ፕሪምየር ሊግ | የ24ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቅድመ ዳሰሳ – ክፍል 2

በክፍል ሁለት ቅድመ ዳሰሳችን ከ24ኛው ሳምንት የዛሬ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች መሀከል ላለመውረድ በሚደረገው ፉክክር ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ ክለቦች የሚያደርጓቸው ጨዋታዎችን ተመልክተናል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ወላይታ ድቻ

የ23ኛውን ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውጤት የተመለከተ ሰው የኤሌክትሪክ እና የድቻን አልሸነፍ ባይነት ሳያደንቅ አያልፍም። አሁን እርስ በእርሳቸው ሲገናኙ ደግሞ የትኛው ቡድን ባሳለፍነው ሳምንት ያሳየውን ባህሪ ይዞ ይቀጥላል የሚለው ጥያቄ መልስ አጓጊ ይሆናል።አስገራሚ በነበረው ምሽት ደደቢትን 4-3 ማሸነፍ የቻለው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከወራጅ ቀጣናው ውጪ ሆኖ ሳምንቱን አሳልፏል። ተደጋጋሚ ለውጥ በሚታይበት የታችኛው ፉክክር ግን የነጥብ ስብስቡ 30 እስኪያልፍ ብዙም ዕረፍት የሚያገኝ አይመስልም። በመሆኑም ለአራተኛ ተከታታይ ጊዜ አዲስ አበባ ላይ የሚጫወተው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሙሉ ነጥብ የመሰብሰብ ግዴታ ይኖርበታል። 9ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ወላይታ ድቻም ቢሆን በቀጣይ ጨዋታዎች ችግር ውስጥ ላይገባ እንደሚችል እርግጠኛ መሆን አይቻልም። ከአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተሳትፎው በኃላ እየተቀዛቀዘ የመጣው ድቻ ከአሸናፊነት ከራቀ አንድ ወር አሳልፏል። የነገውንም ጨዋታ እዮብ አለማየው ከነገሰበት የፋሲሉ ጨዋታ በኃላ ወደ ድል አድራጊነት ለመመለስ የሚፋለምበት እንደሚሆን ይጠበቃል።

ሁለቱ ተጋጣሚዎች ከጉዳት እና ቅጣት ነፃ የሆነ ስብስባቸውን ይዘው ለጨዋታው እንደሚቀርቡ ይጠበቃል። በክለቡ ቅጣት ተላልፎበት የነበረው የወላይታ ድቻው ግብ ጠባቂ ወንደሰን ገረመው ይቅርታው ተቀባይነት ያገኘ ቢሆንም በዚህ ጨዋታ ላይ ግን እንደማይሰለፍ ተሰምቷል።

በጨዋታው አንድ አጥቂ ከፊት አድርገው ወደ ሜዳ እንደሚገቡ የሚጠበቁት ሁለቱ ቡድኖች የማጥቃት እንቅስቃሲያቸው እነኚሁን የፊት መስመር ተሰላፊዎቻቸውን መሰረት ያደረገ እንደሚሆን ይታሰባል። በአዲስ ነጋሽ እና ኄኖክ ካሳሁን ጥምረት የመሀል ሜዳ ሚዛኑን ለመጠበቅ የሚጥረው ኢትዮ ኤሌክትሪክ የማጥቃት ሀላፊነት ያለባቸው ቀሪዎቹ ሶስቱ አማካዮች በፈጣን ሽግግር በተጋጣሚ የተከላካይ እና የአማካይ መስመር መሀል ሲገቡ ቡድኑ አስፈሪነቱ ይጨምራል። በተለይ በዲዲዬ ለብሪ መሪነት በቀኝ መስመር በኩል ያደላው የቡድኑ ጥቃት የካሉሻ አልሀሰን ድጋፍ ተጨምሮበት ያሬድ ዳዊት ለሚሰለፍበት የድቻ የግራ ወገን የመከላከል ክፍል ፈተና እንደሚሆን ይጠበቃል። በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ተደጋጋሚ ለውጦች እያደረገ የሚገነው ወላይታ ድቻ በበኩሉ ሁለት የተከላካይ አማካዮችን የሚጠቀመው ተጋጥሚው ደካማ ጎን የሆኑት ሁለቱ መስመሮች ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ይጠበቃል። በዚህም ከመስመር አማካዬቹ ለፊት አጥቂው የሚሻገሩ ኳሶች ዋነኛ የማጥቃት አማራጭ እንደሚፈጥሩለት ይታሰባል። ከዚህ በተጨማሪ የአብዱልሰመድ አሊ እና በዛብህ መለዮ የአማካይ ጥምረት ከኢትዮ ኤሌክትሪኮቹ አዲስ እና ኄኖክ ጋር የሚገናኙባቸው ቅፅበቶች ተጠባቂ ናቸው።

የእርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ኤሌክትሪክ እና ወላይታ ድቻ በሊጉ 9 ጊዜ ተገናኝተው 3 ጊዜ ኤሌክትሪክ ሲያሸንፍ 4 ጊዜ አቻ ተለያይተዋል። ወላይታ ድቻ 2 ጊዜ ማሸነፍ ችሏል። 12 ጎሎች በተቆጠሩበት የሁለቱ ግንኙነት እኩል 6 ጎሎችን አስቆጥረዋል።

– አዲስ አበባ ላይ በተደረጉ 4 ጨዋታዎች 2 ጊዜ ኤሌክትሪክ ሲያሸንፍ 2 ጊዜ አቻ ተለያይተዋል። ወላይታ ድቻ ወደ መዲናዋ መጥቶ ኤሌክትሪክን አሸንፎ አያውቅም።

– ሶዶ ላይ በተደረገው የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ ወላይታ ድቻ የ2-0 ድልን አሳክቷል።

– ወላይታ ድቻ ባለፉት 4 ተከታታይ የሜዳ ውጪ ጨዋታዎች ሽንፈት አጋጥሞታል።

ዳኛ

 – ሁለቱ ቡድኖች የሚያደርጉት ጨዋታ የሚዳኛው በፌደራል ዳኛ ጌቱ ተፈራ ይሆናል።

አርባምንጭ ከተማ ከ ወልዲያ

በዚህ ሳምንት ከሚደረጉ ጨዋታዎች መሀከል ሁለቱም ተጋጣሚዎች በሊጉ ተመሳሳይ አላማን ይዘው የሚገናኙበት ብቸኛ ጨዋታ ይህ ይሆናል። እጅግ ደካማ ከሆነው የሜዳ ውጪ ሪከርዱ አንፃር ከጅማ ነጥብ ይዞ መመለሱ አነጋጋሪ የነበረው አርባምንጭ አሁን ደግሞ ጥንካሬውን ሲያሳይ ወደ ሰነበተበት ሜዳው ይመለሳል። አርባምንጭ ሜዳው ላይ ካደረጋቸው ጨዋታዎች በኃላ ከወራጅ ቀጠናው በጊዚያዊነትም ቢሆን ሲወጣ ይታያል። ይህን ስኬቱን ለማስቀጠል ደግሞ ዋነኛ ተፎካካሪዎቹ ከሆኑት ቡድኖች መሀከል ከወልዲያ ጋር መገናኘቱ ተነሳሽነቱን የሚጨምርለት ይሆናል። በአንፃሩ በሁለተኛው ዙር አንዴም ድል ሳይቀናው የመጨረሻው ደረጃ ላይ የተቀመጠው ወልዲያ ከአርባምንጭ ውጤት ይዞ የማይመለስ ከሆነ እና ከበላዩ ካሉት ክለቦች ጋር ያለው ልዩነት ከአንድ ጨዋታ ውጤት በላይ ከፍ ካለ በሊጉ ለመቆየት ይቸገራል። ይህ እንዳይሆን ለማድረግ ደግሞ ከሌሎች የታችኛው ሰንጠረዥ ቡድኖች ጋር ሲገናኝ የሚያስመዘግበው ውጤት ከሶስት ነጥብ በላይ የሆነ ትርጉም ይኖረዋል። 

ገዛሀኝ እንዳለ ከቅጣት ምንስተትኖ አበራ ከጉዳት የሚመለሱለት አርባምንጭ ሙሉ ስብስቡን ይዞ ለዚህ ጨዋታ የሚቀርብ ሲሆን በወልዲያ በኩል ከሰለሞን ገብረመድህን በተጨማሪ አዲስ የተሰማው የጉዳት ዜና የብርሀኔ አንለይ ብቻ ነው።

የጨዋታው አስፈላጊነት በጥንቃቄ የተሞላ እና በተለይ የመጀመሪያ ግብ እስኪስተናገድበት ድረስ ዋነኛ የመከላከል ኃላፊነት ያለባቸው የቡድኖቹ ተሰላፊዎች ትኩረት የሚፈተንበትም ጭምር ይሆናል። ባለሜዳዎቹ አርባምንጮች የአንዷለም ንጉሴ እና ኤዶም ኮድዞን ከመቆጣጠር ባለፈ የተጋጣሚያቸውን የጨዋታ አቀጣጣይ ምንያህል ተሾመን እንቅስቃሴ የማፈን ሀላፊነት ይኖርባቸዋል። የወንደሰን ሚልኪያስ እና አለልኝ አዘነ የአማካይ ክፍል ጥምረት ዋነኛ ሀላፊነትም ይህ ይመስላል። በማጥቃቱ ረገድ ግብ በማስቆጠር የአጥቂውን ክፍል ሀላፊነት ሲጋሩ የሚታዩት የአርባምንጭ ከተማ የመሀል ሜዳ ተሰላፊዎች ወደ ተጋጣሚያቸው ሳጥን ቀርበው ቀጥተኛ ሙከራዎችን የሚያደርጉበት ሂደት ወሳኝ ይሆናል። የአራቱንም አማካዮቻቸውን የመከላከል ኃላፊነት በመጨር እና ከተከላካይ ክፍላቸው ጋር የሚኖራቸውን ርቀት በማጥበብ የተጋጣሚያቸው አማካዮች ነፃነት እንዳያገኙ ለማድረግ እንደሚጥሩ የሚጠበቁት ወልዲያዎች ግብ ለማስቆጠር አሁንም እምነታቸው በአንዷለም ላይ የሚሆን ይመስላል። ቡድኑ ወደ ተጋጣሚው የሜዳ ክልል ዘልቆም ይሁን መልሀ ሜዳውን ሳያቋርጥ ከሁለቱ መስመሮች ወደ አንዷለም በቀጥታ የሚልካቸው ኳሶች ዋነኛ የግብ ሙከራዎችን የሚፈጥርበት መንገድ እንደሚሆኑ ይታሰባል። 

የእርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ሁለቱ ቡድኖች 5 ጊዜ ተገናኝተው አርባምንጭ ከተማ ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ ወልዲያ አንድ አሸንፏል። ሁለት ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ ናቸው። በእርስ በእርስ ግንኙነቱ 6 ጎል ሲቆጠር ሶስት ሶስት ተካፍለዋል።

– አርባምንጭ ላይ ሁለት ጊዜ ተገናኝተው አርባምንጭ አንዱን ሲያሸንፍ ሌላኛው በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

– በመጀመርያው ዙር ወልዲያ ላይ ተገናኝተው ወልዲያ በአንዱዓለም ንጉሴ እና ፍፁም ገብረማርያም ጎል 2-0 አሸንፏል።

– አርባምንጭ ከተማ ያለፉት 5 ተከታታይ የሜዳው ጨዋታዎችን ሲያሸንፍ ወልዲያ በአንፃሩ ባለፉት 9 ጨዋታዎች ከድል ርቋል።

ዳኛ

– ኢንተርናሽናል ዳኛ በአምላክ ተሰማ ይህን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት የሚመራው ይሆናል። 

ሲዳማ ቡና ከ አዳማ ከተማ

ባሳለፍነው የሊጉ ሳምንት ጥሩ ትዝታ የሌላቸው ሁለቱ ክለቦች አሁን ላይ መገናኘታቸው ለየት ያለ አጋጣሚ ይመስላል። ሶዶ ላይ ከ2-0 መሪነቱ ተነስቶ በመጨረሻ ደቂቃዎች በተቆጠሩበት ጎሎች ምክንያት ነጥብ ለመጋራት የተገደደው ሲዳማ ቡና  ከሽንፈት ርቆ የቆየበትን የአንድ ወር ውጤት አስጠብቆ ለመቀጠል አዳማን ያስተናግዳል። የሲዳማ ይህ ተከታታይ ውጤታማነት ከአደጋ ዞኑ ያረቀው ቢሆንም ነጥቡን ከ30 በላይ ለማድረግ እና ይበልጥ ለመደላደል ነገ ማሸነፍ ይጠበቅበታል። የዋንጫ ተፎካካሪነቱ አንዴ ደመቅ አንዴ ፈዘዝ እያለ 24ኛው ሳምንት ላይ የደረሰው አዳማ ከተማ ደግሞ የ31 ጨዋታ የሜዳው ላይ ያለመሸነፍ ሪከርዱን በመቐለ ተነጥቆ ወደ ይርጋለም ያቀናል። በርግጥ ሰባት ጨዋታዎች እየቀሩ ከመሪዎቹ ጋር የአራት ነጥብ ልዩነትን መያዝ ተስፋ የሚያሳጣ ባይሆንም ወጥ ያልሆነው የስካሁኑ ጉዞው አዳማን ከፉክክር እንዳያርቀው ያሰጋል። ዘንድሮ ሁለት ተከታታይ ሽንፈት ገጥሞት የማያውቀው አዳማ ከዚህ ጨዋታ ዉጤት ይዞ መመለስ ከቻለ ስለሻምፒዮንነት እያሰበ ለመቆየት ዕድል ያገኛል።

በሁለቱም ቡድኖች በኩል የተሰማ የቅጣትም ሆነ የጉዳት ዜና የሌለ ሲሆን የአዳማው የመስመር አማካይ ሲሳይ ቶሊ ሀዋሳ ላይ ከተመለከተው የቀይ ካርድ አራት ጨዋታዎች ቅጣት በኃላ ወደ ሜዳ እንደሚመለስ ይጠበቃል።

ለፈጣን ጥቃት የተመቹ ተጨዋቾችን የያዙት ሁለቱ ቡድኖች የተለያየ አቀራረብ ያላቸው ቢሆንም በቶሎ ወደ ግብ እየደረሱ ሙከራዎችን ለማድረግ እምብዛም የሚቸገሩ አይመስልም። የሁለቱ የገዛሀኝ ወንድማማቼች እና አዲስ ግደይን በፊት አውራሪነት የሚጠቀመው ሲዳማ ቡና በተጋጣሚው የመሀል ሜዳ የቁጥር ብልጫ ሊወሰድበት ይችላል። የሶስቱ አጥቂዎች በብዛት ከአማካይ ክፍሉ መራራቅ ለዚህ ችግር የሚዳርገው ቢሆንም በሚነጠቁ ድንገተኛ ኳሶች ግን በፍጥነት ወደ ጎል ለመድረስ ያላቸው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው። በዚህ ረገድ የአዳማ የመስመር ተከላካዮች በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ወቅት በእጅጉ ሊቸገሩ እንደሚችሉ መናገር ይቻላል። አዳማ ደግሞ መሀል ሜዳ ላይ የበላይነትን ለማግኘት ከቁጥር ብልጫ ባለፈ በጥራትም ረገድ ላቅ ያሉ አማካዮችን የያዘ ቡድን እንደመሆኑ መጠን በተጋጣሚው የሜዳ ክልል ላይ ስኬታማ የቅብብል መስመሮችን በመዘርጋት ለነ ዳዋ ሁቴሳ የመጨረሻ የግብ ዕድሎችን መፍጠር የመጀመሪያ እቅዱ ይሆናል። በተጋጣሚያቸው የመስመር አጥቂዎች ሊታፈኑ የሚችሉት የመስመር ተከላካዮች እገዛ እምብዛም ሊሆን ቢችልም ከአጥቂዎቹ መሀከል የቡልቻ ተሳትፎ ተጨምሮበት የሱራፌል ዳኛቸው ፣ ከንአን ማርክነህ እና በረከት ደስታ ጥምረት ክፍተቶችን ለማግኘት ላይቸገር ይችላል። 

የእርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ሲዳማ እና አዳማ 13 ጊዜ ተገናኝተው ሲዳማ በ6 ድል ቀዳሚ ሲሆን አዳማ 3 ጨዋታ አሸንፏል። 4 ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ሲዳማ 12፣ አዳማ 10 ጎል አስቆጥረዋል።

– ይርጋለም ላይ 6 ጊዜ ተገናኝተው ሲዳማ ቡና 4 ጊዜ ድል ሲያስመዘግብ 1 ጊዜ አዳማ ያሸነፈበት፣ አንድ የአቻ ውጤት ተመዝግቧል። በእርስ በእርስ ግንኙነት ከተቆጠሩት 22 ጎሎች መካከል ደግሞ 9ኙ ይርጋለም ለመይ የተቆጠሩ ናቸው።

– በመጀመርያ ዙር አዳማ ላይ የተገናኑበት ጨዋታ 1-1 የተጠናቀቀ ነበር።

ዳኛ

– ጨዋታውን በመሀል ዳኝነት የመምራቱ ሀላፊነት ለፌደራል ዳኛ ተካልኝ ለማ ተሰጥቷል።

ፋሲል ከተማ ከ ድሬዳዋ ከተማ                      

የዚህ ጨዋታ ውጤት ከፋሲል በላይ ለድሬዳዋ እጅግ ወሳኝ ነው። በወራጅ ቀጠና ካሉት ቡድኖች መሀል 25 ነጥብ ላይ ደርሶ እና ሶስት የግብ ዕዳዎች ብቻ ኖረውበት 12ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ድሬዳዋ ከአንድ ወር በኃላ ከሜዳው ውጪ ይወጣል። በነዚህ ጊዜያት ሳይሸነፍ መዝለቁ አሁን ላይ የተሻለ ተስፋን እንዲይዝ ቢያደርገውም በሚቀጥለው አመት በሊጉ ለመቀጠል ግን የመትረፍ ጉዞው ገና ብዙ ይቀረዋል። ሆኖም ደደቢትን ሜዳው ላይ ከረታ በኃላ ውጤት የራቀው ፋሲል ወደ አሸናፊነት ለመመለስ በማሰብ ለድሬደዋ ከባድ ፈተና እንደሚሆን ይጠበቃል። ለመሀል ሰፋሪነት እየቀረበ የሚገኘው ፋሲል በዋንጫ ፉክክሩ ውስጥ ለመቆየት የነበረው ተስፋ እየደበዘዘ መጥቷል። የአሰልጣኝ ለውጥ ካደረገ በኃላ አሳይቶት የነበረው መነቃቃትም ተቀዛቅዟል። ይህን ጨዋታ ማሸነፍ ከቻለ ግን ወደ መነቃቃቱ ለመመለስ የተሻለ ዕድል የሚፈጥርለት ይሆናል። 

በፋሲል ከተማ ስብስብ ውስጥ የያሬድ ባየህ እና አይናለም ኃይለ ጉዳት የተጠበቀ ሲሆን በጉዳትም ሆነ በቅጣት ቡድኑ የሚያጣው ተጨማሪ ተጨዋች አይኖርም። በድሬዳዋ ከተማ በኩል ከሚካኤል አካፉ ፣ ዘነበ ከበደ እና ያሬድ ታደሰ በተጨማሪ ሀብታሙ ወልዴም በጉዳት ከጨዋታው ውጪ እንደሚሆን ተሰምቷል።

ድሬዳዋ ከተማ ከዚህ ጨዋታ የሚያገኘው ነጥብ ወሳኝ ከመሆኑ አንፃር ከሌሎቹ ጊዚያት አንፃራዊ ጥንቅቄ የሚያደርግበት ፋሲል ከተማ ደግሞ ሙሉ ለሙሉ ማጥቃት ላይ የሚያተኩርበት የጨዋታ እንቅስቃሴ ይጠበቃል። ወደ ኃላ ካፈገፈገ ቡድን ጋር ሲገናኙ ክፍተቶችን ለማግኘት የሚቸገሩት ፋሲሎች በመስመር አጥቂዎቻቸው አማካይነት የሜዳውን ስፋት ተጠቅመው በድሬ የኃላ መስመር ተሰላፊዎች መሀል ክፍቶችን ለመፍጠር እንደሚንቀሳቀሱ ይጠበቃል። ቡድኑ እየተዳከመ በመጣው የማጥቃት ሂደቱ ላይ የማጥትቃ ባህሪ ባላቸው አማካዮቹ ላይ መሻሻሎችን ማድረግም ይጠበቅበታል። ከኢማኑኤል ላርያ ፊት የሚኖሩ ስሶት አማካዮቻቸውን ወደ ኃላ መለስ አድርገው ክፍተት ባለመስጠት እና የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን በመጠባበቅ እንደሚጫወቱ የሚጠበቁት ድሬዎች አንድ አጥቂ በመቀነስ ሳውሬል ኦልሪሽን ተጠቅመው የአማካይ ክፍል ተሰላፊዎቻቸውን ቁጥር ወደ አምስት ከፍ የማድረግ አማራጭም ይኖራቸዋል። በሁለቱም አቀራረቦች ዮሴፍ ዳሙዬ ፣ ዘላለም ኢሳያስ እና ሱራፌል ዳንኤል ቡድኑ ወደማጥቃት በሚሸጋገርባቸው ወቅቶች ላይ የሚኖራቸው ሚና ግን ወሳኝነቱ የጎላ ነው።

የእርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– በሊጉ ሶስት ጊዜ ተገናኝተው ድሬዳዋ አንዱን ሲያሸንፍ በሁለቱ አቻ ተለያይተዋል። ፋሲል ምንም ድል አላስመዘገበም። ድሬዳዋ 2፣ ፋሲል አንድ ጎል አስቆጥረዋል።

– ጎንደር ላይ አንድ ጨዋታ (2009) ተከናውኖ ያለ ግብ ተጠናቋል።

– ዘንድሮ በመጀመርያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ 1-1 ሲለያዩ ለተጨማሪ ህክምና ወደ ባንኮክ ያመራው ዓይናለም ኃይለ በጨዋታው ላይ መጎዳቱ የሚታወስ ነው።

– ፋሲል ከተማ በቅዱስ ጊዮርጊስ ከተሸነፈ ወዲህ ጎንደር ላይ ባደረጋቸው 5 ጨዋታዎች ሽንፈት ያላስተናገደ ሲሆን ድሬዳዋ በአንፃሩ ከሜዳው ውጪ ድል ካስመዘገበ አንድ አመት አልፎታል።

ዳኛ

– ኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ ይህን ጨዋታ የመዳኘት ሀላፊነት ተሰጥቶታል።