በዘንድሮው የውድድር አመት ጎልተው መታየት ከቻሉ ተጫዋቾች መካከል አንዱ የኢትዮ ኤሌክትሪኩ አልሃሰን ካሉሻ ነው። ከአማካይ ስፍራ እየተነሳ 10 ግቦችን ማስቆጠር የቻለው ጋናዊው ካሉሻ ትላንት ኤሌክትሪክ የሞት ሽረት ትግል አድርጎ ደደቢትን 3-4 ባሸነፈበት ጨዋታ ሁለት ጎሎችን በማስቆጠር ትልቁን አስተዋፅዖ አድርጓል።
አልሃሰን ከጨዋታው ፍፃሜ በኋላ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረገው አጭር ቆይታ ዘንድሮ የተቀላቀለውን ሊግ እየተላመደ መሆኑን ተናግሯል። ” ኢትዮጵያ ደስ የሚሉ ህዝቦች ያሉባት ጥሩ ሀገር ነች። እዚህ ከመጣው ጀምሮ ያገኘኋቸው ሰዎች ሁሉ መልካም አቀባበል አድርገውልኛል። ፕሪምየር ሊጉ ከባድ ነው። ከውጭ እንደ ቀላል ሊግ አድርጎ የማሰብ አዝማሚያ አለ። ይህ ግን የተሳሳተ ነው። ፉክክር ያለበት እና አስቸጋሪ ሊግ ነው። እኔም ከዚህ ጋር መላመድ አስፈልጎኛል።” ያለው አማካዩ በመጀመርያዎቹ የሊግ ጨዋታዎች ነገሮች ሁሉ ቀላል የሆኑለት ይመስል ነበር። በመጀመርያዎቹ 10 ጨዋታዎች 7 ጎሎችን በማስቆጠርም ድንቅ አጀማመር ነበር ያደረገው።
ሆኖም ኤሌክትሪክ የአሰልጣኝ ለውጥ ማድረጉን ተከትሎ የአጨዋወት ለውጡ አልሃሰንን ከጎል መንገድ አርቆታል። ትላንት ሁለት ጎሎችን ከማስቆጠሩ በፊትም ባለፉት 12 ጨዋታዎች አንድ ጎል ብቻ ነበር ማስመዝገብ የቻለው። ተጫዋች ለዚህ ምላሽ አለው። ” ዋናው ምክንያት ጉዳት ነው። ከመከላከያ ጋር በነበረው ጨዋታ እንኳን መጫወት አቅቶኝ ነበር። አንዳንዴም ከጉዳት ጋር የተጫወትኩባቸው ወቅቶች ነበሩ። ይህም የሆነው ቡድኔ የኔን ግልጋሎት ስለሚፈልግ ነው።” ይላል።
በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከአማካይ ስፍራ በመነሳት ጎሎችን ማስቆጠር ቀላል አይደለም። ጎል የማስቆጠር ኃላፊነት ለአጥቂዎች ብቻ የተተወ በሚመስልበት እግርኳሳችን አልፎ አልፎ ብቅ የሚሉ ጎል አስቆጣሪዎች ግን አይጠፉም። አምና ፍሬው ሰለሞን 10 ጎሎች ሲያስቆጥር ዘንድሮ አልሃሰን ከወዲሁ ቁጥሩን ተስተካክሏል። አልሃሰንም ” ከአማካይ ተነስቶ 10 ግቦችን ማስቆጠር ቀላል አይደለም። ይህን ላደርግ የቻልኩት ከቡድን አጋሮቼ እርዳታ የተነሳ ነው። ስናጠቃም ስንከላከልም እንደ ቡድን ነው።” በማለት ይህን ማድረግ ቀላል እንዳልሆነ መስክሯል።
በሜዳ ላይ የሚያሳየውነሰ ብቃት ያህል ንግግር ላይ እምብዛም የሆነው አልሃሰን ለአመታት ላለመውረድ እየታገለ የሚገኘው ኢትዮ ኤሌክትሪክን የመታደግ ከባድ ኃላፊነት ተሸክሟል። እሱም ዋንኛ አላማቸው የሆነው በሊጉ መቆየትን ማሳካት እንደሚችሉ ተስፋውን በመግለፅ አስተያየቱን ቋጭቷል።
” የዛሬው ድል (ከደደቢት) በጣም ወሳኝ ነበር። ለዚህም ፈጣሪን እናመሰግናለን። ከዚህ በኋላ ትኩረታችንን የምናደርገው በቀጣይ ከወላይታ ድቻ ጋር በሚኖረን ጨዋታ ላይ ነው። ገና ብዙ ነገር ከፊታችን አለ። ነገር ግን ጠንክረን ከሰራን ከመውረድ እንደምንተርፍ ተስፋ አደርጋለሁ።”