የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ 9ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ትላንት እና ዛሬ ተደርገው የየምድቦቹ መሪዎች ሀዋሳ ከተማ እና አፍሮ ፅዮን አሸንፈዋል።
በምድብ ሀ መሪው ሀዋሳ ከተማ በሜዳው ሲዳማ ቡናን 2 ለ 1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ መሪነቱን አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ የመጀመሪያ አጋማሽ በሁለቱም በኩል አመርቂ እንቅስቃሴ የታየበት ሲሆን ገና በ3ኛው ደቂቃ የውድድሩ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነትን እየመራ የሚገኘው መስፍን ታፈሰ ከእንየሁ ስንታየሁ የተሻገረለትን ኳስ ከመረብ አሳርፎ ሀይቆቹን ቀዳሚ አድርጓል። በ8ኛው ደቂቃ ላይ ምንተስኖት ደግሞ እንድሪያስ የሰጠውን ኳስ ቢኒያም ካሳሁን አስቆጥሮ ሀዋሳ ከተማ ሁለት ለምንም እንዲመራ አድርጓል፡፡
በሁለተኛውው አጋማሽ የሲዳማ ቡና የበላይነት የታየበት ሲሆን በርከት ያሉ እድሎችን ቢያገኙም ለመጠቀም ሲያዳግታቸው ታይቷል። በ84ኛው ደቂቃ ላይ የሀዋሳ ከተማ ተከላካዮችን መናበብ ችግር እንዳለበት ያስተዋለው ሀብታሙ ሲሳይ በሚገባ ለተመስገን ደራ የሰጠውን ኳስ ተመስገን አስቆጥሮ ሲዳማን ወደ ጨዋታ የመለሰች ግብ ቢያስቆጥርም ተጨማሪ ጎል ሳይቆጠር በሀዋሳ ከተማ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
በዚሁ ምድብ ዛሬ በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ማራቶን ስፖርት መከላከያን 1-0 ሲያሸንፍ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ደደቢት ያደረጉት ጨዋታ ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተፈፅሟል።
በምድብ ለ ትላንት መድንን የገጠመው አፍሮ ፅዮን 2-1 በማሸነፍ የምድቡን መሪነት በዚህ ሳምንት አራፊ ከነበረው ኢትዮጵያ ቡና በ3 ነጥብ ልዩነት ተረክቧል። ሰሰዶ ላይ ደግሞ ወላይታ ድቻ ኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚን አስተናግዶ 3-1 ማሸነፍ ችሏል።