈልግም፡፡ ›› ብለዋል፡፡
የቴክኒክ ዳይሬክተሩ አሁን ባለው የተጫዋቾች ዝውውር ላይም አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ ‹‹ በአዲሱ ህግ (የፊርማ ክፍያ ቀርቶ በደሞዝ እንዲሆን የወጣው ህግ) ጉዳት እንደሚደርስብን እናውቃለን፡፡ አንዳንድ ክለቦች ቅድሚያ የፊርማ ገንዘብ እየሰጡ ነው፡፡ እነሱ ስላደረጉ ግን እኛ ማድረግ አንፈልግም፡፡ በመመርያው መሰረት እንሰራለን፡፡ በየወሩም ከተጫዋች ደሞዝ ለመንግስት 6 ሚልዮን ብር ገቢ እናስገባለን፡፡ ዘንድሮ መመርያው በሁሉም ክለቦች 50 በመቶ እንኳን ተግባራዊ ቢደረግ በየአመቱ እየተሻሻለ ወደ ትክክለኛ አሰራር መምጣት ይቻላል፡፡ መመርያው ዋጋው ለማይገባቸው ተጫዋቾች የምናወጣውን ከፍተኛ ወጪ ይቀንስልናል ብለን እናስባለን፡፡›› ብለዋል