የሰው ሰር መገኛ ምድር አፋር የፊታችን እሁድ በሚደረገው የፌዴሬሽን ምርጫ እንግዶቿን ለመቀበል ዝግጅቷን ማጠናቀቋን አዘጋጅ ኮሚቴው አሳወቀ።
የኢትዮዽያ እግርኳስ ፌዴሬሽንን ለቀጣዩ አራት አመታት የሚመሩት ፕሬዝዳንት እና ስራ አስፈፃሚ አባላትን ለመምረጥ ከመስከረም 30 ጀምሮ በተለያዩ ምክንያቶች ሳይደረግ ቆይቶ በእግርኳሱ የበላይ አካል ፊፋ አስገዳጅ ውሳኔ መሰረት የፊታችን እሁድ ግንቦት 26 በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ ሊደረግ የመጨረሻ ቀጠሮ ተይዞለታል።
ሰመራ ከአንዴም ሁለቴ ምርጫውን ለማካሄድ በተሰጣት እድል መሰረት ለሆቴል እና ለመስተንግዶ ከፍተኛ ወጪ በማውጣት እንግዶቿን ለመቀበል እየተጠባበቀች ባለችበት ወቅት ምርጫው በመራዘሙ ከፍተኛ ኪሳራ እንዳስተናገዱ የሚገልፁት የአዘጋጅ ኮሚቴ አባላት በአሁኑ የመጨረሻ የምርጫ ቀጠሮ የፊታችን እሁድ ግንቦት 26 ሰመራ ላይ የሚደረገውን ምርጫ በጥሩ ሁኔታ ለማካሄድ እንደተዘጋጁ ገልፀዋል።
” ምንም እንኳ ወቅቱ ለክልሉ ህዝብ የረመዳን ፆም ወር መሆኑ አስቸጋሪና አድካሚ ቢያደርግም የሚመጡት የስብሰባ ተሳታፊዎችን በሙሉ በጥሩ እንግዳ ተቀባይነት ባህል ተቀብሎ ለመሸኘት በሆቴል፣ በመስተንግዶ፣ በትራንስፖርት እና በሌሎች አስፈላጊ ጉዳዮች ሁሉ የክልሉ አስተዳደር እና ህዝብ ዝግጅታቸንን አጠናቀን እንግዶቻችንን ለመቀበል እየጠበቅን እንገኛለን።” በማለት የአዘጋጅ ኮሚቴው አባል የአፋር ክልል እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝደንት አቶ መሀመድ ያዮ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል።