ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ| ፋሲል ከተማ ከ ድሬዳዋ ከተማ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 24ኛ ሳምንት ሰኞ ሊካሄዱ ከነበሩ ጨዋታዎች መካከል አንዱ የነበረው የፋሲል ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ በዝናብ ምክንያት ወደ ማክሰኞ ረፋድ መዘዋዘሩ ይታወሳል። ይህን ተከትሎም በሰኞ በቅድመ ዳሰሳ ላይ ካካተትነው ፅሁፍ የዚህን ጨዋታ ዳሰሳ ለብቻ በመነጠል ልናስነብባችሁ ወደድን።

የዚህ ጨዋታ ውጤት ከፋሲል በላይ ለድሬዳዋ እጅግ ወሳኝ ነው። በወራጅ ቀጠና ካሉት ቡድኖች መሀል 25 ነጥብ ላይ ደርሶ እና ሶስት የግብ ዕዳዎች ብቻ ኖረውበት 13ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ድሬዳዋ ከወራጅ ቀጠኔው የማምለጥ ተልዕኮን ይዞ ከአንድ ወር በኃላ ከሜዳው ውጪ ጨዋታ ያደርጋል። በነዚህ ጊዜያት ሳይሸነፍ መዝለቁ አሁን ላይ የተሻለ ተስፋን እንዲይዝ ቢያደርገውም በሚቀጥለው አመት በሊጉ ለመቀጠል ግን የመትረፍ ጉዞው ገና ብዙ ይቀረዋል። ሆኖም ደደቢትን ሜዳው ላይ ከረታ በኃላ ውጤት የራቀው ፋሲል ወደ አሸናፊነት ለመመለስ በማሰብ ለድሬደዋ ከባድ ፈተና እንደሚሆን ይጠበቃል። ለመሀል ሰፋሪነት እየቀረበ የሚገኘው ፋሲል በዋንጫ ፉክክሩ ውስጥ ለመቆየት የነበረው ተስፋ እየደበዘዘ መጥቷል። የአሰልጣኝ ለውጥ ካደረገ በኃላ አሳይቶት የነበረው መነቃቃትም ተቀዛቅዟል። ይህን ጨዋታ ማሸነፍ ከቻለ ግን ወደ መነቃቃቱ ለመመለስ የተሻለ ዕድል የሚፈጥርለት ይሆናል።

በፋሲል ከተማ ስብስብ ውስጥ የያሬድ ባየህ እና አይናለም ኃይለ ጉዳት የተጠበቀ ሲሆን በጉዳትም ሆነ በቅጣት ቡድኑ የሚያጣው ተጨማሪ ተጨዋች አይኖርም። በድሬዳዋ ከተማ በኩል ከሚካኤል አካፉ ፣ ዘነበ ከበደ እና ያሬድ ታደሰ በተጨማሪ ሐብታሙ ወልዴም በጉዳት ከጨዋታው ውጪ እንደሚሆን ተሰምቷል።

ድሬዳዋ ከተማ ከዚህ ጨዋታ የሚያገኘው ነጥብ ወሳኝ ከመሆኑ አንፃር ከሌሎቹ ጊዚያት አንፃራዊ ጥንቅቄ የሚያደርግበት ፋሲል ከተማ ደግሞ ሙሉ ለሙሉ ማጥቃት ላይ የሚያተኩርበት የጨዋታ እንቅስቃሴ ይጠበቃል። ወደ ኃላ ካፈገፈገ ቡድን ጋር ሲገናኙ ክፍተቶችን ለማግኘት የሚቸገሩት ፋሲሎች በመስመር አጥቂዎቻቸው አማካይነት የሜዳውን ስፋት ተጠቅመው በድሬ የኃላ መስመር ተሰላፊዎች መሀል ክፍቶችን ለመፍጠር እንደሚንቀሳቀሱ ይጠበቃል። ቡድኑ እየተዳከመ በመጣው የማጥቃት ሂደቱ ላይ የማጥትቃ ባህሪ ባላቸው አማካዮቹ ላይ መሻሻሎችን ማድረግም ይጠበቅበታል። ከኢማኑኤል ላርያ ፊት የሚኖሩ ስሶት አማካዮቻቸውን ወደ ኃላ መለስ አድርገው ክፍተት ባለመስጠት እና የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን በመጠባበቅ እንደሚጫወቱ የሚጠበቁት ድሬዎች አንድ አጥቂ በመቀነስ ሳውሬል ኦልሪሽን ተጠቅመው የአማካይ ክፍል ተሰላፊዎቻቸውን ቁጥር ወደ አምስት ከፍ የማድረግ አማራጭም ይኖራቸዋል። በሁለቱም አቀራረቦች ዮሴፍ ዳሙዬ ፣ ዘላለም ኢሳያስ እና ሱራፌል ዳንኤል ቡድኑ ወደማጥቃት በሚሸጋገርባቸው ወቅቶች ላይ የሚኖራቸው ሚና ግን ወሳኝነቱ የጎላ ነው።

የእርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– በሊጉ ሶስት ጊዜ ተገናኝተው ድሬዳዋ አንዱን ሲያሸንፍ በሁለቱ አቻ ተለያይተዋል። ፋሲል ምንም ድል አላስመዘገበም። ድሬዳዋ 2፣ ፋሲል አንድ ጎል አስቆጥረዋል።

– ጎንደር ላይ አንድ ጨዋታ (2009) ተከናውኖ ያለ ግብ ተጠናቋል።

– ዘንድሮ በመጀመርያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ 1-1 ሲለያዩ ለተጨማሪ ህክምና ወደ ባንኮክ ያመራው ዓይናለም ኃይለ በጨዋታው ላይ መጎዳቱ የሚታወስ ነው።

– ፋሲል ከተማ በቅዱስ ጊዮርጊስ ከተሸነፈ ወዲህ ጎንደር ላይ ባደረጋቸው 5 ጨዋታዎች ሽንፈት ያላስተናገደ ሲሆን ድሬዳዋ በአንፃሩ ከሜዳው ውጪ ድል ካስመዘገበ አንድ አመት አልፎታል።

ዳኛ

– ኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ ይህን ጨዋታ የመዳኘት ሀላፊነት ተሰጥቶታል።