በ24ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 09፡00 ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም የተገናኙት ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ወላይታ ድቻ ጨዋታቸውን ያለግብ አጠናቀዋል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ ደደቢትን 4-3 ካሸነፈበት ጨዋታ ግራ መስመር ተከላካይ ቦታ ላይ ተክሉ ታፈሰን በዘካርያስ ቱጂ የተካበት ቅያሪ ብቸኛው ለውጡ ነበር። በአንፃሩ በርከት ያለ ለውጦች ያደረጉት ድቻዎች ከሲዳማ አቻ ከተለያዩበት ጨዋታ የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ግብ ጠባቂው መሣይ ቦጋለን በኢማኑኤል ፌቮ እንዲሁም ቀኝ መስመር ተከላካዩ እሸቱ መናን በተስፉ ኤልያስ ለውጠዋል። ከዚህ በተጨማሪም ጃኮ አራፋት እና ዮናታን ከበደ በፀጋዬ ብርሀኑ እና ዳግም በቀለ ምትክ የዛሬውን ጨዋታ በመጀመሪያ ተሰላፊነት ጀምረዋል።
ጨዋታው በጀመረበት ቅፅበት አብዱልሰመድ በረጅሙ ወደ ሳጥን በላከው ፣ ጃኮ አራፋት ከተስፋዬ መላኩ ቀምቶ በግራ መስመር ይዞ በገባው እና እዮብ አለማየሁ ከዚሁ አቅጣጫ ባሻገረው ኳስ በፈጣን ማጥቃት የጀመሩት ድቻዎች እጅግ አስፈሪነትን ተላብሰው ነበር። በነዚህ ደቂቃዎች የነበረው የኢትዮ ኤሌክትሪክ የኃላ መስመር አለመረጋጋትም ዋጋ ሊያስከፍለው ተቃርቦ ነበር። ሆኖም 4ኛው ደቂቃ ላይ በሀይሉ ተሻገር ካደረገው ኢላማውን ያልጠበቀ የርቀት ሙከራ በኃላ መጠነኛ መነቃቃት ያሳዩት ኤሌክትሪኮች ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው ገብተዋል። ከሁለቱ ተከላካይ አማካዮች የማጥቃት ሀላፊነት በነበረው አዲስ ነጋሽ እየተመሩም እስከ 25ኛው ደቂቃ ድረስ ጥሩ የኳስ ቁጥጥርን ማግኘት ችለዋል። ነገር ግን በግራ በኩል ቀጥተኛ ሩጫዎችን ሲያደርግ ወደ ሚታየው ዲዲዬ ለብሪ ከሚጣሉ ኳሶች በቀር ቡድኑ መሀል ላይ በቁጥር ተበራክተው የሚከላከሉት ድቻዎችን አልፎ ወደ ሳጥን ውስጥ ለመዝለቅ ተቸግሯል። ከዐወት እና ተክሉ ከኝ መስመር ወደ ውስጥ ይጣሉ የነበሩ ኳሶችም በድችል ተከላካዮች ከመገጨት ያለፈ ፋይዳ አልነበራቸው። 22ኛው ደቂቃ ላይ ዲዲዬ ለብሪ ከሳጥን ውስጥ ለካሉሻ ሰጥቶት ተከላካዮች እንደምንም ደርሰው ያወጡት ኳስ የኤሌክትሪክ ጠንካራ ሙከራ ነበር።
በጀመሩበት ፍጥነት መቀጠል ያልቻሉት ድቻዎችም በሜዳቸው ላይ ቆይተው ተጋጣሚያቸውን የመቀባበያ ክፍተት በማሳጣቱ በኩል ቢሳካላቸው በረጅም ኳሶች ጃኮን ለማግኘት በመሞከር ላይ ነበር በአመዛኙ የተመረኮዙት። እዮብ አለማየሁ በ21ኛው እና 29ኛው ደቂቃዎች ላይ ያደረጋቸው የሳጥን ውጪ ሙከራዎች ከድቻ በኩል የሚነሱ ሲሆን በተለይም ሁለተኛው ሙከራ በሱላማና አቡ ዳነ እንጂ ግብ ለመሆን ተቃርቦ ነበር። ከዚህ ውጪ የወላይታ ድቻ አማካዮች የኤሌክትሪክ የወገብ በታች ቡድን ላይ በሚያሳድሩት ጫና የሚቀሟቸው ኳሶች ለጦና ንቦቹ መልካም አጋጣሚዎችን ሲፈጥሩ ይታዩ ነበር። ኄኖክ ካሳሁን እና ተስፋዬ መላኩም በዚህ ጫና ምክንያት በተደጋጋሚ የቅብብል ስህተት ሲሰሩ ይታዩ ነበር። 43ኛው ደቂቃ ልይ በዛብህ መለዮ ከግራ መስመር በተቀማ ኳስ ያገኘው ንፁህ ዕድል በአቡ ግብ ከመሆን ቢድንም ለዚህ ነጥብ ሁነኛ ማስያ ተደርጎ የሚወሰድ ነው።
የተጨዋቾቻቸው ተደጋጋሚ ስህተት ያሳሰባቸው አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ 40ኛው ደቂቃ ላይ ተስፋዬ መላኩን አስወጥተው ግራ መስመር ተከላካዩ ዘካርያስ ቱጂን አስገብተዋል። ጨዋታውን በአማካይነት የጀመረው አዲስ ነጋሽ ወደ መሀል ተከላካይነት እንዲሁም በግራ መስመር ተከላካይነት የገባው ተክሉ ተስፋዬ ወደ አማካይ መስመር ያደረጉት ለውጥም የአሰልጣኝ አሸናፊን ለውጥ ተከትሎ የተደረጉ መሸጋሸጎች ነበሩ። የመጀመሪያው አጋማሽ የመጨረሻ ሙከራም በዲዲዬ ለብሪ ከሳጥኑ ጠርዝ ላይ ተደርጎ ኢላማውን ሳይጠብቅ ሲቀር አቀባዩ ኳስ ከታፈሰ ተስፋዬ ተቀብሎ በግራ መስመር በኩል ሰብሮ የገባው ዘካርያስ ቱጂ ነበር።
ሁለተኛው አጋማሽ በአመዛኙ የኢትዮ ኤሌክትሪክ የበላይነት የታየበት ነበር። ኤሌክትሪኮች በመጀመሪያው አጋማሽ እጅግ ከብዷቸው የነበረው ከኳስ ጋር ከወላይታ ድቻ የተከላካይ መስመር ጀርባ የመግባትን ሂደት በበርካታ አጋጣሚዎች ሲያሳኩት ተስተውሏል። ነገር ግን በድቻ ሳጥን ውስጥ ይሰሩት የነበረው የቅብብል ስህተት እና የገኟቸውን የመጨረሻ ዕድሎች ወደ ጎል መቀየር አለመቻላቸው ጎድቷቸዋል። 51ኛው ደቂቃ ላይ ታፈሰ ተስፋዬ ከርቀት ባደረገው ሙከራ የድቻን በር ማንኳኳት የጀመሩት ኤሌክትሪኮች በቁጥር በርክተው ሶስተኛው የሜዳ ክፍል ውስጥ ዘልቀው ገብተው ከጨዋታ ውጪ ከሆኑባቸው አጋጣሚዎች ሌላ ኢላማቸውን የጠበቁ በርካታ ሙከራዎችንም ማድረግ ችለዋል። በተለይ 63 እና 65ኛው ደቂቃ ላይ ባልተለመደ መልኩ ካሉሻ ከቅርብ ርቀት ያመከናቸው ኳሶች ለቡድኑ እጅግ የሚያስቆጩ ነበሩ። ጥሩ ሲንቀሳቀስ የዋለው ሲሴይ ሀሰንም የታፈሰን የማዕዘን ምት በግንባሩ ወደ ግብነት ለመቀየር ተቃርቦ የነበረ ቢሆንም ኢማኑኤል ፌቮ እንደምንም አውጥቶበታል።
በመጀመሪያው አጋማሽ የነበራቸውን ጫና ፈጥሮ ኳስ የማስጣል ብቃት አጥተው ከእረፍት የተመለሱት ወላይታ ድቻዎች ጃኮ አራፋትን ኢላማ ካደረጉ ረጃጅም ኳሶቻቸው በቀር መሀል ሜዳ ላይ ጊዜውን ካሳለፈው የተጋጣሚያቸው የተከላካይ መስመር ጀርባ መገኘት ከብዷቸው ታይቷል። በተፈጠረባቸው ጫና በብዛት በራሳቸው ሜዳ ላይ ሆነው በርካታ ደቂቃዎችን ያሳለፉት ድቻዎች 68ኛው ደቂቃ ላይ እዮብ አለማየሁ ከርቀት ካደረገው ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ውጪ ወደ ጎል ለመድረስ እስከመጨረሻው ደቂቃ ድረስ ለመጠበቅ ግድ ሄኖባቸው ነበር። 75ኛው ደቂቃ ላይ ዳግም በቀለ ጃኮ አራፋትን ቀይሮ ከገባ በኃላ በተቀሩት ጊዜያት ተጋጣሚያቸው ከራሱ ማዳ እንዳይወጣ በማድረጉ በመጠኑ የተሳካላቸው ድቻዎች ሙከራዎችን ለማድረግ ግን በኢትዮ ኤሌክትሪክ ተጨዋቾች ስህተት ላይ ተመስርተው ነበር። ተጨማሪ ደቂቃ ላይ ሱሊማን አቡ ከሳጥን ውጪ ኳስ በእጁ ነክቶ የተሰጠው እና ዮናታን ከበደ የመታው ቅጣት ምትም የወላይታ ድቻ ምርጡ ሙከራ ቢሆንም ሱሊማና አቡ ለጥቂት አድኖታል። ጨዋታውም በዚህ መልኩ ያለግብ ተጠናቋል።
የአሰልጣኞች አስተያየት
ም/አሰልጣኝ ቦጋለ ዘውዴ – ኢትዮ ኤሌክትሪክ
ዛሬ አሸንፈን ደረጃችንን ለማሻሻል አስበን ነበር የመጣነው። ግን እንደታየው ዕድል ከኛ ጋር አልነበረችም እነሱም 0-0 መጨረሱን የፈለጉት ይመስላል። አልተሳካልንም እንጂ ብዙ ሙከራዎችን አድርገን ነበር። ገና ቀሪ ጨዋታዎች በመኖራቸው የአርባምንጭ ማሸነፍ ብዙ ልዩነት አያመጣም ብዬ ነው የምገምተው።
አሰልጣኝ ዘነበ ፍሰሀ – ወላይታ ድቻ
ጨዋታው አጠቃላይ ጥሩ ነበር። ከውጤት ማጣት ጋር ተያይዞ ጫና ውስጥ ገብተን ነበር። ዛሬ ተጨዋቾቻችን ያደረጉት እንቅስቃሴ ጥሩ ነበር። የተሰጣቸውን ታክቲክም በከፊል ስለተገበሩ ከሞላ ጎደል ጨዋታው መልካም ነበር። ከኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተሳትፎ በኃላ ውጤት ማጣታችን ተጨዋቾቻችንን ውጥረት ውስጥ ክቷቸዋል። በዚህ ምክንያት ውጤት ከመፈለግ የተነሳ ነው በሁለተኛው አጋማሽ ኳሶች ይበላሸብን የነበረው።