11፡00 ላይ ኢትዮጵያ ቡናን ከደደቢት ያገናኘው የ24ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጨረሻ ጨዋታ ጥሩ ፉክክር ተደርጎበበት 2-2 -በሆነ ውጤት ተጠናቋል።
ሁለቱ ቡድኖች በመጨረሻ የሊግ ጨዋታቸው ከተጠቀሙት የመጀመሪያ አሰላለፍ አንፃር የዛሬው ቡድናቸው ሲታይ በርካታ ለውጥ የተደረገው በደደቢት በኩል ነበር። ኢትዮጵያ ቡና አማካይ ክፍል ላይ በወልዲያው ጨዋታ ዕድል ተሰጥቶት በነበረው አዲስ ፍሰሀ ምትክ ኤልያስ ማሞን ከመስገባቱ በቀር ሌላ ለውጥ አልተስተዋለበትም። ደደቢት በግብ ጠባቂ ቦታ ጉዳት የገጠመው አማራህ ክሌመንትን በታሪክ ጌትነት ሲተካ ሌላው ጉዳት ላይ የሚገኘው የግራ መስመር ተከላካዩ ብርሀኑ ቦጋለን ቦታ በኄኖክ መርሻ ሸፍኗል። ከድር ኩሊባሊ ወደ አማካይ ክፍል በመዘዋወሩ ደግሞ አንዶህ ኩዌኩ በመሀል ተከላካይነት ከደስታ ደሙ ጋር ተጣምሯል። ከዚህ በተጨማሪ ያልተጠበቀ ለውጥ በተደረገበት የአማካይ ክፍሉ ላይ የአብስራ ተስፋዬ እና አቤል እንዳለ ወደ ተጠባባቂነት ሲወርዱ ከቅጣት የተመለሰው የሽመልስ ጉግሳ መግባትም ከኢትዮ ኤሌክትሪኩ ጨዋታ የተደረገ ሌላኛው ለውጥ ነበር።
የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ እንቅስቃሴ የሜዳው አስቸጋሪነት ተጨምሮበት የሁለቱም ቡድኖች የማጥቃት ዕቅዶች በርካታ የግብ ዕድሎችን ያልፈጠሩበት ነበር። ሆኖም የጨዋታው የመጀመሪያ ሙከራ 4ኛው ደቂቃ ላይ ለጥቂት ወደ ውጪ በወጣችው የኤልያስ ማሞ ወደ ግራ ያዘነበለች የቅጣት ምት የታየ ነበር። ከአምስት ደቂቃዎች ቆይታ በኃላ ደደቢቶች ወደ ግራው የማዕዘን ምት ከቀረበ ቦታ ያገኙት የቅጣት ምት ግን ወደ ግብነት ተቀይሯል። ቅጣት ምቱ በጌታነህ ከበደ ከተመታ በኃላ በሀሪሰን እና በቡድን ጓደኞቹ በአግባቡ ከአደጋ ዞን ሳይርቅ ቀርቶ በስዩም ተስፋዬ አማካይነት የተቆጠረ ነበር። ከጎሉ መቆጠር በኃላ ሁለቱ ተጋጣሚዎች በመረጧቸው አጨዋወቶች አጥቅተው የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የሞከሩባቸው ቢሆኑም ስኬታማ ነበሩ ለማለት አያስደፍርም።
ከድር ኩሊባሊን በተከላካይ አማካይነት አሰልፎ ለአስራት መገርሳ የማጥቃት ኃላፊነቱን የሰጠው ደደቢት አማካይ ክፍል ላይ በተወሰደበት የበላይነት እንደወትሮው ኳስ መስርቶ ለመጫወት ተቸግሮ ታይቷል። ቡድኑ ለማጥቃት በሚሞክርባቸው አጋጣሚዎች ወደ ሁለቱ አጥቂዎች ለመድረስ ይጠቀምባቸው የነበሩት የመስመር አማካዮቹ ሽመክት ጉግሳ እና ኤፍሬም አሻሞ እንቅስቃሴ ፍሪያማ ሊሆን አልቻለም። ለጌታነህ በቀጥታ ከሚደርሱ ኳሶች ዕድሎችን ለመፍር የተሞከረበትም ሂደት ዕምብዛም ስኬታማ አልሆነም። የቡድኑ ተሰላፊዎች በማጥቃት ጊዜ ለመከላከል ከተሳቡበት ጥልቅ ቦታ እየተነሱ ወደ ኢትዮጵያ ቡና የሜዳ ክልል እስኪደርሱ ባለው ጊዜ ውስጥ የቁጥር ብልጫ እየተወሰደባቸው ኳሶቻቸው ይበላሹባቸውም ነበር። በጥቅሉ መሀል ሜዳ ላይ የነበረው የቀድሞው የቡድኑ መዋቅር በዚህ ጨዋታ ላይ አለመኖሩ ንፁህ የግብ ዕድሎች እንዳይፈጠሩ እና በሜዳው ምቹ አለመሆን ከተከላካዮች ስህተት የሚገኙ ዕድሎችን ለመጠቀም እንዲከብዳቸው መንስኤ ሆኗል።
ከተጋጣሚያቸው የተሻለ የግብ ዕድሎችን የፈጥሩት ኢትዮጵያ ቡናዎችም በሁለቱ መስመሮች ይከፍቷቸው የነበሩት ጥቃቶች በፈለጉት መጠን በደደቢት ሳጥን ውስጥ እንዲገኙ ያስቻሏቸው አይመስልም። የክሪዚስቶም ንታንቢ የርቀት እና የማዕዘን የግንባር ሙከራዎች እንዲሁም የአቡበከር ነስሩ እና የሳምሶን ጥላሁን ሙከራዎች ተጠቃሽ ቢሆኑም ቡድኑ አግኝቷቸው እንደነበሩት ክፍተቶች ከዚህም በላይ ተጭኖ መጫወት ይችል ነበር። በተለይ ደደቢቶች ወደ መከላከል ሲሸጋገሩ ከነበራቸው ዝግ ያለ ፍጥነት የኢትዮጵያ ቡና አማካዮች ሰብረው የመግባት አጋጣሚዎች ቢፈጠርላቸውም የአብዛኞቹ ኳሶች መዳረሻ የነበሩት ግን በሁለቱ መስመሮች በኩል የተሰለፉት ሚኪያስ መኮንን እና ሳሙኤል ሳኑሚ ነበሩ። ይህ ሁኔታ መደጋገሙ ተገማች ያደረገው በሚመስል መልኩ ከሳኑሚ ወደ ውስጥ የሚጣሉ ኳሶች በደደቢት ተከላካዮች ሲመለሱ ሚኪያስ ወደ ውስጥ ለመግባት ያደርግ የነበረው ጥረትም በተደጋጋሚ ሲበላሽበት ነበር። ሆኖም ቡድኑ 22ኛው ደቂቃ ላይ ፈጥሮት እንደነበረው እድል 45ኛው ደቂቃ ላይም በሳሙኤል ሳኑሚ ወደ ሳጥን ዘልቆ በመግባት ከፈጠረው አጋጣሚ አስራት መገርሳ ኤልያስ ማሞ ላይ በሰራው ጥፋት የፍፁም ቅጣት ምት አግኝቶ በሳሙኤል ሳኑሚ በማስቆጠር አቻ መሆን ችሏል።
ሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታው ፍጥነት የጨመረበት እንዲሁም ሙከራዎችን እና ጎሎችንም ያስመለከተን ነበር። 47ኛው ደቂቃ ላይ ሳሙኤል ሳኑሚ በቀኝ መስመር ሰብሮ በመግባት ያደረገው ሙከራ እና ከአንድ ደቂቃ በኃላ ደግሞ ደደቢቶች ከአማኑኤል ዮሀንስ በተቀማ ኳስ ባገኙት የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚ ጌታነህ ከርቀት ያደረገው ሙከራ ሁለተኛውን አጋማሽ በተነቃቃ መንፈስ አስጀምረውታል። በመጀመሪያው አጋማሽ የነበረባቸውን ድክመት አስተካክለው የገቡት ኢትዮጵያ ቡናዎች የማጥቃት ፍጥነታቸው ጨምሮ ተጋጣሚያቸው የመከላከል ቅርፁን ከመያዙ በፊት ወደ አደጋ ዞን ይቀርቡ የነበረ በመሆኑ አስፈሪነታቸው ጨምሮ ነበር። 56ኛው ደቂቃ ላይ ከኩዌኩ በተቀማ ኳስ 57ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ከኤልያስ ማሞ በተላከ ኳስ በአበበከር ነስሩ እና ሳሙኤል ሳኑሚ የተደረጉት ሙከራዎች ተጠቃሽ ናቸው። በ66ኛው ደቂቃ ላይ በሰከንዶች ልዩነት በሚኪያስ መኮንን እና አቡበከር ነስሩ ጥምረት በሁለት አጋጣሚዎች የተፈጠሩት ዕድሎችም ጎል ለመሆን ተቃርበው ነበር።
ተደጋጋሚ ጫና ውስጥ የገቡት ደደቢቶች አቤል ያለውን እና አስራት መገርሳን በአቤል እንዳለ እና የአብስራ ተስፋዬ በመቀየር መሀል ለመሀል የሚሰነዘርብቻውን ጥቃት በማርገብ ቀጥተኛ ጥቃት ለመሰንዘር ያደረጉት ጥረት 71ኛው ደቂቃ ላይ ፍሬ አፍርቷል። በአቤል እንዳለ ፣ ኤፍሬም አሻሞ እና ጌታነህ ከበደ መሀከል የተደረገው የማልሶ ማጥቃት ቅብብል በጌታነህ ድንቅ አጨራረስ ታጅቦ ለቡድኑ ሁለተኛ ጎል ሆኗል። ግቧ ኢትዮጵያ ቡናዎች እጅግ በተነቃቁበት እና በተደጋጋሚ ወደ ጎል እየደረሱ በነበረበት ወቅት የተገኘች መሆኗ ለደደቢት እጅግ ወሳኝ አድርጓት ነበር። 75ኛው ደቂቃ ላይም ደደቢቶች ሌላ ጥሩ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚ ያገኙ ቢሆንም ጌታነህ ከኤፍሬም ተቀብሎ ያደረገው የርቀት ሙከራ ኢላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል። ነገር ግን 79ኛው ደቂቃ ላይ ለአቡበከር ነስሩ ከፍ ብላ የተላከችውን ኳስ ለማጨናገፍ የወሰደው እርምጃ ኩዌኩ አንዶህን በቀይ ካርድ ከሜዳ እንዲወጣ አድርጎት የቀሩት ደቂቃዎች ለደደቢት ፈታኝ ሆነዋል።
በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የቁጥር ብልጫ ያገኙት ኢትዮጵያ ቡናዎች አስራት ቱንጆ እና ቃልኪዳን ዘላለምን ቀይረው በማስገባት ወደ ኃላ ያፈገፈገው ተጋጣሚያቸውን ከግራ እና ቀኝ በሚነሱ ተሻጋሪ ኳሶች ማስጨነቅ ችለዋል። አልፎ አልፎ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን ለመጠቀም ፍላጎት የሚያሳዩት ደደቢቶች በአንፃሩ መከላከል ላይ ትኩረት አድርገዋል። ከ20 አመት በታች ቡድኑ መጥቶ ለዋናው ቡድን የመጀመሪያ ጨዋታውን ውጥረት በበዛበት ደቂቃ ላይ ለማድረግ የገባው ቃልኪዳን 88ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር ጥሩ ኳስ ወደ ሳጥን ውስጥ አድርሶ አቡበከር እና ሳኑሚ ሳይደርሱበት ቀርተዋል። ነገር ግን ከደቂቃዎች በኃላ በግራ መስመር ቃልኪዳን ያሻማዋል ተብሎ የተጠበቀውን ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ በመምታት ኢትዮጵያ ቡናን ከመሸነፍ ያዳነች ግብ አስቆጥሯል። አምስት ደቂቃዎች የተጨመሩበት ጨዋታም እስከማብቂያው ድረስ ድንቅ ፉክክር ተደርጎበት 2-2 ተጠናቋል።
የአሰልጣኞች አስተያየት
አሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜስ – ኢትዮጵያ ቡና
ውጤቱ አሳዝኖናል። እንደነበረን በርካታ የማግባት አጋጣሚ ማሸነፍ ይገባን ነበር። ተጋጣሚያችን በማጥቃቱ ጥሩ ነበር። እኛም ጨዋታውን ተቆጣጥረን የራስችንን ጨዋታ ተጫውተናል። አጥቂያቸውን በመቆጣጠሩ በኩል ግን ደከም ብለን ነበር። ቡድኔ በተለይ በሚጫወትበት መንገድ ላይ እየተሻሻለ እንደሆነ ይሰማኛል። አሁን 4ኛ ደረጃ ላይ ነን 37 ነጥቦች ላይም ደርሰናል። ቀሪውን ጊዜ ያለምንም ስህተት መጓዝ ይጠበቅብናል።
ም/አሰልጣኝ ጌቱ ተሾመ – ደደቢት
ጨዋታው በኛ በኩል በጣም ጥሩ ነበር። የነበረው ፉክክርም ጥሩ ነበር። ተጨዋቾቻችን የሚችሉትን አድርገዋል። ሊመሰገኑም ይገባል። መሀል ላይ ኩሊባሊ እና አስራትን ተጠቅመናል የተወሰኑ ስህተቶች የነበሩ ቢሆንም ተበልጠን ነበር ብዬ ግን አላስብም። በኔ እይታ ተጋጣሚያችን የተሻለ ነበር ብዬ አላስብም እኛም ብዙ ሙከራዎች አድርገናል። የሜዳው ምቹ ባለመሆኑ ምክንያት ወደ ውጪ የወጡብን ኳሶች ቢኖሩም ጥሩ ተንቀሳቅሰናል።