የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 23ኛ ሳምንት ዛሬ ሶዶ ላይ ወላይታ ድቻ እና ሲዳማ ቡናን አገናኝቶ 2-2 ተጠናቋል። ባለሜዳዎቹ ድቻዎች በመጨረሻ ደቂቃዎች ባገኟቸው ጎሎች ነጥብ ሲጋሩ ፤ ሲዳማ ቡናዎች የማታ የማታ ሙሉ ነጥብ የማግኘት ዕድላቸውን አሳልፈው ሰጥተዋል።
ወላይታ ድቻዎች ከሜዳቸው ቅጣት እና ከሊጉ መቋረጥ ጋር ተያይዞ ሚያዚያ 4 ላይ በ19ኛው ሳምንት መርሐ ግብር .ከሃዋሳ ከተማ ጋር ነጥብ ከተጋሩበት ጨዋታ በኃላ ወደ ሶዶ በተመለሱበት መርሃግብር በተከታታይ 5 ጨዋታዎች ያላሳኩትን 3 ነጥብ ለማግኘት እንዲሁም ዕኩል ነጥብ በመያዝ በሊጉ ጥሩ እየተነቃቃ የሚገኘው ሲዳማ ቡና ከሜዳው ውጪ ነጥብ ለማሳከት የሚደርጉት ፍልሚያ መሆኑ ጨዋታውን አጓጊ አድርጎታል፡፡ ለረጅም ጊዜያት በሁለቱ ደርቢ ቡድኖች መሀከል የሚስተዋለው የደጋፊዎች ያልተገባ ስሜት ዘንድሮ በደጋፊ ማህበራት ጥረት ተረጋግቶ መታየቱ ይበል የሚያሰኝ ነው።
ከጨዋታው መጀመር በፊት እንዳስተዋልነው የሶዶ ስታዲየም ደጋፊ ቁጥር እነደከዚህ ቀደሙ ተበራክቶ አለመታየቱ ከቡድኑ ወቅታዊ ውጤት እና የስራ ቀን ከመሆኑ ጋር የተገናኘ ይመስላል። በተቃራኒው ባልተለመደ ሁኔታ የሲዳማ ቡና ደጋፊዎች በሶዶ ስታዲየም በቁጥር በዛ ብለው ቡድናቸውን ሲያበረታቱ ተስተውሏል። እንደ ከዚህቀደሙ ሁሉ በኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር በተጀመረው ጨዋታ ሁለቱ ቡድኖች የስፖርታዊ ጨዋነት መልዕክት ያነገቡ መፈክሮችን በመያዝ ወደ ሜዳ ሲገቡ ፤ ጨዋታው መጀመር ከነበረበት 15 ደቂቃ ያህል ዘግይቶ ነበር የተጀመረው፡፡
በጨዋታው ወላይታ ድቻ ባሳለፍነው አርብ በተስተካካይ መርሐ ግብር በድሬዳዋ ከተማ ከተሸነፈበት ስብስብ ውሰጥ የአራት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርግ ኢማኑኤል ፌቮን በመሳይ ቦጋለ ፣ ሙባርክ ሽኩሪን በውብሸት አለማየው ፣ ታዲዎስ ወልዴን በአብዱልሰምድ አሊ እንዲሁም ዮናታን ከበደን በእዮብ አለማየው ተክቷል። በአንጻሩ ሲዳማ ቡና በ22ኛው ሳምንት ደደቢትን ከረታበት ስብስብ ውስጥ ዮናታን ፍሳሃን በፍጹም ተፈሪ የተካበትን ለውጥ ብቻ አድርጓል።
በባለሜዳዎቹ ድቻዎች ፈጣን እንቅስቃሴ የጀመረው ጨውታ ብዙም ሳይቆይ ነው የመጀመርያ ሙከራ ያስተናገደው። 2ኛው ደቂቃ ለይ ጥሩ ሲንቀሳቀስ በነበረው እዮብ አለማየው ተሞክሮ ወደ ውጪ ከወጣው ከዚህ ሙከራ በኃላ በ8ተኛው ደቂቃ በዛብህ መለዮ በግሩም ሁኔታ ለእዮብ ያሳለፈለትን ኳስ እዮብ በአግባቡ ቢሞክርም በመሳይ አያኖ ተይዛበተለች። በመጀመያዎቹ 25 ደቂቃዎች ጨዋታው ድቻዎች በቀኝ እና ግራ መስመር እንዲሁም ከማዕዘን አና ከመሀል በሚጣሉ ኳሶች ወደ ሲዳማ ቡና የግብ ክልል ለመግባት በሚያደርጉት ጥረት ሲቀጥል በአንጻሩ ሲዳማዎች ኳስን መስርተው በመጫወት እና ለሁለቱ ፈጣን ለሆኑት የመስመር አጥቂዎች አዲስ ግደይ አና ሀብታሙ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረዋል። በዚህ ክፍለ ጊዜ ግን የድቻዎች ጫና ጎልቶ ታይቷል፡፡በተለይም በ11ኛው ደቂቃ በዛብህ መለዮ የሞከራት እና በግቡ አናት የሄደችው አንዲሁም እሸቱ መና ከርቀት ወደ ግብ የሞከራት ኳስ በባለሜዳዎቹ በኩል ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ፡፡
የሲዳማ ቡና የመጀመርያ ሙከራ የታየው በጫወታው 26ኛው ደቂቃ ላይ ሲሆን በግሩም ሁኔታ ከማሃል ተመስርቶ የመጣውን ኳስ ሃብታሙ ገዛህኝ በቀኝ መስመር ተቀብሎ ይዞ በመግባት እና አክርሮ በመምታት ጥሩ ሙከራ ሲያደርግ ወንድሜነህ አይናለም በ34ተኛው ደቂቃ በተመሳሳይ ሁኔታ ከሃብታሙ የተቀበለውን ኳስ ወደግል ቢሞክርም መሳይ ጳውሎስ አድኖበታል፡፡በመጀመርያው አጋማሽ የመጨረሻ 15 ደቂቃዎች ሲዳማ ቡና በፍጹም ተፈሪ ፣ ዬሴፍ ዩሃንስ ፣ በወንድሜነህ አይናለም እና አዲስ ግደይ አማካኝነት ማራኪ የኳስ ፍሰት እና አልፎ አልፎ ሃይል የተቀላቀለበት አጨዋወት ያሳየ ሲሆን በሁለቱም ቡድኖች በኩል ግን የጠራ የግብ ዕድል ሳይፈጠር የመጀመርያው አጋማሽ ተገባዷል።
ሁለተኛው አጋማሽ በርካታ ሙከራዎች እና አርት ጎሎች የታዩበት ነበር፡፡ በተጨማሪም ጨዋታው በመጨረሻ ደቂቃዎች አስገራሚ ትዕይንቶችን አስመልክቶናል። በተለይም ባለሜዳዎቹ ድቻዎች 2-0 ከመመራት አቻ የሆኑበትን ጎሎች ያገኙባቸው ደቂቃዎች እና ሲዳማ ቡናዎች በሁለተኛው አጋማሽ ሙሉ የጫዋታ ብልጫ አግኝተው ያለቁ የግብ እድሎችን በለመጠቀም ያመከኑበት አንዲሁም የማታ ማታ ዋጋ ከፈሉበት ክፍለጊዜ ነበር፡፡
በአማካይ ክፍሉ ብልጫ የተወሰደባቸው ድቻዎች ድክመታቸውን አሻሽለው የጎል እድሎችን ለመፍጠር በሚመስል መልኩ ከዕረፍት ሲመለሱ አብዱልሰምድ ዓሊን በቸርነት ጉግሳ ቀይረው ገብተዋል፡፡ ገና በ47ኛው ደቂቃ ላይም ሲዳማ ቡና ሳጥን ውሰጥ እዮብ አለማየው ያገኘውን ጥሩ ኳስ ሞክሮ ወደ ውጪ ወጥቶበታል። በተቃራኒው በዚህ አጋማሽ ጠንካራ ከነበርው የሲዳማ የተከለካይ ክፍል የሚመለሱ ኳሶችን በተደጋጋሚ በመልሶ ማጥቃት አደገኛ ሙከራዎችን ሲያደርጉ ተስተውሏል፡፡ በ49ኛው ደቂቃ ላይም በዚህ ሁኔታ የተገኘችውን ኳስ ባዬ ገዛኸኝ በግራ መስመር ጥሩ ሲንቀሳቀስ ለነበረው አዲስ ግደይ ለማሻገር ሲሞክር ኳሱን የማውጣት እድል የነበራቸው መሣይ ቦጋለ እና እሸቱ መና ባለመናበባቸው በቅጽበት ፈጣኑ አጥቂ አዲሰ ግደይ በአግባቡ በመጠቀም ለሲዳማ ቡና የመጀመርያወን ጎል አስቆጥሯል።
ከዚህች ጎል መቆጠር በኋላ ድቻዎች ለማጥቃት በሚሄዱበት አጋጣሚ በሚተዉት ክፍተት ተጠቅመው በተለይም በዬሴፍ ዩሃንስ፣ በወንድሜንህ አይናለም፣ ባዬ ገዛህኝ፣ ሐብታሙ ገዛኸኝ እና አዲስ ግደይ አማካኝነት የሚፈጠሩት የመልሶ ማጥቃት ሂደት ቀጥሎ በ55ኛው ደቂቃ ላይ አዲስ ግደይ በግራ መስመር ሰብሮ ሲገባ በውብሸት አለማየሁ ግልጽ ጥፋት ቢሰራበትም የእለቱ ዳኛ ጥፋት አልተስራም በማለት አልፈውታል፡፡ ድቻዎች በአንፃሩ በመጀመርያ አጋማሽ የነበራቸውን የመስመር ላይ እንቅስቃሴ መድገም ባለመቻላቸው በይበልጥ ተዳክሞ የነበረው ጸጋዬ ብርሃኑን በ56ኛው ደቂቃ በጃኮ አራፋት ቀይረው በማስገባት ወደ ሲዳማ ቡና የግብ ክልል ለመድረስ ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል። በ65ኛው ደቂቃ ከማዕዘን የተሻማውን ኳስ በሲዳማ የግብ ክልል ውስጥ በእጅ ብትነካም ዳኛው የፍጹም ቅጣት ምት ባለመስጠት ጨዋታውን ሲያስቀጥሉት በመልሶ ማጥቃት በርካታ እድሎችን የፈጠረው ሲዳማ ቡና በ75ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ መስመር ፍጹም ተፈሪ በግሩም ሁኔታ ያሻገረው ኳስ ከግብ ጠባቂው መሳይ ስታልፍ በሐብታሙ ገዛኸኝ ተቀይሮ የገባው ትርታዬ ደመቀ በቀላሉ በግንባሩ ገጭቶ 2ኛውን ጎል አስቆጥሯል፡፡
ከሲዳማ ሁለተኛ ጎል መቆጠር በኋላ በሁለቱም በኩል የጎል ሙከራዎች ተስተናግደዋል። በ77ኛው ደቂቃ የግብ ጠባቂውን መውጣት በመመልከት እዮብ አለማየው ከርቀት አክርሮ የመታውን ኳስ መሳይ አያኖ በግሩም ሁኔታ አውጥቶበታል፡፡ በሲዳማ በከለል ደግሞ በ80ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር በመልሶ ማጥቃት ወደ ድቻ የግብ ክልል የገባው ትርታዬ ደመቀ ለባዬ ያቀበለውን እና ባዬ ጥፋት የተሰራበት ቢሆንም ኳሷ ለአዲስ ግደይ በመድረሷ ምክንያት ዳኛው ጨዋታውን ሲያስቀጥል አዲስ ግደይ ግብ አስቆጠረ ተብሎ ሲጠበቅ አንደምንም ኃይማኖት ወርቁ በመድረስ ያስጣለው ኳስ የሚጠቀሱ ናቸው።
በሲዳማ አሸናፊነት ሊገባደድ የተቃረበው ጨዋታ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በተቆጠሩ ጎሎች መልኩ ተቀይሯል። ባለሜዳዎቹ ድቻዎች ሙሉ ለሙሉ በሚባል መልኩ በበዛብህ መለዮ፣ እዮብ አለማየሁ፣ ጃኮ አራፋት እና እሸቱ መና አማካኝነት ተደጋጋሚ ጥቃት ሰንዝረዋል። በ86ኛው ደቂቃ አሸቱ መና ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ጃኮ በግንባሩ ሲሞክር ጥሩ አቋቋም ላይ የሚገኘው በዛብህ መለዮ አግኝቶት የጎል ልዩነቱን አጥብቧል። ብዙም ሳይቆይ በ89ኛው ደቂቃ ከግራ መስመር ያሬድ ዳዊት በግሩም ሁኔታ ያሻገረውን ኳስ በሲዳማ የግብ ክልል ውሰጥ ነፃ አቋቋም ላይ የተገኘው በዛብህ መለዮ ለራሱ ሁለተኛ ቡድኑን የማታ የማታ ነጥብ ያጋራች ገል አስቆጥሯል።
በተጨማሪ 4 ደቂቃዎች ውስጥ ምንም አይነት ግብ እድል ሳይፈጠር ሲዳማ ቡናም የሁለት ጎል መሪነቱን ሳያስጠብቅ እንዲሁም ወላይታ ዲቻ በመጨረሻ ወሳኙን አንድ ነጥብ አግኝቶ ጨዋታው 2-2 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡
የአሰልጣኞች አስተያየት
ዘነበ ፍስሃ – ወላይታ ድቻ
ደርቢ እንደመሆኑ መጠን ጨዋታው እጅግ በጣም ፈታኝ እና ከባድ ነበር። ሜዳው ደግሞ ከጭቃው ጋር ተያይዞ ትንሽ ፈታኝ ነበር። የተከላካይ ስፍራችን መሻሻል አለብት። ሰርተን መጥተን ነበር ፤ ነገር ግን ሁለቱም ጎሎች በተከላካይ እና ግብ ጠባቂ አለመናበብ ነበር የገባብን። እግር ኳስ ሁሌም ስህተት አለው፡፡
ውጤቱ ከ 2-0 ተነስቶ 2-2 መሆን እጅግ በጣም ከባድ ነው። እናም የተጫዋቾቼ ያለመሸነፍ ጥረት ደስ ይላል።
ዘርዓይ ሙሉ
ከሜዳው አስቸጋሪነት አንፃር ጨዋታው ጥሩ ነበር። በተለይ ከዕረፍት በኋላ ጥሩ ለመንቀሳቀስ ሞክረናል፤ በዚህም መስረት 2-0 መርተን ነበር። 10 ደቂቃ ሲቀር ግን በሰራናቸው ስህተቶች ጎል ተቆጠረብን እንጂ አሸንፈን እንወጣ ነበር። በተለይ ሁለተኛውን ጎል ካገባን በኋላ 3ኛ ጎል ማስቆጠር እንችል ነበር። ያንን ባለመጠቀማችን ዋጋ አስከፍሎናል፡፡
በጨዋታው ውጤት ምንም አልከፋኝም። በዚህ በጭቃ የታጀበ ጨዋታ ተጫዋቾቼ በጣም ትግል አድርገዋል ፤ ጉልበት ጨርሰዋል ፤ ጥሩ ነገር አድርገዋል። በቡድኑ በጣም ደስተኛ ነኝ።