የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የምርጫ አስፈፃሚ ኮሚቴ ዛሬ ባደረገው ስብሰባ የስራ አስፈፃሚዎች ምርጫ አካሄድ ላይ ከስምምነት ሳይደርሱ ለነገ ቀጠሮ ይዘው ተለያይተዋል።
ፌዴሬሽኑን የሚመሩ አንድ ፕሬዝደንት እና አስር የስራ አስፈፃሚ አባላትን ለመምረጥ ግንቦት 26 በአፋር ክልል ሰመራ ሊካሄድ በጣት የሚቆጠሩ ቀናት በቀረበት በአሁኑ ወቅት የምርጫውን ሂደት እንዲያስፈፅሙ ሚያዚያ 27 በካፒታል ሆቴል በተካሄደው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ የተመረጡት አምስት አባላት የያዘውና በአቶ አስጨናቂ ለማ ሰብሳቢነት የሚመራው የምርጫ አስፈፃሚ ኮሚቴ በወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት የመጨረሻዎቹ እጩ ተወዳዳሪዎች የፕሬዝደንትና የስራ አስፈፃሚ ዝርዝር እና ሌሎች የስራ ተግባራትን በማጠናቀቅ የምርጫውን ቀን እየተጠባበቀ ይገኛል።
አስመራጭ ኮሚቴው ዛሬ ባደረገው መደበኛ ስብሰባ ምርጫው በምን መልኩ ይደረግ በሚለው ጉዳይ ላይ ውይይት ሲደረግ በዋናነት የስብሰባው አጀንዳ የነበረው አስር አባላት የሚመረጡበት የስራ አስፈፃሚ አባላት ምርጫው በምን መልኩ ይሁን በሚለው ጉዳይ ላይ ሁለት ሀሳቦች ተነስተዋል።
አንደኛው በየክልሉ አንድ ተወካይ ይመረጥ የሚለው ነው። ይህ ማለት ከአንድ ክልል አራት ሰው ቢወከል አንዱ ከፍተኛ ድምፅ ያገኘው ብቻ ይግባ የሚል ሲሆን የሕ የሚፀድቅ ከሆነ አፋር፣ ደቡብ፣ ኢትዮ ሶማሌ እና ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ በእጩነት የቀረቡት ተወዳዳሪዎች ያለምርጫ በቀጥታ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ይሆናሉ። በሁለተኝነት የተነሳው ሀሳብ ደግሞ ለሁሉም (22) እጩ ተወዳዳሪዎች እኩል የማሸነፍ እድል የሚሰጠው ምርጫ ነው። በዚህ ሀሳብ ግለሰቡ ከየትኛውም ክልል የመጣ ቢሆን በምርጫው የተሻለ ድምፅ ካገኘ የኮሚቴው አባል መሆን ይችላል። አስመራጭ ኮሚቴው አባላት በሁለቱ ሀሳቦች ዙርያ ሰፊ ውይይት እና ክርክር አድርገው በመጨረሻም ከውሳኔ ላይ ሳይደርሱ ለነገ በይደር እንደተለያዩም ከፌዴሬሽኑ አካባቢ መረጃ አግኝተናል።
የምርጫው አስፈፃሚው ኮሚቴ በዚህ ጉዳይ ላይ የመጨረሻ ውሰኔ ነገ የማይሰጥ ከሆነ እሁድ ግንቦት 26 ሰመራ ላይ በሚደረገው የምርጫ ጉባኤ ላይ በተሳታፊዎች በኩል ትልቅ የክርክር ርዕስ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።