በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 24ኛ ሳምንት ላለመውረድ በሚደረገው ትግል ውስጥ ተሳታፊ የሆኑት አርባምንጭ ከተማ እና ወልዲያን ያገናኘው ጨዋታ በአርባምንጭ ሁለገብ ስታድየም ተካሂዶ አርባምንጭ ከተማ 5-0 በማሸነፍ የውድድር ዘመኑን ከፍተኛ ድል ማስመዝገብ ችሏል፡፡
አርባምንጭ ከተማዎች ከጅማ ከተማ ጋር ያለ ግብ አቻ በተለያዩበት ጨዋታ ላይ ጉዳት ያገጠመው አንድነት አዳነን በአሌክስ አማዙ የቀየሩ ሲሆን ተከላካዩን ተመስገን ካስትሮን የአጥቂነት ሚና በመስጠት ወደ ሜዳ ገብተዋል። ወልዲያዎች በበኩላቸው ከኢትዮጵያ ቡናው ሽንፈት መልስ ከመጀመርያ አሰላለፉ ብርሃኔ አንለይ እና ኤደም ኮድዞ እና መስፍን መስፍንን በማሳረፍ ሐብታሙን ሸዋለም ፣ አልሳዲቅ አልማሒ እና በላይ አባይነህን በምትካቸው በመጠቀም ወደ ሜዳ ገብተዋል፡፡
ኢትዮጵያን በአለም ዋንጫ የሚወክሉት ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ የመሩት ጨዋታ ለመመልከት ከወትሮው ለየት ባለ መልኩ ገና በጊዜ ነበር የአርባምንጭ ከተማ ደጋፊዎች ወደ ሜዳው መትመም የጀመሩ ሲሆን ስታድየሙም መልካም ድባብ ተላብሶ ነበር። አርባምንጭ ከተማዎች በረጃጅም ኳሶች ወደ ወልድያ የግብ ክልል ለመድረስ ሲሞክሩ ቢታይም ኢላማቸውን የሳቱ ስለነበሩ ይበላሽባቸው ነበር፡፡ 9ኛው ደቂቃ ላይ ብርሃኑ አዳሙ አክርሮ የመታት ኳስ የመጀመርያ ሙከራ የነበረች ሲሆን ከዚህች ኳስ በመቀጠል 11ኛው ደቂቃ ላይ ጸጋዬ አበራ በመሬት በግራ እግሩ አክርሮ የመታት ኳስ በበረኛው በቀላሉ ተይዛለች፡፡ በጨዋታው መከላከልን ምርጫቸው አድርገው የነበሩት ወልዲያዎች በራሳቸው ሜዳ ለይ ለመቆየት ተገደዋል፡፡ አርባምንጮችም ደግሞ ይሄንን የመከላከል ሲስተም ለመስበር ጥረት ሲያደርጉ ቢቆዩም ጎል ለማስቆጠር ግን 39 ደቂቃ ፈጅቶባቸዋል፡፡ በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ወጣቱ አለልኝ አዘነ በተመስገን ካስትሮ ላይ በተፈፀመ ጥፋት የተሰጠውን ቅጣት ምት በግሩም ሁኔታ ወደ ግብ ቀይሮ አዞዎቹን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።
ከዚህች ጎል በኋላ ወልዲያዎች ጎል ለማስቆጠር ወደ ተጋጣሚያቸው ግብ ክልል ለመድረስ በአንዷለም ንጉሴ አማካኝነት ጥረት ቢያደረጉም ፍሬ አልባ ነበር፡፡ ጨዋታው ሊጠናቀቅ 1 ደቂቃ ሲቀረው ፀጋዬ አበራ ከርቀት ወደ ጎል መትቶ በግቡ አናት ወደ ውጪ የወጣው ኳስ የመጀመሪያው አጋማሽ የመጨረሻ ሙከራ ነበር።
ተመስገን ካስትሮ ጎልቶ በወጣበት ሁለተኛው አጋማሽ ወልዲያዎች የአቻነት ግብ ፍለጋ፣ አርባምንጭም የጎል ልዩነቱን ለማስፋት መጣራቸውን ተከትሎ ክፍት የሆነ እንቅስቃሴ ተመልክተናል፡፡ በተለይ አርባምንጭ ከተማዎች በአምበሉ ጎበና፣ አለልኝ አዘነ እንዲሁም የአጥቂውን ክፍል ለማገዝ ከአጥቂ ጀርባ ሲጫወት የነበረው እንዳለ ከበደ በተጋጣሚያቸው ላይ ጫና መፍጠር ችለዋል፡፡ ሁለተኛ ጎላቸውንም በዚህ አጋጣሚ ነው ማግኘት የቻሉት፤ 53ኛው ደቂቃ ላይ በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው እንዳለ ከበደ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ተመስገን ካስትሮ በአግባቡ ተቆጣጥሮ ወደ ግብነት በመለወጥ የግብ ልዩነቱን ወደ ሁለት አስፍቷል።
አርባምንጮች ከዚህ ግብ መቆጠር በኋላ ተስፋ መቁረጥ የታየበት ወልድያን በተደጋጋሚ ሲፈትኑ ተስተውለዋል፡፡ የወልዲያ የተከላካይ መስመርም በተመስገን ካስትሮ፣ በብርሃኑ አዳሙ እንዲሁም በፀጋዬ አበራ በተደጋጋሚ የሚደርስባቸውን ጫናዎች ለመቋቋም ሲቸገሩ ተስተውሏል። የወልዲያ ተጫዋቾች ሜዳው ላይ ሲያደርጉት የነበረው ደካማ እንቅስቃሴ በተመልካች ዘንድ አግራሞትን ፈጥሮ አልፏል፡፡ በተከላካይ መስመሩ በተደጋጋሚ የሚሰሩት ስህተቶችም ቡድኑን ዋጋ ሲያስከፍሉት ታይቷል። በ70ኛው ደቂቃ ተከላካዮች የሰሩትን ስህተት በመጠቀም አለልኝ አዘነና ተመስገን ካስትሮ ያገኙትን እድል ግብ ጠባቂው ቢሊንጋ ያዳነበት አጋጣሚ ለዚህ እንደ ማሳያ የሚታይ ነበር። አርባምንጮች በአንፃሩ በመስመር አጥቂዎች ፈጣን የማጥቃት ሃይል በመታገዝ በተደጋጋሚ የግብ ክልል ውስጥ በመገኘት ጫና ፈጥረው ተጫውተዋል። በዚህም በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረውና የጨዋታው ኮከብ የነበረው ተመስገን ካስትሮ ወርቅይታደስ አበበ ከመስመር ያሻገረውን ኳስ ብርሃኑ አዳሙ ወደ ግብ ሞክሮ የግብ አግዳሚ ሲመልስበት ኳሷን በፍጥነት አግኝቶ ለራሱ 2ኛ ለክለቡ ደግሞ ሶስተኛዋን ግብ አስቆጥሯል፡፡
ከግቧ መቆጠር ቡኃላ አርባምንጭ ከተማ አማኑኤል ጎበናንና በምንተስኖት አበራ ፣ ብርሃኑ አዳሙን ደግሞ በበረከት አዲሱ ቀይረው አስገብተዋል፡፡ በወልዲያ በኩል ደግሞ ምንያህል ተሾመ እና አማረ በቀለን በማስወጣት ኤፍሬም እና ተስፋ ሚካኤል ቢያስገቡም ተቀይረው በገቡት ተጫዋቾች አማካይነት የተለየ ነገር ለመፍጠር አልቻሉም፡፡ ይልቁንም አርባምንጭ ከተማዎች ይበልጥ የማጥቃት ሃይላቸውን በመጨመር 82ኛ ደቂቃ ላይ ከመስመር በእንዳለ ከበደ አማካኝነት የተሻገረውን ኳስ ተመስገን ካስትሮ ወደ ግብ ቀይሮ አርባምንጭ ከተማ 4-0 እንዲመራ ከማስቻሉም በላይ በግሉም ሐት-ትሪክ መስራት ችሏል።
ጨዋታው መገባደጃ ላይ አርባምንጭ ከተማዎች ተጨማሪ ጎሎች በማስቆጠር የጎል እዳቸውን ለመቀነስ በመሚስል መልኩ በወልዲያ የግብ ክልል በቁጥር በዝተው ጫና መፍጠር ችለዋል። በዚህም የተሳኩ የግብ እድሎችን በመፍጠር ድንቅ ሆኖ የዋለው እንዳለ ከበደ ለተመስገን ካስትሮ ያሻገረውን ኳስ ተመስገን ካስትሮ ሞክሮ ግብ ጠባቂ ቤሊንጋ ሲመልሰው አጠገቡ የነበረው በረከት አዲሱ ወደ ጎልነት በመለወጥ የጎል ልዩነቱን ወደ 5 አስፍቷል። ይህች ጎል በአመቱ አጋማሽ ክለቡን ለተቀላቀለው በረከት አዲሱ ከ1 ዓመት በላይ ከሆነ ጊዜ በኋላ ያስቆጠረው የመጀመርያ ጎል ሆኖ ተመዝግቧል።
ጨዋታው በአርባምንጭ ከተማ 5-0 አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ ወራጅ ቀጠና ውስጥ የነበሩት አዞዎቹ የግብ እዳቸውን ወደ 7 በማውረድ በ26 ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጡ ወልዲያ 20 ነጥብና 19 የግብ እዳ በመያዝ የደረጃው ግርጌ ላይ መቀመጥ ችሏል፡፡
የአሰልጣኞች አስተያየት
የአርባምንጭ ከተማ አሰልጣኝ ጃክሰን ፊጣ
እንዳያችሁት ጨዋታው በጣም አሪፍ ነበር፡፡ልተጫዋቾቹም ከቀን ወደ ቀን በመሻሻል ላይ ናቸው። ጨዋታውንም ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥረን ተጫውተናል፡፡ ወልዲያ የተከላካይ ከፍል ስህተት እንደሚሰራ አወቅ ነበር። ለዛም ነው ተመስገን ከተከላካይነት ወደ አጥቂነት ያመጣሁት፡፡ ሜዳው ላይ ለመተግበር የፈለግነውን አሳይተናል፡፡ ይህ ለኛ ጅማሬያችን ነው ፤ ደጋፊያችንን ከዚህ በላይ አስደስተን ለመካስ እንጥራለን፡፡
የወልዲያ አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው
ጨዋታው በጣም የሚያሳፍር ነበር፡፡ መሸነፍ ያለ ነው፤ ነገር ግን ጥረህ ለፍተህ ሲሆን ነው፡፡ ዛሬ ግን ተጫዋቾች መርሐ ግብሩን ለማሟላት የሚጫወቱ ነበር የሚመስሉት፡፡ ባየሀት ነገር አዝኛለሁ፡፡ በዚህ አይነት በቀጣይ የምናደርገውን ጨዋታ ከዚህ መንፈስ መውጣት ካልቻልን ፕሪምየር ሊጉ ከባድ ሊሆንብን ይችላል፡፡ አርባምንጭ ከተማዎች ጋር የነበረው ተነሳሽነት ፣ ፍላጎት እና የወጣትነት ጉልበት አስገርሞኛል፡፡ ሙሉ በሙሉ ተበልጠን ተሸንፈናል፡፡