በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 24ኛ ሳምንት ይርጋለም ላይ አዳማ ከተማን ያስተናገደው ሲዳማ ቡና በአዲስ ግደይ ብቸኛ የፍፁም ቅጣት ምት ግብ 1-0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ከወራጅ ቀጠናው መራቅ ችሏል።
ሲዳማ ቡናዎች በ23ኛው ሳምንት በደቡብ ደርቢ ከመምራት ተነስቶ ሁለት አቻ በተለያየበት ጨዋታ ከተጠቀመው የመጀመርያ አሰላለፍ መካከል የአንድ ተጫዋች ብቻ ለውጥ በማድረግ ሙጃይድ መሐመድን በዮናታን ፍሰሀ ብቻ ተክተው ሲገቡ አዳማ ከተማዎች በሜዳቸው በመቐለ ከተረቱበት የ23ኛው ሳምንት ጨዋታ የሶስት ተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ ሱሌይማን ሰሚድ፣ ተስፋዬ በቀለ እና ቡልቻ ሹራ ወደ ተጠባባቂ ወንበር ሲወርዱ ተስፋዬ ነጋሽ፣ ሚካኤል ጆርጅ እና ኢስማኤል ሳንጋሪ ወደ መጀመርያ አሰላለፍ ተካተዋል። ከዚህ በተጨማሪ በአዳማ በኩል በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ አዲስ ህንፃ ተካቶ የነበረ ቢሆንም ዳኞች ፍተሻ በሚያደርጉበት ወቅት የአዳማ ከተማ የአሰልጣኝ ቡድን አባላት የተጫዋቹን ቴሴራ ረስተው በመምጣታቸው ምክንያት በሱራፌል ዳኛቸው ተተክቶ ከጨዋታው ውጭ ሆኖ በተመልካችነት ለማሳለፍ ተገዷል።
በሲዳማ ቡና ደጋፊዎች ማኅበር የተዘጋጀ “ከሁሉ በፊት ለስፖርታዊ ጨዋነት ቅድሚያ እንስጥ” የሚል መልዕክት አዘል ባነር እና የኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙር ታጅቦ በፌድራል ዳኛ ተካልኝ ለማ መሪነት የተጀመረው ጨዋታ አሰልቺ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ የታየበት ሆኖ አልፏል።
አዳማ ከተማዎች በመጀመሪያዎቹ 15 ደቂቃዎች የተሻለ በመንቀሳቀስ በረጅሙ በሚጣሉ ኳሶች ያልተሳኩ ሙከራዎችን አድርገዋል። 2ኛው ደቂቃ ላይ ሱራፌል ዳኛቸው ከማዕዘን ምት በቀጥታ ሞክሮ ግብ ጠባቂው መሳይ አያኖ እንደምንም ያወጣበት የመጀመርያ ተጠቃሽ ሙከራ ስትሆን 7ኛው ደቂቃ ላይ አዲስ ግደይ ላይ በተሰራ ጥፋት በግራ በኩል የተሰጠውን ቅጣት ምት ፈቱዲን ጀማል በቀጥታ መትቶ ለጥቂት የግቡን ብረት ጨርፋ የወጣችው በሲዳማ ቡና በኩል የመጀመርያው ሙከራ ነበር። 19ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ሐብታሙ ገዛኸኝ በረጅሙ ያሻገረለትን ኳስ አዲስ ግደይ አምልጦ ገብቶ የሞከራትና ወደ ውጪ የወጣችው ኳስም ሌላዋ የምትጠቀስ ሙከራ ነች።
ለረጅም ደቂቃዎች ያለ ጎል ሙከራ የዘለቀው ጨዋታ ለተመልካች እጅግ አሰልቺ የነበረ ሲሆን ከ19ኛው ደቂቃ ሙከራ በኋላ የሚጠቀስ የግብ አጋጣሚ ለመመልከት 20 ደቂቃዎች ፈጅቷል። 40ኛው ደቂቃ ላይ ሱራፌል ከበረከት ጋር በጥሩ ቅብብል አድርጎ ወደ ውስጥ ይዘው የገቡትን ኳስ በረከት አክርሮ ወደ ግብ መቷት ግብ ጠባቂው መሳይ አያኖ ሲመልስበት 42ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ አዲስ ግደይ ሁለት የአዳማ ተጫዋቾችን በማለፍም ከሙጂብ እግር ስር ነጥቆ ከግብ ጠባቂው ጃኮ ፔንዜ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ የመታትን ኳስ ጃኮ ፔንዜ። ያዳነበት በመጀመርያው አጋማሽ የመጨረሻ ደቂቃዎች የሚጠቀሱ ሙከራዎች ነበሩ።
ሲዳማ ቡና ተሻሽሎ በቀረበበት ሁለተኛው አጋማሽ ባለሜዳዎቹ ፍፁም ተፈሪን በትርታዬ ደመቀ፣ ባዬ ገዛኸኝን በወጣቱ አጥቂ ይገዙ ቦጋለ፣ ሀብታሙ ገዛኸኝን በተከላካዩ ማይክል አናን በመተካት ጥሩ ጥሩ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል። 53ኛው ደቂቃ ላይ ወንድሜነህ አይናለም ከርቀት አክርሮ መቷት ጃኮ ፔንዜ እንደምንም ሲይዝበት በ69ኛው ደቂቃ አዲስ ግደይ ወንድሜነህ የሰጠውን ኳስ አስቆጠረ ሲባል ጃኮ ከእግሩ ስር ነጥቆታል። በአዳማዎች በኩል ደግሞ 56ኛው ደቂቃ ላይ ከነዓን ማርክነህ በግል ጥረቱ እየገፋ ገብቶ ያገኘውን እድልን በቀላሉ አምክኖታል።
አዳማዎች ግብ ዳዋ ሆጤሳ እና ሱራፌል ዳኛቸው ፤ ሲዳማዎች ደግሞ አዲስ ግደይን ማዕከል ያደረጉ የማጥቃት እንቅስቃሴዎችን ባየንበት የመጨረሻዎቹ 20 ደቂቃዎች ሲዳማ ቡና አሸናፊ የሆነበትን ጎል ጨምሮ በርካታ እድሎች መፍጠር ችሏል። በተለይ ሐብታሙ፣ ወንድሜነህ ይገዙ ባደረጉት አንድ ሁለት ቅብብል ወደ ሳጥን ገብተው በመጨረሻም ይገዙ ቦጋለ ሞክሯት በቀላሉ የባከነችው እንዲሁም 71ኛው ደቂቃ ላይ የአዳማ ከተማው ተከላካይ ምኞት ደበበን ሰህተት የተጠቀመው ወንድሜነህ አይናለም አክርሮ መትቶ አግዳሚውን ታካ ወጥታለች። 73ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ በመስመር ላይ በተደጋጋሚ የአዳማን ተከላካይ ሲረብሽ የነበረው አዲስ ግደይ በግራ በኩል እየገፋ ወደ ሳጥን ሲገባ በግብ ክልል ውስጥ በሙጂብ ቃሲም በመጠለፉ ምክንያት የእለቱ ፌ/ል ዳኛ ተካልኝ ለማ የሰጡትን የፍፁም ቅጣት ምት ራሱ አዲስ ግደይ በመምታት የሲዳማን ወሳኝ ግብ አስቆጥሯል።
ሲዳማዎች ከግቡ በኋላም በይገዙ ቦጋለ፣ አዲስ ግደይ እንዲሁም በወንድሜነህ አይናለም አማካይነት በርካታ የግብ እድልን ቢያገኙም ተጨማሪ ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ጨዋታው በሲዳማ ቡና 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ከጨዋታው በኋላ የአዳማ ከተማው አማካይ በረከት ደስታ ከሲዳማ ቡና ደጋፊዎቹ ጋር የፈጠረው ውዝግብ የወረወረው ውሀ አዘል የፕላስቲክ ጠርሙስ ደጋፊውን ያስቆጣ ሲሆን ጨዋታ ከተጠናቀቀ በኋላ ደጋፊዎች ወደ መጫወቻ ሜዳው የሚገቡበት ልማድ በይርጋለም ስታዲየም በተደጋጋሚ እየተስተዋለ ሊታረም ያልቻለ እና እንግዳ ክለቦች (በዛሬው እለት አዳማ ከተማን ጨምሮ) ስጋታቸውን የሚገልፁበት ጉዳይ ነው።
የአሰልጣኞች አስተያየት
ዘርዓይ ሙሉ – ሲዳማ ቡና
“ጨዋታው ከባድ ነበር ማለት እችላለሁ። ያ ማለት ተጋጣሚያችን ይዞ የመጣሁ አጨዋወት ትንሽ ፈትኖን ስለነበር በፊት ወደ ነበርንበት እንቅስቃሴ ለመምጣት ተቸግረናል። ሆኖም ግን ከእረፍት በኃላ ለማስተካከል ሞክረን ውጤታማ ሆነናል። ባናሸንፍም ከስጋት እንወጣለን። ተጫዋቾቹ አቅም ያላቸው ናቸው። ቡድናችንንም ወደ ተፎካካሪነት እናመጣዋለን”
*የአዳማ ከተማው አሰልጣኝ ተገኔ ነጋሽ ለጋዜጠኞች የድህረ ጨዋታ አስተያየት ሳይሰጡ ቀርተዋል። ለአስተያየት በተጠየቁበት ወቅትም ያልተገባ ምላሽ ሰጥተዋል።