ከ17ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዋች መካከል በዕረፍት ሰዓት በደጋፊዎች ግጭት ምክንያት የተቋረጠው የወልዋሎ ዓ.ዩ እና መቐለ ከተማ ጨዋታ ቀሪ የሁለተኛ አጋማሽ 45 ደቂቃዎች ዛሬ በሽረ ተደርገው ወልዋሎ የ1-0 መሪነቱን አስጠብቆ አጠናቋል።
በሁለት አጋጣሚዎች ሊካሄድ ፕሮግራም ወጥቶለት በተለያየ ምክንያት ሳይካሄድ በቀረው እና ዛሬ 09:00 በተደረገው ጨዋታ ወልዋሎ ዓ.ዩ ከድር ሳሊህን በኤፍሬም ጌታቸው ተክቶ ወደ ሜዳ ሲገባ በመቐለ በኩል ደግሞ ግብ ጠባቂው ፍሊፖ ኦቮኖ ሀገሩ ኢኳቶሪያል ጊኒ ከኬንያ ጋር በማቻኮስ ላለባት ጨዋታ በመጠራቱ በወጣቱ ግብ ጠባቂ ሶፈንያስ ሰይፈ የተተካ ሲሆን ጉዳት በገጠማቸው ዳንኤል አድሃኖም እና ቢስማርክ ኦፖንግ ምትክ ደግሞ ካርሎስ ዳምጠው እና ለክለቡ የመጀመሪያ ጨዋታውን ባደረገው ቶክ ጄምስ ተቀይረዋል።
ጨዋታው ከመቋረጡ በፊት የሁለቱ ቡድኖች አሰላለፍ ይህንን ይመስል ነበር።
አሰላለፍ | |||
ወልዋሎ 93 ዮሀንስ ሽኩር ተጠባባቂዎች 49 ዘውዱ መስፍን |
መቐለ ከተማ 1 ፊሊፕ ኦቮኖ ተጠባባቂዎች 30 ሶፎንያስ ሰይፈ |
ውጥረት የተሞላበት እና ብዙ የጎል ሙከራ ባልነበረው ጨዋታ የመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ወልዋሎዎች ከመቐለ ከተማ በተሻለ ተጭነው ቢጫወቱም የጠሩ የጎል ዕድሎችን መፍጠር ግን አልቻሉም። በአንፃሩ መቐለ ከተማዎች ከክፍት የጨዋታ እንቅስቃሴ ይልቅ በቆሙ ኳሶች ብዙ የጎል ዕድሎች ቢፈጥሩም መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል። በጨዋታው በርካታ የማዕዘን ምት ያገኙት መቐለ ከተማዎች በዚህ ዓመት የሚስተዋልባቸው የቆሙ ኳሶች አጠቃቀም ችግር በዚህም ጨዋታ ተስተውሎባቸዋል። ከዚህ በተጨማሪ ዓመለ ሚልኪያስ በ73ኛው ደቂቃ ላይ ባሳየው ያልተገባ አጨዋወት በሁለተኛ ቢጫ ከሜዳ ከሜዳ ሲወጣ ለመቐለ ከተማም የአመቱ የመጀመርያ ቀይ ሆኖ ተመዝግቧል።
በጨዋታው መጀመርያ የመስመር አጥቂው ከድር ሳሊህን በማስወጣት ተከላካዩ ኤፍሬም ጌታቸውን ያስገቡት ወልዋሎዎች በጨዋታው የመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የያዙትን ውጤት አስጠብቀው ለመውጣት በሚመስል መልኩ አፈግፍገው ሲጫወቱ መቐለዎች በአንፃሩ ያለቀላቸው የጎል ዕድሎችን ፈጥረዋል። በተለይም በጨዋታው ማብቂያ አካባቢ ጋናዊው ተከላካይ አቼምፖንግ አሞስ በወልዋሎ ግብ ክልል ያገኛትን ኳስ አክርሮ ሞክሮ ዮሀንስ ሽኩር አድኖበታል።
ወልዋሎ ወሳኙን ድል ተከትሎ የነጥብ ድምሩን 23 በማድረስ ከወራጅ ቀጠናው ባይወጣም ከበላዮቹ ካሉ ክለቦች ያለውን ልዩነት አጥብቧል። መቐለ በአንፃሩ የሊጉ መሪ የሚሆንበትን እድል አምክኗል።