ትላንት በተደረጉ አራት ጨዋታዎች ጅማሮውን ያደረገው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ ዛሬ በተደረጉ አራት ጨዋታዎች ቀጥሏል። ጅማ አባ ቡና፣ ካፋ ቡና፣ ስልጤ ወራቤ እና ነገሌ ከተማም ድል አስመዝግበዋል።
ጅማ አባ ቡና 3-1 ድሬዳዋ ፖሊስ
(በቴዎድሮስ ታደሰ)
ጅማ አባቡና ድሬዳዋ ፖሊስን 3-1 በማሸነፍ ደረጃውን ሲያሻሽል ከመሪዎቹ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነትም ማጥበብ ችሏል፡፡ አባ ቡናዎች በመጀመሪያው አጋማሽ ሙሉ ለሙሉ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ መውሰድ የቻሉ ሲሆን ብዙዓየሁ እንደሻው ጨዋታው በተጀመረ በ6ኛው ደቂቃ የድሬዳዋ ፖሊስ ተከላካዮች መዘናጋት ተከትሎ ያገኘውን አጋጣሚ ወደግብ በመቀየር አባቡናን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል። ከግቡ መቆጠር በኃላ ይበልጥ የተነቃቁት አባቡናዎች በቀኝ መስመር በኩል የሚያደርጓቸው የማጥቃት እቅስቃሴዎች ለተጋጣሚያቸው አዳጋች የነበሩ ሲሆን ከመሀል ሜዳ ለአጥቂዎች የሚለቀቁትን ኳሶች ሱራፌል አወልና ብዙዓየሁ እንደሻው በተደጋጋሚ ኳሶችን መቆጣጠር ባለመቻላቸው ከግብ ጠባቂው ጋር እየተገናኙ ያልተጠቀሟቸው አጋጣሚዎች የሚያቆጩ ነበሩ። በ20ኛው ደቂቃ ከግራ መስመር ሱራፌል ጌታቸውና ሮባ ወርቁ ተቀባብለው በመግባት ሱራፌል የአባቡናን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ያደረች ግብ ማስቆጠር ችሏል። ድሬዳዋ ፖሊሶች የመጀመሪያ የግብ ሙከራቸውን ለማድረግ ረጅም ደቂቃዎች የወሰደባቸው ሲሆን እስከ 30ኛው ደቂቃ ድረስ ከራሳቸው የሜዳ ክፍል ለመወጣት እና ኳስን አደራጅተው ለመጀመር ሲቸገሩ ተመልክተናል። ፖሊሶች በ33ኛው ደቂቃ በዘርዓይ ገ/ሥላሴ አማካኝነት የመጀመርያ ሙከራ ሲያደርጉ አባ ቡናዎች በ36ኛው እና 41ኛው ደቂቃ ለግብ የቀረቡ መከራዎች ማድረግ ቢችሉም ተጨማሪ ጎል ሳይቆጠር ለእረፍት ወጥተዋል።
ከእረፍት መልስ ድሬዳዋ ፖሊሶች በመጀመሪያው አጋማሽ የተወሰደባቸውን የጨዋታ የበላይነት ማስመለስ ችለዋል። በ47እና 49ኛው ደቂቃ በእዩኤል ሳሙኤል እና በአቤል ብርሀኑ አማካኝነት እድሎችን ቢፈጥሩም ወደግብነት መቀየር አልቻሉም። በመልሶ ማጥቃት የተሻሉ የነበሩት አባ ቡናዎች በ76ኛው ደቂቃ ብዙዓየሁ እንደሻው ባስቆጠረው ጎል መሪነታቸውን ወደ 3-0 ከፍ ሲያደርጉ ብዙዓየሁ እንዳሻውም የግብ መጠኑን ወደ 10 በማድረስ የውድድሩን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ለብቻው መምራት ጀምሯል። በ84ኛው ደቂቃ በአባቡና የግብክልል ውስጥ ኳስ በእጅ በመነካቱ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣትምት ብሩክ ጌታቸው አስቆጥሮ ድሬዎችን ከባዶ ከመሸነፍ በማዳን ጨዋታው በጅማ አባ ቡና 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ስልጤ ወራቤ 4-1 ወልቂጤ ከተማ
(በአምሀ ተስፋዬ)
በከፍተኛ ውጥረት ከሚካሄዱ የከፍተኛ ሊግ ጨዋታዎች አንዱ የሆነው የስልጤ ወራቤ እና ጨዋታ በስልጤ ወራቤ 4-1 የበላይነት ተጠናቋል። በመጠነኛ ዝናብ ታጅቦ በጀመረው ጨዋታ በ9ኛው ደቂቃ የቀድሞ የአርባምንጭ እና የሀዲያ ሆሳዕና ተጫዋች መልካሙ ፈንዱሬ የመጀመሪያው ኳስ ከመረብ በማገናኘት ወራቤን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል። በ17ኛው ደቂቃ ደግሞ የወልቂጤ ግብ ጠባቂ ስህተት ታክሎበት የተገኘውን የግብ አጋጣሚ ገብረመስቀል ዱባለ በግሩም በሆነ ሁኔታ አስቆጥሮ ልዩነትን ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችለዋል። በወራቤ የበላይነት በቀጠለው ጨዋታ በ26ኛው ደቂቃ መልካሙ ወደ ግብ አክርሮ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ሲያድንበት አክሊሉ አግኝቶ ሞክሮ በድጋሚ ግብ ጠባቂው ቢያድነውም ለሁለተኛ ጊዜ ኳስ ወደ እግሩ የገባችው አክሊሉ ታረቀኝ ወደ ግብነት በመለወጥ መሪነቱን ወደ 3-0 አስፍቷል። በ32ኛው ደቂቃ ላይ የወልቂጤው ብስራት ገበየው በግምት ከ20 ሜትር ርቀት አክርሮ የመታው ኳስ በተከላካይ ተጨርፎ ወደ ግብነት ለውጦ በወራቤ 3-1 መሪነት የመጀመርያው አጋማሽ ተጠናቋል።
ከዕረፍት መልስ ውጤቱን ለማስጠበቅ የወራቤ ቡድን ወደ ኃላ በማፈግፈግ መከላከልን የመረጡ ሲሆን በተቃራኒው ወልቂጤዎች ተጭነው በመጫወት ውጤቱን ለማጥበብ ጥረት አድርገዋል። በተለይ በ49ኛው ደቂቃ ብስራት ገበየው በግንባሩ በመግጨት የሞከራትን ግብ ጠባቂው ሲያድንበት በ67ኛው ደቂቃ ብሩክ በየነ ወደግብ የመታውን ኳስ የወራቤው ግብ ጠባቂ በድጋሚ ያዳነበት የሚጠቀሱ ነበሩ። በመልሶ ማጥቃት የወልቂጤን የተከላካይ መስመር የፈተኑት ወራቤዎች የፊት አጥቂዎቹ ከኳስ እና ከኳስ ውጭ የሚደርጉት የነበረው እንቅስቃሴ ፈታኝ ነበር። በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ገብረመስቀል ዱባለ በ76ኛው ደቂቃ ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ አራተኛ ጎል አስቆጥሮ የግብ ልዩነቱን ከፍ ማድረግ ችሏል። ጨዋታውም በስልጤ ወራቤ 4-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ሌሎች ጨዋታዎች
ካፋ ቡና ቤንች ማጂን አስተናግዶ ደረጃውን ያሻሸለበትን የ2-0 ድል አስመዝግቧል። በ2ኛው ደቂቃ ትዕዛዙ ፍቃደ የመጀመሪያውን ግብ ሲያስቆጥር በ57ኛው ደቂቃ ሀቁምንይሁን ገዛኸኝ ሁለተኛውን ግብ አስቆጥሯል። ነገሌ ከተማ ሀዲያ ሆሳዕናን አስተናግዶ በ50ኛው ደቂቃ አሰፋ ሳላድ ባስቆጠረው ብቸኛ ጎል ማሸነፍ ችሏል።